ጾም በክርስትና ሕይወት
የጾም ትርጉም
ጾም፡-ማለት ክርስቲያን የሆነ ሰው ሁሉ ለተወሰነ ጊዜና ሰዓት ከጥሉላት ከሥጋ፣ከቅቤ፣ከእህል ከውኃ ተከልክሎ መቆየት ነው፡፡
ከዚህም ሌላ ጾም ማለት፡- ዓይን ክፉ ከማየት ጆሮ ክፉ ከመስማት፣አንደበትክፉ ከመናገር፣እጅ ክፉ ከመሥራት በአጠቃላይ ሰውነት የኃጢአትሥራ ከመሥራት የሚገታበት፣ የሚከለከልበት ማለት ነው፡፡
ጾም፡- ሁለት ዓይነት ነው ይኸውም
ሀ.የግል ጾም ነው ፡-የግል ጾም ስንል አንድ ሰው በሠራው ኃጢአት ምክንያት ለንስሐ አባቱ ተናግሮ የሚሰጠው የንስሐ ጾም ሲሆን እንዲሁም አንድ ሰው ስለደረሰበትና በእርሱ ላይ ስለሆነ ነገር ስለሚፈልገው ጉዳይ እግዚአብሔር ተገቢውን መልስ እንዲሰጠው የሚጾመው ጾም ነው፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ዳዊት
የልጁን መታመም በሰማ ጊዜ ጾሟል፡፡ /2ኛ.ሳሙ.12፡16/
ነገር ግን በግል ጾም ጊዜ ጾሙ ይፋ ስላልሆነ ራስን መሰወር እንደሚያስፈልግ ታዟል፡፡
ይህንንም አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ሲል ተናሯል፡፡ ‹‹ስትጾሙም እንደ ግብዞች አትጠውልጉ ለሰዎች ሊታዩ እንደ ጾመኛ ፊታቸውን ያጠወልጋሉና አንተ ግን ስትጾም ለሰዎች እንዳትታይ ራስህን ተቀባ በስውር የሚያይህ አባትህ በግልጥ ይከፍልሃል›› /ማቴ.6፡16-18/ ይህ ቅዱስ ቃል ስለግል ጾም የተነገረ ነው፡፡ በዚህ መሠረት የግል ጾምን ከጿሚው ሰው እና ከእግዚአብሔር ውጭ ማንም ማወቅ የለበትም፡፡
ለ. የአዋጅ ጾም ነው፡- ይህም በስውር ሳይሆን ሁሉ አውቆት ክርስቲያን የሆነ ሁሉ የሚጾመው ጾም ነው፡፡ ይህም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት አለው፡፡ ‹‹በጽዮን መለከትን ንፉ ጾምንም ቀድሱ ጉባኤውንም አውጁ›› /ኢዩ.2፡15/ይህም ከአሕዛብ ተለይተን የምንታይበት የልዑል እግዚአብሔር ቤተሰቦች መሆናችን ተለይተን የሚታወቅበት ነው፡፡
ሰባቱ አጽዋማት የአዋጅ ጾሞች ናቸው፡፡ እነዚህም እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል
1.የነቢያት ጾም 2.የገሀድ ጾም 3.የነነዌ ጾም 4.ዐቢይ ጾም 5.የሐዋርያት ጾም 6.ጾመ ድኅነት (ረቡዕና ዓርብ) 7.ጾመ ፍልሰታ
ጾም ያስፈለገበት ምከንያት
ጾም፡-ያስፈለገበት ምክንያት ልጓመ ሥጋ ስለሆነ ነው፡፡ ሰው ሁልጊዜ የጣመ የላመ ምግብ የማይለየውና እንደ ልቡ እየበላ እየጠጣ ሳይጾም የሚኖር ከሆነ ለኃጢአት ይጋለጣል፡፡ ይህም በፍትሐ ነገሥት ተጽፏል፡፡ ‹‹ከመ ያድክም ኃይለ ፍትወት›› (ኃይለ ፍትወትን፣ሥጋዊ ፍትወትን ያደክም ዘንድ) ጾም ታዘዘ /ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15/ እንዲሁም በምንጾምበት ጊዜ ረሀብን ችግርን እናውቃለን፡፡ ‹‹ከመ ያእምር ደዋሚ ሕማም ረሀብ ወይምሐሮሙ ለርኁባን›› (ጿሚ ሰው የረኀብን ችግር ያውቅ ዘንድና ለተራቡ ይራራ ዘንድ) ጾም ታዘዘ፡፡ /ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 /ችግርን የቀመሰ ችግርን ያውቃል›› እንዲሉ አባቶቻችን
3ኛ. የጾም ጥቅሞች
የጾም ጥቅሞች እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል
1.በጾም መንግሥተ ሰማያትን እንወርሳለን፡፡ይህንንም የሰላም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ስለጽድቅ ብለው የሚራቡና የሚጠሙ ንዑዳን ክቡራን ናቸው እነርሱ ይጠግባሉና›› /ማቴ 5፡6/ ሲል ተናግሯል፡፡
2.በጾም በአገር ላይ የታዘዘው መቅሠፍት ይርቃል፡-፡፡ የነነዌ ሰዎች የዮናስን ትምህርት መሠረት በማድረግ ሦስት ቀን ጾሙ፡፡ ለእነርሱ የታዘዘው እሳት የዛፉን ጫፍ ጫፍ አቃጥሎ ተመልሷል፡፡ /ትን ዮናስ 3 በሙሉ/
3.በጾም ሰይጣን ድል ይሆናል፡፡‹‹እንዲህ ዓይነት አብሮ አደግ ጋኔን ያለ ጾምና ጸሎት አይወጣም›› /ማቴ.17፤21/ ሲል ጌታችን በቅዱስ ወንጌል የተናገረው ቃል ሰይጣን በጾም ድል እንደሚሆን የሚገልጽ ነው፡፡
4ኛ.ጾም ከፈተና፣ከመከራ ያድናል
ነቢዩ ዳንኤል በጾም ከአፈ አናብስት (ከአንበሶች አፍ) ድኗል፡፡ /ትን ዳን.6 በሙሉ/ ሶስና በጾም ከሐሰት ምስክሮች ድናለች፡፡ /መጽ ሶስና 1/በሙሉ ሌሎችም ቅዱሳን በጾም ከፈተና፣ከመከራ ድነዋል፡፡
5.ጾም እድሜን ያረዝማል፡፡ ጾም የመልካም ሥራ ሁሉ መሠረት በመሆኑ እድሜን ያረዝማል፡፡
ታላቁ ጻድቅ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በገድላቸው እንደተጻፈው እድሜ ልካቸውን በጾም ነው የኖሩት የእናታቸውን ጡት እንኳን አልጠቡም፡፡ በዚህ ዓለም የኖሩት አምስት መቶ ስልሳ ሁለት ዓመት ነው፡፡ ሌሎችም ቅዱሳን በጾም የእድሜ ባላጸጎች ሆነዋል፡፡
6.በጾም ምስጢር ይገለጻል፡፡ አይሁድ አርባ ስድስቱን መጻሕፍተ ብሉያት ቆነጻጽለው ባጠፏቸው ጊዜ ዕዝራ ሱቱኤል አዝኖ አርባ ቀን ጾመ ከዚህ በኋላ ታላቁ መልአክ ቅዱስ ዑራኤል ሰማያዊ መጠጥ በብርሃን ጽዋዓ (ጽዋዓ እሳት) ለዕዝራ አጠጣው ዕዝራም ምስጢር ተገልጾለት አርባ ስድስቱን መጻሕፍተ ብሉያት ጽፏል፡፡ /መጽ ዕዝ.ሱቱ 13፤36-41/ ሌሎችም ደጋግ ሰዎች በጾም ምስጢር ተገልጾላቸዋል፡፡
7.በጾም ኃጢአት ይሠረያል፡፡የነነዌ ሰዎች የዮናስን ትምህርት መሠረት በማድረግ ሦስት ቀን ጾመው ኃጢአታቸው ተሠርዮላቸዋል፡፡ /ትን. ዮና 3 በሙሉ/ ሌሎችም ሰዎች በጾም ኃጢአታቸው ተሠርዮላቸዋል ይህንንም ታላቁ ሊቅ ማኅቶተ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ያሬድ በዜማ ድርሰቱ እንዲህ ሲል ተናግሯል፡፡ ‹‹በጾም ወበጸሎት ይሠረይ ኃጢአት›› (በጾምና በጸሎት ኃጢአት ይሠረያል) ሌሎችም ሰዎች በጾም ኃጢአታቸው ተሠርዮላቸዋል፡፡
8.በጾም ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ይቻላል፡፡ሊቀ ነቢያት ሙሴ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾሞ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ለቃል ተነጋግሯል፡፡ /ዘዳግም 9፤9-14/
ነቢዩ ኤልያስም በጾም ከእግዚአብሔር ጋር ተነጋግሯል፡፡ /1ኛ.መጽ.ነገ.17፤2/
9. በጾም ልመናችን ይፈጸማል፡፡እስራኤል በጾም የለመኑትን አግኝተዋል፡፡/2ኛ ሳሙ.12፡7-14/ ሌሎችም ቅዱሳን በጾም ልመናቸው ተፈጽሞላቸዋል፡፡
የጾም ጥቅሞች ከላይ ከ1-9 ተራ ቁጥር የተገለጹ ሲሆን ከላይ በርዕሱ እንደተገለጸው ጾም የመልካም ሥራ ሁሉ መሠረት ሲሆን በአንጻሩ አለመጾም ደግሞ የኃጢአት ሁሉ መሠረት ነው፡፡ለመጀመሪያ ጊዜ ለሰዎች የተሰጠው የጾም ትእዛዝ ነው፡፡ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር አዳምና ሔዋንን፡- ይህን ዕፀ በለስ አትብሉ ማለቱ ከዕፀ በለሱ ተከልከሉ ጹሙ ማለቱ ነው እነርሱ ግን አትብሉ የተባሉትን በሉ ከገነት ወጡ ተጎዱ አለመጾም ያስጎዳል፡፡ በዚህ መሠረት ኃጢአት በመብል ምክንያት ወደዓለም ገባ፡፡
በምን ዓይነት መንገድ መጾም እንዳለብን
ጾም ፡- ከትርጉሙ እንደተረዳነው ከእህል ከውኃ ከመከልከሉ ጋር ከክፉ ነገር ከኃጢአት መራቅ ስለሆነ ጾማችን ከክፉ ነገር በመራቅ፣በቅን ልቡና፣ በንጹሕ ልብ መሆን አለበት፡፡
እንዲሁም ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹በምትጾሙበት ጊዜ እንጀራህን ለተራበ ብትቆርስ ብርሃንህ እንደንጋት ይበራል የዚያን ጊዜ ትጠራለህ እግዚአብሔርም ይሰማሃል ትጮሀለህ እርሱም እነሆኝ ይላል›› /ኢሳ.58፡6-9/ ባለው መሠረት በጾም ጊዜ የጧት ቁርሳችን ለድሆች ከተሰጠ ሰማያዊ ዋጋ እናገኛለን፡፡ስለዚህ ጾማችን ከምጽዋት ጋር መሆን አለበት፣ ጾም፣ጸሎት፣ምጽዋት አይለያዩምና እነዚህን ገንዘብ እናድርግ፡፡በረከተ ሥጋ፣በረከተ ነፍስ እንድናገኝ ጾማችን በቅንነትና በንጹህ ልቡና ይሁን ጾማችን ከምጽዋትጋር ይሁን፡፡ለዚህም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንዲሁም ቅዱሳን በአማላጅነታቸው ይርዱን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
(ላዕከ ወንጌል በእደማርያም ይትባረክ (ቀሲስ) የአ/አ/ሀ/ስ/የስ/ወ/ትምህርት ስርጭት ኃላፊ)