ፈቃድ ሳይሰጣቸው በየገዳማቱና አድባራቱ እየተዘዋወሩ የሚሰብኩ ሰባክያን ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግባቸው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለገዳማትና አድባራት ጠንከር ያለ የጹሑፉ መመሪያ አስተላለፈ

640

ጥንታዊትና ሐዋርያዊት የሆነችዋ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሀገራችን ኢትዮጵያን በመንፈሳዊና በማኀበራዊ መስክ ስታገለግል የኖረችና እያገለገለች ያለች መሆንዋን የገለጸው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአገልግሎቱ ከሚሳተፉ አካላት ብዛትና ከቁጥጥር ማነስ የተነሳ አንድ አንድ ችግሮች እየተፈጠሩ ስለሆነ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍና ስብከተ ወንጌል በተሻለ ስፋትና ጥራት ባለው ፣ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን በጠበቀ መልኩ ማስፋፋት ይቻል ዘንድ በቁጥር 1177/482/07 27/03/08 በተጻፈ ደብዳቤ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ ገዳማትና አድባራት መመሪያ አስተላልፎል፡፡
በመሆኑም በርካታ ገዳማትና አድባራት በተላለፈው መመሪያ የስብከተ ወንጌሉን መዋቅር እየጠበቁና እያስጠበቁ የሚገኙ ሲሆን አንድ አንድ ኃላፊነታቸውን የዘነጉ የገዳማትና አድባራት የሥራ አመራሮች መመሪያውን ወደ ጐን በመተው ሕጋዊ ያልሆነ ተግባር ሲፈጽሙ የታዩ ሲሆን ሀገረ ስብከቱ በእነዚህ ኃላፊነታቸውን በዘነጉ የገዳማትና አድባራት የሥራ አመራር ላይ አስፈላጊውን ሕጋዊ ርምጃ እየወሰደ መሆኑን የሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ ዋና ክፍል ኃላፊ መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ ገልጸዋል፡፡
ጥር 17 ቀን 2008 ዓ.ም የነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት በልማትና በፐርሰንት ክፍያ ላቅ ያለ ውጤት ላስመዘገቡ አብያተ ክርስቲያናት በያዘው የመሰጋገኛና የማበረታቻ ሽልማት መርሐ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የሌላቸውና ኢሕጋውያን የሆኑ ሰባክያንን አስመልክቶ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ባቀረቡት ገለፃ ያልተፈቀደላቸው ኢህጋውያን ሰባኪን በተመለከተ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በቁጥር 3075/90/04 በቀን 18/08/04 ዓ.ም ተደጋጋሚ ውሣኔዎችን ያሰተላለፈ መሆኑን በመጥቀስ በስብከተ ወንጌል ስም እየተቧደኑ የቤተ ክርስቲያንን ሰላም ለማናጋት በየጊዜው የሚወጡ፣ የሚወርዱ ፣የሚጥሩ ግለሰቦች አፍራሽ ተልእኮ እየፈጸሙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ ፖትርያርኩም ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት እነዚህ ኢሕጋውያን ሰባክያን፣ከአንዱ ወደ ሌላው እየዘለሉና እየተፈናጠሩ ለሕዝብ ጥቅም ሳይሆን ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ በቤተክርስቲያናችን ሰላምና አንድነት ላይ ችግር ለማድረስ እየጣሩ ስለሆነ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ልጆቻችን ቤተክርስቲያናቸውን ነቅተው ሊጠብቁ ይገባቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ከሀገር ውጭና ከሀገር ውስጥ በመዘዋወር የሃሳብ አቅጣጫቸውን እየቀያየሩ የሚሠሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ቃሉ “ ወእምፍሬሆሙ ተአምርዎሙ” ከፍሬአቸው ታውቋቸዋላችሁ ብሎ እንደአስተማረን ከድርጊታቸው ግንዛቤ በመውሰድ ቅድስት ቤተክርስቲያንን ነቅተንና ተግተን ልንጠብቅ ይገባናል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለገዳማትና አድባራት ያስተላለፈውን ጥብቅ መመሪያ ሙሉ ሐሳቡን እንደሚከተለው

አቅርበናዋል፡፡
ጥንታዊትና ሐዋርያዊት የሆነችዋ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስያን ሀገራችን ኢትዮጵያን በመንፈሳዊና በማኅበራዊ መስክ ስታገለግል የኖረችና እያገለገለች ያለች መሆንዋ ይታወቃል፤ በአሁኑ ወቅትም የምእመናንን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ፍላጎቶች ለማርካት የሚችሉ መጠነ-ሰፊ የአገልግሎት ዘርፎችን ዘርግታ በማገልገል ላይ ትገኛለች፡፡ ከእነዚህም አገልግሎቶች አንዱና ዋነኛው ስብከተ ወንጌል ነው፡፡
የቅድስት ቤተክርስቲያን የህልውና መሠረት የሆነው የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ እየተስፋፋና እየተጠናከረ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ከሥራው ስፋት በአገልግቱ ከሚሳተፉ አካላት ብዛትና ከቁጥጥር ማነስ የተነሣ አንዳንድ ችግሮች እየተፈጠሩ ስለሆነ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍና ስብከተ ወንጌል በተሻለ ስፋትና ጥራት፣ ወጥነት ባለው ሥርዓተ ቤተክርስቲያን በጠበቀ መልኩ ማስፋፋት ይቻል ዘንድ፤
1.በአንዲት አጥቢያ ቤተክርስቲያን አውደ ምሕረት የስብከተ ወንጌል ጉባኤን የማዘጋጀት መብት ያለው የአጥቢያ ቤተክርስቲያን የሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤትና ከዚህ በላይ ያሉ የቤተ ክርስቲያን መዋቅሮች (ወረዳ ቤተ ክህነት፣ ሀገረ ስብከትና ጠቅላይ ቤተክህነት) ብቻ ሆኖ ሌሎች ግለሰቦችና ማኅበራት በገንዘብ፣ በጉልበትና በዕውቀት ከማገልገል ውጭ በቤተክርስቲያናችን ስም የስብከተ ወንጌል ጉባኤን የማዘጋጀት መብትና ኃላፊነት የሌላቸው መሆኑ እንዲታወቅ፤
2.በቤተክርስቲያን መዋቅር ያልተቀጠሩ ሰባክያነ ወንጌል ወደ አህጉረ ስብከት ሔደው ማገልገል ሲፈልጉ በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ቀርበውና ተመዝግበው መምሪያው አገልግሎታቸውን አምኖበት በጽሑፍ ሲፈቅድላቸው ብቻ በሚመድባቸው ቦታ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔን አክብረው የቤተክርስቲያናችንን ዶግማና ቀኖና ጠብቀው እንዲያገለግሉ እንጂ ያለፈቃድ እየተዘዋወሩ መዋቅርን ባልጠበቀ አሠራር የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን እንዳይሰጡ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ፤
3.በውጭ ሀገር በተለያዩ አቅጣጫ የሚያገለግሉ ሰባክያነ ወንጌል ወደ ሀገር ቤት ሲገቡ በሚኖሩበት ሀገር በቅድስት ቤተክርስቲያናችን መዋቅር ሥር እናት ቤተ ክርስቲያንን ሲያገለግሉ መቆየታቸውን የሚያረጋግጥ ደብዳቤ ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ይዘው ካልመጡ በቀር ሳይፈቀድላቸው ከሀገር ሀገር እየተዘዋወሩ በየአጥቢያ ቤተክርስቲያን እየተገኙ እንዳያስተምሩ የማስተማሪያ መድረክም በየትኛውም ቦታ እንዳይሰጥ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ፤
4.ከሀገር ውስጥ ወደ ማንኛውም የውጭ ሀገር የሚወጡ ሰባክያነ ወንጌል ከስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በሚቀርበው አስተያየት መሠረት ከቤተክርስቲያኒቱ የውጭ ግንኙነት ጽ/ቤት ደብዳቤ ይዘው ካልወጡ በቀር በውጭ ሀገር በሚገኙ የቤተክርስቲያናችን አህጉረ ስብከት ጽ/ቤቶች ሥር በሚገኙ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እንዳያገለግሉ የየአህጉረ ስብከቱ ጽ/ቤት ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደርጉና እንዲያሳውቁ፤
5.መምህራነ ወንጌልን የመመደብ መብት በአንድ ሀገረ ስብከት ውስጥ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ሲሆን፣ ሀገረ ስብከቱ ተስማምቶ ሲጠይቅ ደግሞ ከማእከል የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤ/ክ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ስለሆኑ ከዚህ ውጭ በሚጻፉ ደብዳቤዎች ወይም ደብዳቤ ሳይይዙ በየአጥቢያ ቤተክርስቲያን እየተዘዋወሩ ማስተማር መዋቅርን ያልጠበቀ ከመሆኑ የተነሣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት የጎደለው ስለሆነ ጥብቅ ክትትል እንዲደረግበትና አስተዳደራዊ ርምጃም እንዲወሰድ፤
6.የተፈቀደላቸው ሰባክያነ ወንጌል ቢሆኑም የሕዝቡን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ሕይወት የሚያንጽ ትምህርተ ወንጌልን ከማስተማር ውጭ በቤተክርስቲያን መድረክ ላይ የግል ፍላጎታቸውን በማስተጋባት፣ ሕዝቡን ወደ አልሆነ አቅጣጫ የሚያነሳሳ ንግግርን እንዳያደርጉና በሃይማኖት ነፃነት ስም የፖለቲካ አሰባቸውን እንዳያስተላልፉ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ፤
7.ከአጥቢያ ቤተክርስቲያን፣ ከወረዳ ቤተ ክህነት፣ ከሀገረ ስብከት ጽ/ቤትና ከጠቅላይ ቤተክህነት ውጭ በስብከተ ወንጌል ስም በግልና በቡድን በነጭ ወረቀት ገንዘብ ማሰባሰብ በቃለ ዓዋዲውም ሆነ በስብከተ ወንጌል ማስፋፊያና ማጠናከሪያ ጉባኤ ደንብ የተከለከለ ስለሆነ ክትትልና ቁጥጥር ተደርጎ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ይህን መመሪያ ማስተላለፍ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ስለዚህ ሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አህጉረ ስብከት፣ ወረዳ ቤተ ክህነትና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት መመሪያውን ተከታትለው እንዲያስፈጽሙ በሚል ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት መመሪያው ተላልፎ በተላለፈው መመሪያ መሠረት እንዲያስፈጽሙ ለአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በተደጋጋሚ ጊዜ መመሪያው የተላለፈ ቢሆንም በአንዳንድ አድባራትና ገዳማት ግን መመሪያው ባለመፈፀሙ ችግሮች እየተከሰቱ እንደሆነ ተደርሶበታል፡፡
ስለሆነም ይህ መመሪያ በድጋሜ ከተላለፈበት ጊዜ ጀምሮ ከመደበኛ ሰባክያነ ወንጌል ውጭ በማዕከል ተፈቅዶ በሀገረ ስብከቱ በኩል ተረጋግጦ ካልሆነ በስተቀር ፈቃድ የሌላቸው ሰባክያነ ወንጌል በየትኛውም አድባራት እና ገዳማት እንዳያገለግሉ የተከለከለ መሆኑን አውቃችሁ በተጨማሪም በሕግ አግባብ በሚመለከተው አካል እንዲያስተምሩ የተፈቀደላቸው ሰባክነያነ ወንጌል ቢሆኑም ለስብከተወንጌል በሚጋበዙበት ወቅት የሚያስተምሩበት ርዕሰ ጉዳይ እና ሕዝበ ክርስቲያኑ እንዲማር የተፈለገው ዓላማና ግብ ተቀምጦለት ከጉባኤ በኋላ የተሰጠው ትምህርት ርዕሱን የጠበቀና ዓላማውን ያሣካ ስለመሆኑ እየተገመገመ በየቀኑ በስብከተወንጌል ክፍል እንዲቀመጥና በየሦስት ወሩ ለሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ዋና ክፍል እንዲቀርብ እያስገነዘብን ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን መመሪያውን ለማስፈፀም ሲባልና የቤተክርስቲያኒቷን ደህንነት ለመጠበቅ እንዲቻል ይህንን በማያስፈፅሙ አካላት ላይ አስፈላጊውን የሥነ ሥርዓት እርምጃ ለመውሰድ የምንገደድ በጥብቅ እየገለፅን የክፍለ ከተማ ቤ/ክ/ጽ/ቤትም ክትትል በማድረግ መመሪያውን እንዲያስፈፅሙ በዚህ ደብዳቤ ግልባጭ የታዘዙ መሆኑን እናስታውቃለን፡፡

                                                                                                      ከመንፈሳዊ ሰላምታ ጋር

 

{flike}{plusone}