‹‹ ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል›› 1ጴ 4፣8
‹‹ኃጢአት አንዳች የእግዚአብሔር ፀጋ፣ ሰማያዊ በረከት፣ በነፃ የተቸረን የለጋስ አምላክ ሥጦታ የማጣት ትርጉም ያለው ክፉ የመንፈስ ደዌ ነው፡፡ የዘላለሙን አምላክ ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ ለጊዜውም ቢሆን ያደናቀፈ፣ ልዑላዊ ክብር ተችሮት በአምላክ አምሳያ የተፈጠረውን ሰው ያዋረደ፣ የአዳምን ውበት ያጠፋ፣ የሔዋንን ደም ግባት ያረገፈ፣ የልጆቻቸውን ዕድሜ በበርካታ መቶ ዓመታት የቀነሰ ይኸው የሰው ልጆች የዕድሜ ልክ ቀበኛ ‹‹ኃጢአት›› ነው፡፡
ኃጢአት የሚበልጠው የሚሽረው እስኪመጣ ድረስ የሰዎችን ማንነት የመለወጥ ብቃት፣ የህይወት አቅጣጫን የመቀየር ብርታት፣ የዓለምን ጉዞ ወደ ፈቃዱ የማዞር አቅም ነበረው፡፡ ስለሆነም የምድር ፍጥረትን ገዢ አንገቱን አስደፍቶ በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ገዛው፡፡ አዳም ሊነግስባትና ሊረባባት የተሰጠችውን ምድር በምልአት አፍኖ በውስጧ ያሉትን ሁሉ ነገሰባቸው፤ ረባባቸው፡፡ አዋቂውን ፍጡር አሳውሮ በድንቁርናና ባለማስተዋል ጠፍር ተብትቦ የፈጠረውን አምላክ አስረስቶ እንጨት ያስጠረበው፣ ድንጋይ ያስለዘበው፣ ብረት ያስቀለጠው ይኸው ‹‹ኃጢአት›› ነው፡፡ ‹‹በአንድ ሰው ምክንያት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ›› ሮሜ 5፣12 ተብሎ እንደተፃፈ የኃጢአት ምክንያቱ አንድ ቢሆንም ርባታው ግን በመላው የሰው ልጆች ልብ ተቀፍቆፎ በአንደበታቸው በገፃቸውና በብልቶቻቸው ሁሉ ስለተፈለፈለ ብዛቱ የምድር አሸዋና የሰማይ ከዋክብት ቢባዙና ቢበዙ የማይተካከሉት ኁልቆ መሳፍርት ከ እስከ የሌለው ሆኗል፡፡
ስለሆነም እግዚአብሔር ከሰማይ ሆኖ ሲጎበኝ ምድርና ፍጡራን ሲመለከት የደስታ አምላክ እስኪከፋው፣ በፍጡሩ እስኪያዝን፣ በሥራው እስኪፀፀት ድረስ የሚጠቀስ ሁነኛ ሰው እንዳጣ ፍርድና ፅድቅንም እንዳላገኘ ተነግሯል ኢ፡ 59፣16፡፡ የዚህን ምክንያቱ ደመና ሰማይን እንደሚሸፍን ውሃም ሸለቆን እንደሚከድን ኃጢአትም ምድርንና ምድራውያንን ውጦአቸዋልና ከፀበሉ ያልደረሰው ከምሬቱ ያልተጎነጨ ባለመኖሩ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ፃዲቅ የለም አንድ ስንኳ አስተዋም የለም እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፡፡
ሁሉ ተሳስተዋል በአንድነትም የማይጠቀሙ ሆነዋል፡፡ ሁሉ ኃጢአት ሰርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል›› ተብሎ የተፃፈ በሮሜ፡ 3፡11፣23፡፡ *የሚደንቀው የኃጢአት ብዛቱ ምንም መሥፈሪያና መዘርዘሪያ መመዘኛና መመጠኛ ቢታጣለት የበደል ስፍዓቱ የምድርን ክበብ ዘልቆ የህዋን ክልል ቢሸፍን አምላካዊ ፍቅር ከዚህ እጅግ በዝቶ ያለልክም ተርፎ የብዙ ብዙ የሰፊም ሰፊ የሆነውን ኃጢአት ሊወጠውና ሊሸፍነው መቻሉ ነው፡፡ የአምላካችን ፍቅሩ ከጥልቆቹ ሁሉ የጠለቀ ከአንሰርቶች ሁሉ የረዘመ ለስፋቱም የአድማስ ጥግ የሌለው በመሆኑ በእርግጥ የኃጥያትን ብዛት ይሸፍናል፡፡
የሰው ልጅ የኃጢአት ብዛት ውጦት ድምፁ በማይሰማበት፣ ጩኸቱ በማይደመጥበት ሰዓት፤ የኃጢአት ብርታት አቅም አሳንሶት፣ ጉልበት አሳጥቶች ጌታውን መከተል ባልቻለበት ጊዜያት፤ የኃጢአት ፅልመጽት ህሊናውን ጋርዶት፣ዓይኑን አሳውሮት የአምላኩን ፈቃድ መለየት በተሳነው ወቅት፤ የጭንቅ ቀን ደራሽ የሆነለት በብቃቱና በብርታቱ ከሁሉ የሚልቀው እንዲያው በነፃ የተገለፀው አምላካዊ ፍቅር ነበር፡፡ ይህንኑ ቅጥ ያጣ ማህበራዊ ኑሮ፣ የተበላሸ አስተሳሰብና በኃጢአት ቀንበር የወደወቅን ህብረተሰብ ለመታደግ ምክንያት ሊሆን የሚችል የሰው ወገን ስላልተገኘ የእግዚብሔር የገዛ ክንዱ መድኃኒት እንዳመጣለት ፅድቁም እንዳገዘው ተጠቅሷል፡፡ ‹‹በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘልዓለም ህይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና›› ዮሐ 3፣16፡፡ እንግዲህ የሰዎችን ሕይወት፣ ታሪክ፣ ስምና መንገድ የቀየረ ይህ እንዲው ተብሎ የተገለፀው ምክንያት የሌለው ፍቅር ነበር፡፡ ልጅ ተብሎ የተገለፀው ጌታ ኃያል አምላክ፣ የሰላም አለቃና የዘለዓለም አባት ተብሎም የተጠራ የዘመናት ሽማግሌ እንጂ እንደሰው ዘመንና ወራት የሚቆጠሩለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ለአባቱ የባህርይ ልጅ ነውና ልጅየውም ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው ‹‹አንድያ›› ተብሎ የተጠራ፡፡ እንደልጅነቱም የራሱም ፈቃድ የሆነውን የአባቱን ፈቃድ ሊፈፅም የሰው ልጆች ፍቅር አገብሮት እንደሰው ተገለፀ፡፡ ‹‹ፍቅር ሰሀቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብፅሆ እስከለሞት›› ኃያል ወልድን ፍቅር ከመንበሩ ሳበው እስከሞትም አደረሰው፡፡ አዎን! ከሰዎች አዕምሮና አቅም በላይ የሆነውን ኃጢአት በፅድቁ ያንበረከከው የእግዚአብሔር ፅድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ለመለኮታዊ ጌታ መገለፅ በእኛ መካከል ማደርና ስለኃጢአታችን መሞት ብቸኛው ምክንያት ወሰን የሌለው ፍቅሩ ነበር፡፡
ይህም አምላካዊ ግብር ለሰው ልጆች የአምላካቸውን ውዴታ የሚያረጋጋጡበት ጽኑ ማስረጃ ነው፡፡ ሐዋርያውም ‹‹ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለእኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል›› ሲል መስክሯል ሮሜ 5፣8 እግዚአብሔር በባህሪው ፍቅር በመሆኑ ፍቅር ወለድ አምላካዊ ሥራዎቹ እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ ሰውን ከአለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ በምናብ እንኳ በማይታወቅበት ጊዜ በግዙፍ አካል አቁሞ በሰማይና በምድር እውቅና የሰጠው፣ ህልውና ያገኘው ማንነት የሰማያዊውን አምላክ መልክና ምሳሌ ተላብሶ ወደር ለማይገኝለት ክብር የበቃው በእግዚአብሔር ፍቅር ነበር፡፡ ይኸው ፍቅር አንድ ጊዜ የወደደውን አዳም እስከመጨረሻው በመውደድ ከእርሱ በፊት የተፈጠሩትን ከሰማይ በታች ያሉትን ፍጥረታት ሁሉ አስገዛለት፡፡ አምላካዊ ፍቅር በጊዜ፣ በቦታና በሁኔታ የማይገደብ በመሆኑ የጌታውን ፍቅር የዘነጋ ሥጦታውን ልብ ያላለው ሰው ትዕዛዝ ተላልፎ እርቃኑን በቀረ ጊዜ ፍርሃቱን በቅጠል ሊጋርድ ሲጥር ቁርበት ያለበሰው፣ ከደስታ ምድር ሲባረር እንደወጣ ላይቀር ተስፋ የሰጠው፣ የተስፋውን ቃልም በዘመን ፍፃሜ አንድ ልጁን በመላክ ያረጋገጠው የፍቅር መገኛ ምንጭ ልዑል አምላክ ነበር፡፡ በሰው ላይ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው የሚገልፀው መለኮታዊ ጥበቃ፣ ለሥጋዊ ምግቡ በሚያገኘው ምድራዊ በረከት፣ ከሀዘኑ ከጭንቀቱና ከፍራቻው በላይ በሚታደለው የሰላምና የመጽናናት መንፈስ የእግዚአብሔር ፍቅር በየጊዜውና በየሰዓቱ ይገለጣል፡፡ ይልቁንም ወሰን በሌለው ትዕግስቱ በኃጢአት ምክንያት ከፈቃዱ ሲጣላ ከሃሳብ ሲጋጭ የሚገኘውን ሰው ዓይኑ እንዳየች ሳይፈርድ ጆሮው እንደሰማ ሳይበይን ለንስሐ ዕድሜ መስጠቱ ሌላው ዓይነተኛ የፍቅሩ መግለጫ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን የፍቅር ሥራ የሕያው አምላክን የፍቅር ስጦታ መዘርዘር የዝናብን ጠብታ የመቁጠር ያህል ነው፡፡
እንዲያው ነቢዩ እንዳለው ‹‹የእግዚአብሔር ቸርነት ምድርን ሞላች›› መዝ፡ 32፣5 ሐዋርያውም እንደገለፀው ‹‹ስለማይነገር ሥጦታው እግዚአብሔር ይመስገን›› 2ቆሮ 9፣15 ብሎ ማለፉ የሚቀል ይመስላል፡፡ የዚህ ድንቅ ፍቅር ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር በባህሪው ፍቅር ነውና በአርአያው ለፈጠረው ሰው የሰጠው ሕግ የፍቅር ሕግ ነበር፡፡ የተዘረዘሩ በርካታ ህግጋት ቢኖሩም እንኳን ሕግጋት ሁሉ ፍቅረ እግዚአብሔርና እና ፍቅረ ቢፅ በተሰኙ ሁለት ሕግጋት ይጠቀለላሉ፡፡ የፍቅር አምላክ እግዚአብሔር ከሁሉ በፊት ሰዎች እርስ በርሳቸው አጥብቀው እንዲዋደዱ አዟል፡፡ ፍቅር የክርስትና ሃይማኖት መሠረት፣ የአምላክ ከሰማይ ወደ ምድር የመውረድ ምስጢር፣ የጌታ ልጆች የእምነት ማህተብ፣ የደቀመዝምርነት ልዩ ምልክት ነው፡፡ ስለሆነም ከምንም ነገር በላይ ከየትኛውም ነገር በፊት ክርስቲያኖች ሊሸከሙት የሚገባ መስቀል፣ ሊያነግቡት የሚገባ ዓርማ ሊሆን ይገባል፡፡ ፍቅር የሌለበት እምነት፣ ፍቅር የጎደለው ፀሎት፣ ፍቅር ያልቀደመው ቸርነት፣ በፍቅር ያልታጀበ አገልግሎት እንዲው ባዶ ደምሮ ደምሮ በዜሮ የማባዛት ያህል ነው፡፡
ስለዚህም ወገኖች ልብ እንበል ጌታ በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጠን፡፡ ቅድሳት መጻሕፍትን ስንመረምር እንደምናገኘው እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው ዓላማው ፍቅር ነው መኃ 2፣4 ለወደዳቸውም ሰዎች የሚያነሳው የመጀመሪያው ጥያቄ ‹‹የዮናስ ልጅ ስምዖን ሆይ ትወደኛለህን›› የሚል ነው ዮሐ 21፣16 ፡፡ የጌታ ቀዳሚ ትዕዛዙም ‹‹የኃጢአትን ብዛት ፍቅር ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስበርሳችሁ አጥብቃችው ተዋደዱ›› ይሰኛል፡፡ 1ጴ 4፣8፡፡ የዚህ ትዕዛዝ ዓላማ እርስ በርስ አጥብቆ መዋደድ ሲሆን ግቡም የኃጢአትን ብዛት መሸፈን ነው፡፡ በፍቅር የማይፈጠር ታሪክ፣ የማይለወጥ ተፈጥሮ ሕግ፣ የማይከፈል ባህር፣ የማይናድ ተራራ፣ የማይሞላ ሸለቆ፣ የማይገሰፅ ማዕበል የለም፡፡ ፍቅር ከሌለ ሁሉ ባዶ ዜሮ እንደሚሆን ሁሉ በፍቅርም ሁሉ ይሆናል፡፡ የኀጢአት ብዛትም ይሸፈናል፡፡ እንደደም የቀላው ኃጢአት እንደ ባዘቶ የሚጠራው፣ እንደ አለላ የሆነው በደል እንደ አመዳይ የሚነፃው በፍቅር ነው፡፡ ፍቅር ካለ የተናጠልም ሆነ የማኅበር ኃጢአት አይኖርም፡፡ ቢኖርም እንኳ የፍቅር ጌታ በክርስቲያኖች ኅብረት መሐል ባለው የፍቅር ሙላት የኃጢአትን ብዛት ይሸፍነዋል፡፡ ስለዚህ ክርስቲያኖች ቅደም ተከተል እንወቅ፡፡ ቃሉ እንደሚያዘን ከሁሉ በፊት አጥብቀን እንዋደድ፡፡
ብዙ ጊዜ ንፋስን እንደምንጎስም እየሆንን በከንቱ የምንባክነው ፊተኛውን ደረጃ ዘለን በ2ኛውና በ3ኛው ደረጃ ላይ ስለምንቧቸር ነው፡፡ ፍቅር ያለው ሁሉ አለውና በመጀመሪያው ደረጃ ላይ ብንፀና ተስፋዎች፣ ስጦታዎችና በረከቶችን ሁሉ ወደ እና ይወርዳሉ፡፡ ስለሆነም ቂምና በቀልን፣ ቅሬታንና ቅያሜን፣ መተቻቸትና መነቃቀፍን አስወግደን ያለጥቁረትና ያለፊት መጨማደድ በቅንነትና በየዋህነት መንፈስ አጥብቀን ልንዋደድ ይገባል፡፡ ይህ ከሆነ አፅራረ ፍቅር ሌጌዎን ወደ እርያዎቹና ወደ ባህሩ ይጣደፋል፡፡ የጦቢያና የሰንበለጥ ስላቅ የፈርኦንና የስናክሬም ዛቻ የጎልያድና የናቡከደነፆር ትምክህት እንደምናምን የሚቆጠረው በክርስቲያኖች ፍቅር ነው፡፡ በመሆኑም የፍቅር ጌታ ከሁሉ በፊት ይህንን ያዙ አለን፡፡ ፍቅርን መያዝን፣ በፍቅር መኖርን፣ በፍቅር መፅናትን፣ በፍቅር መሞትን ለሁላችን ያድለን፡፡
የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ!
መምህር ጨምር ተፈራ
የሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል መምሪያ ኃላፊ
{flike}{plusone}