ጾመ ፍልሰታ

                                                                               በሚዲያ ክፍል

ጾም ምንድነው?

ጾም ማለት ሰውነት ከሚፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ ለአንድ የተወሰነ ጊዜ መተው ወይም መከልከልና መቆጠብ  ማለት ሲሆን የእግዚአብሔር መንግሥት ዜጎች ከእግዚአብሔር ጋር ከሚገናኙባቸው የግንኑነት መስመሮች መካከል አንዱ ነው፡፡የሰው ልጅ ግንኙነቱ የሠመረና በበረከት የተሞላ ደግሞም ለንስሐ የሚያበቃ ሕይወት ይኖረው ዘንድ በማቴ 6÷1-19 የተቀመጡለትን የግንኙነት መስመሮች በአግባቡ መተግበርና በሕይወቱ መተርጎም አለበት፡፡

እነዚህም የግንኙነት መስመሮች ስትመጸውቱ ፤ስትጸልዩ እና ስትጦሙም በማለት ከአሁን በፊት አይሁዳውያን ያደርጉት እንደነበር  ከጠቆመ በኋላ በክርስቲኖች ዘንድ ግን የድርጊት ማስተካከያና አቅጣጫ የሚያስፈልገው በመሆኑ ²እናንተ ግን² በሚል አባታዊ መመሪያ ተስተካክሎ እናገኘዋለን፡፡ ጾም ፤ጸሎትና ምጽዋት የሸፈተውን የሰውን ልብ ወደ መጸጸትና ንስሐ የሚያመጡ ብርቱ መንፈሳዊ መሣሪያዎች ናቸው፡፡ ጾም ያለ ጸሎትና ምጽዋት የረሃብ አድማ እንደሚመስል ሁሉ ጸሎትም ያለ ጾምና ራስን መግዛት ትርፉ    ውጤት አልባ ጩኸት መሆኑ ውስጣችን የሚቀበለው ሐቅ ነው፡፡

ጾም የሥጋ ፈቃድ የምናደርግበት፤ ሠራተኞቻችንን የምናስጨንቅበት፤የግፍ ጡጫ የማንማታበትና ለጥልና ክርክር የምንቆምበት ሳይሆን የበደል እስራት የምንፈታበት ፤የተገፉትን አርነት የምናወጣበት ፤የጭቆና ቀንበሩን የምንስብርበት ፤እንጀራን ለተራበ ቆርስን የምናበላበትና የተራቆተውን የምናለብስበት መሆን እንዳለበት እግዚአብሔር በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል ከነገረን በኋላ አምላካዊ መልሱንም ብርሃንህ እንደንጋት ኮከብ ይበራል፤ ጽድቅህም በፊትህ ይሔዳል በማለት ያስቀምጣል፡፡ (ኢሳ 58÷1-13)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ  ተዋሕዶ  ቤተክርስቲያን ከአሐት አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ እንደመሆኗ መጠን የተመሠረተችበት መሠረተ እምነት፤የተለያዩ  ውሳኔዎችንና ሥርዓቶችን ያሳለፈችበትና የደነገገችበት ቀኖና እንዲሁም ከቀደሙት አባቶች የተረከበችው መንፈሳዊ ትውፊቷ  ምልከታዋን የሚያሰፉ  የማንነት መነጽሮቿ ናቸው፡፡

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚሰጡ መንፈሳዊ አገልግሎቶች ተደራሽነታቸውን ለማስፋትና የአማንያኑን መንፈሳዊ ሕይወት ለመገንባት በዓላትንና አጽዋማትን አስመርኩዞ ዘመኑን የሚዋጅና ወቅቱንም የሚዘክር አስተምህሮ በማዘጋጀት፤ተከታዮቿንም በመመገብና በመጠበቅ እነሆ ሽህ ዓመታትን አስቆጥራለች፤አሁንም በማገልገል ላይ ትገኛለች፡፡

በሥርዓተ እምነቷ አካታና በአዋጅ አስነግራ ከምትጾማቸው ከሰባቱ አጽዋማት መካከል አንዱ የሆነውና በወርሐ ክረምት ወቅት የሚታሰበው ጾመ-ፍልሰታ  ሲሆን ራስን ለመግዛትና ለማስተካከል በሚመች መልኩ በሁለት ሱባኤያት ተከፍሎ የሚጾምና የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን የቅድስና፤ የንጽህናና የመሰጠት ሕይወት ምን ይመስል እንድነበር እንዲሁም ዜና ዕረፍተ ሥጋዋ እንዴት እንደነበር የምንዘክርበት ወሳኝ ወቅት ነው፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መለኮታዊ ጥሪው ከደረሳት ጊዜና ወቅት ጀምሮ ለአምላካዊ ጥሪው እንጅ ለራሷ ያልኖረች የሐዲስ ኪዳን የእምነት አርበኛ ናት፡፡ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ የሚለውን አምላካዊ ቃል (ፊሊጵ 1÷27) በአንደበት ብቻ ሳይሆን በሕይወት ካሳዩን ቅዱሳን መካከል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዋንኛና ፋና ወጊ እንደነበረች ቅዱሱ መጽሐፍ ምስክርነቱን ያስቀምጣል፡፡

2.ጸሎት

                      ጸሎት ምንድነው?

በክርስትና ሕይወት ውስጥ ጸሎት እጅግ ታላቅ ሥፍራ አለው፡፡ክርስትና ሕይወት በመሆኑ ምክንያት ጸሎት ለክርስቲያን እስትንፋሱ ነው፡፡በባሕር ውስጥ ያለ ዓሳ ከባሕሩ ሲወጣ ወዲያው እንደሚሞት ሁሉ አንድ ክርስትያንም ከጸሎት ሕይወት ከተለየ ጉዞው ወደ መንፈሳዊ ሞት ያመራ ይሆናል፡፡ ጸሎት ሰው ከፈጣሪው ጋር የሚነጋገርበት መንፈሳዊ መሣሪያ ነው፡፡

ሰው በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ በመፈጠሩ ምክንያት ሁልጊዜም ከአምላኩ ጋር በጸሎት መነጋገር አለበት፡፡ ጸሎት ፍጡር የሆነው ሰው ሁሉን ቻይ ከሆነው ከፈጣሪው እገዛ የሚያገኝበት መንገድ ነው፡፡ጸሎት በእግዚአብሔርና በልጆቹ መካከል የሚደረግ የሁለትዮሽ ንግግር ነው፡፡ሰው ይጸልያል እግዚአብሔር ደግሞ መልስ ይሰጣል፡፡ ጸሎት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትእዛዝ ስለሆነ ሁላችንም የጸሎትን ትርጉምና ምንነት አውቀንና ተረድተን በጸሎት ልንበረታ ያስፈልጋል፡፡ “በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ” (ኤፌ 6÷18)፡፡

የጸሎት አስፈላጊነት

ጸሎት ለሕይወታችን እጅግ አስፈላጊ ስለሆነ እኛ ክርስቲያኖች በተለያየ ምክንያት እንጸልያለን፡፡ከእነዚህም ምክንያቶች መካከል የተወሰኑትን እንመልከት፡፡

እግዚአብሔርን ለማመስገን እንጸልያለን “ከማመስገን ጋር በጸሎት እየነቃችሁ ለእርሱ ትጉ” (ቆላ 4÷2)፡፡ የጸሎታችን የመጀመሪያው ክፍል ምስጋና መሆን አለበት፡፡ምክንያቱም የተደረገልን ነገር ካልተደረገልን ነገር ይበልጣልና፡፡ አባታችን እግዚአብሔር አብ አንድያ ልጁን ለእኛ አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ  ተሰቅሎ ሞቶ በሦስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ ተነሥቶ እኛን ስላዳነን እንዲሁም በደም ዋጋ የተገዛን መሆናችንን አምነን ስለተከፈለልን ውድ ስጦታ ሳንታክት በጸሎት ልናመሰግን ያስፈልጋል፡፡

ሰይጣንን ለመቃወም እንጸልያለን “በመጠን ኑሩ ንቁም ባላጋራችሁ ዲያቢሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት” (1ጴጥ 5÷ 8—9)፡፡ ሰይጣን የክፋት ሁሉ ምንጭና የሐሰት አባት ስለሆነ ሁልጊዜም ያመኑትን ለማሳሳትና በኃጢአት ለመጣል አያንቀላፋም፡፡ይህን የሰይጣን ክፋትና ተንኮል ወደ ልባችን እንዳይገባ የምንከላከልበት ትልቁ መንፈሳዊ መሣሪያችን ጸሎት ነው፡፡

ከእግዚአብሔር መፍትሔ ለማግኘት እንጸልያለን “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ነገር ግን አይዞአችሁ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” (ዮሐ 16÷33) ተብሎ እንደተጠቀሰው በዚች ጊዜያዊ ምድር ስንኖር የተለያዩ ፈተናዎች ወደ ሕይወታችን ይመጣሉ፡፡ውሳኔ መወሰን እስኪያቅተን ድረስ ያስጨንቁናል፡፡ በዚህ ወቅት መፍትሔው መጨነቅ ሳይሆን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መጸለይ ነው እርሱ ዓለምን አሸንፏልና፡፡ መድኃኔዓለም ለችግሮቻችን ሁሉ መፈትሔ ይሰጣል፡፡

እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ይቅር እንዲለን እንጸልያለን “የእምነትም ጸሎት ድወዩን ያድናል ጌታም ያስነሣዋል ኃጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል” (ያዕ 5÷15)፡፡ ሰዎች እንደመሆናችን መጠን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በማሰብ በመናገር በማድረግ ኃጢአት እንሠራለን፡፡ ኃጢአት እኛን ከእግዚአብሔር የሚለይ ግድግዳ በመሆኑ ምክንያት ከእግዚአብሔር እንዳንለይ ቶሎ ብለን ኃጢአታችንን ይቅር በለን በማለት ወደ አምላካችን መጸለይ ያስፈልጋል፡፡

                  ጸሎታችን ምን መሆን አለበት

ማንኛውም ድርጊት የራሱ የሆነ ሥርዓትና ደንብ አለው፡፡ ጸሎት በምንጸልይበት ጊዜ ማስታወስ ያለብን ነገሮች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

በእምነት መጸለይ “እምነት ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው” (ዕብ 11÷1) ተብሎ እንደተጠቀሰው ስንጸልይ በእምነት ተሞልተን መሆን አለበት፡፡

እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ መጸለይ ስለማንኛውም ጉዳይ ስንጸልይ ጌታ ሆይ የአንተ ፍቃድ ይሁን በማለት እርሱ አምላካችን የፈቀደው ነገር እንዲሆን መጸለይ አለብን፡፡

ንስሐ በመግባት መጸለይ ጸሎታችን እንደ ፈሪሳዊው ሰው ራስን ከፍ ከፍ በማድረግና ሌሎችን በመኮነን ሳይሆን  ራሱን ዝቅ አድርጎ “አምላኬ ሆይ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ” (ሉቃ18÷13) እንዳለው እንደ ቀራጩ አይነት ጸሎት መሆን አለበት፡፡

አእምሮን በመሰብሰብ መጸለይ ሌላው በጸሎት ጊዜ ትልቅ ትኩረት ልንሰጠው የሚያስፈልገው ጉዳይ ቢኖር አእምሮን በመሰብሰብ መጸለይ ነው፡፡ ለጸሎት እግዚአብሔር ፊት በምንቆምበት ጊዜ ሁለንተናችንን ለእርሱ ለአምላካችን በመስጠት በአንድ ሐሳብ ወደ እርሱ መጸለይ ይኖርብናል፡፡

ይቅር ባይ በመሆን መጸለይ “ለጸሎት በቆማችሁ ጊዜ በሰማያት ያለው አባታችሁ ደግሞ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ በማንም ላይ አንዳች ቢኖርባችሁ ይቅር በሉ” (ማር 11÷25) ስለሚል ይቅር ባዮች መሆን አለብን፡፡

ለሌሎች መጸለይ ክርስትና ራስን ብቻ ይዞ መሮጥ ሳይሆን ሌሎችንም ማሰብ ስለሆነ በችግር በሥቃይና በመከራ ውስጥ ላሉት መጸለይ ያስፈልጋል፡፡

  1. ንስሐ

                   ተመለሱ በሕይወትም ኑሩ (ሕዝ 18፡32)

ንስሐ ማለት መጸጸት፣ መመለስና መለወጥ ማለት ነው። ስላለፈው ስሕተታችን ተገቢ ያልሆነ አካሄዳችን ወይም ያደረግነውን በደል በሰከነና በተረጋጋ መንፈስ በሙሉ ልብ ተረድተን ተገንዝበን፣ በግዴታ ሳይሆን በውዴታ በራሳችን ስሕተታችንን በልቡናችን ተቀብለን፣ ከፈጣሪያችን ይቅርታን በመጠየቅ፣ የነበረውን የተሳሳተ ሕይወታችን ትተን፣ አዲስ መንፈሳዊ ሕይወት ለመጀመር ቆርጠን መነሣት ማለት ነው። ከተመልስን ደግሞ  እግዚአብሔር ይቅር እንደሚለን ቃል ገብቶልናልና።                  

እግዚአብሔር ኃጢአተኛ ከኃጠአቱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ከነኃጢአቱ ይሞት ዘንድ አይፈቅድምና።  ጻድቁ  ከጽድቁ ሲመለስ ኃጢአት እንደሚሆንበት ሁሉ፣ ኃጢአተኛውም  ከኃጢአቱ ተመልሶ ቢጸጸት ጽድቅ ይሆንለታል። ይህ ቃል የነፍሳት ሁሉ ባለቤት ቃል ነው።

እነሆ፥ ነፍሳት ሁሉ የእኔ ናቸው ይላል እግዚአብሔር ፡፡ የአባት ነፍስ የእኔ እንደ ሆነች ደግሞ የልጅ ነፍስ የእኔ ናት። ከቃሌ ውጭ የሚመላለስ ሰው በሕይወት አይኖርም ፈጽሞ ይሞታል። ኃጢአተኛውም ካደረጋት ኃጢአት ሁሉ ቢመለስ ትእዛዜንም ሁሉ ቢጠብቅ  እርሱ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል። ። የበደለው በደል ሁሉ አይታሰብበትም፤ በሠራው ጽድቅ በሕይወት ይኖራል። አስቦ ከሠራው በደል ሁሉ ተመልሶአልና ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም ። ንስሐ ግቡ ኃጢአትም ዕንቅፋት እንዳይሆንባችሁ ከኃጢአታችሁ ሁሉ ተመለሱ። የበደላችሁትን በደል ሁሉ ከእናንተ ጣሉ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስም ለእናንተ አድርጉ፤  የምዋቹን ሞት አልፈቅድምና ተመለሱ በሕይወትም ኑሩ ይላል ጌታ እግዚአብሔር (ሕዝ 18)

እውነተኛ ንስሐ በእምነት፣ በተስፋና በፍቅር በመጽናት ከእግዚአብሔር ምሕረት በመለመን፣አዲስ ልብና አዲስ መንፈስም  በመልበስ  መጪውን ሕይወት ማስተካከልን ይመለከታል። ለምሳሌ÷ፍጡራን ሆነን ፈጣሪያችንን ሳናውቅ ከቆየን ፈጣሪያችንን  ማወቅ፣ በኃጢአት ሥር ወድቀን ቆይተን ከሆነም ከኃጢአት እንቅልፍ ነቅተን የዓለምን ኃጢአት ለማስወገድ በተላከ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነን በደሙ ታጥበን በመንጻት ላዳነን ስለ ታላቅ ይቅርታው ማመስገን፣ እስካሁን አለማመናችንንም ይቅርታ ጠይቀን ለወደፊቱ እንዳይደገም ከልብ በመነጨ መልኩ ቃል መግባትና በፍጹም እምነት ተከታይና ታዛዥ መሆን፣ ከእግዚአብሔር መታረቅ፣ ከዓለማዊ ምኞትና መቅበዝበዝ ወደ መንፈሳዊ ሕይወት መመለስ፣ ከኃጢአትና ከሰይጣን ባርነት ወጥተን ወደ እረኛችንና አምባችን  መጠጋትና መግባት፣ በጸጋው ተደግፈን ወደ ቅድስና መግባት፣ በስሜት ሳይሆን በእምነትና በተስፋ አምላካችን መከተል፣ የጠራን ፍጹም እንደኾነ በፍቅሩ ተማርከን በጸጋው ተሸፍነን ወደ ፍጹምነት ለመድረስ ቆርጠን መነሣት፣ ከኃጢአት ጎዳና ወጥተን ወደ ጽድቅ ጎዳና ማምራት፣ ከጥርጥርና ስንፍና ወጥተን በፍጹም ልቡናችን፣ አእምሮአችን፣ ሐሳባችን፣ አምላካችንን፣ አዳኛችንን፣ መድኃኒታችንን መውደድ፣ መገዛት፣ መከተልና ማምለክ ነው።

ንስሐ መግባት የመዳን መጀመሪያ እርምጃ ነው፣ ከእምነትም ጋር የተያያዘ ነው።ንስሐ ወደ ይቅርታ ነው የሚመራን፤ ይቅርታ ከሌለ መታረቅ የለም፤ እግዚአብሔር ይቅር ባይለን ከእርሱ ጋር ባልታረቅን ነበር፣ ድኅነታችንን ያገኘነው እግዚአብሔር ይቅር ስላለን ነው፤እግዚአብሔር ይቅር ባይ ነውና ።

ስለ ኃጢአታችን ብንጸጸትና ንስሓ ብንገባ ይቅርም ብንል እግዚአብሔር ይቅር ይለናል። ነገር ግን አሁን ያገኘነው መሠረታዊ  ደኅንነት እግዚአብሔር በክርስቶስ ሞት መሠረት ይቅር ስላለን ነው። እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል ይቅርታችንን ስለተቀበለ ነው ያዳነን፡፡

ልብ እንበል ከበደላችን ክብደትና ብዛት የተነሣ የእኛ ይቅርታ ዘለዓለማዊ ደኅንነት ሊያመጣ አልቻለም ነበር፣ ጌታችን ግን እርሱ ራሱ መስዋዕትና የመስዋዕቱ አቅራቢ በመሆን የሁላችንን ኃጢአት ተሸክሞ መስቀል ላይ በመውጣት ይቅርታችንን አቀረበልን፣ እግዚአብሔርም ይቅር አለን፤ ዘለዓለማዊ ድኅነትም አገኘን። አሁን ግን እግዚአብሔር ይቅር እንዳለን ወይም እግዚአብሔር በክርስቶስ ይቅር እንዳለን ይቅር ባዮችና እርስ በርሳችን ይቅር እንድንባባል ታዝዘናል (ኤፌ 4÷32፣ ቆላ 3÷13)፣ ይህንን ባናደርግ ግን የእግዚአብሔር ሥራ አልተረዳንም  ይቅርታም አናገኝም ማለት ነው (ማቴ 6÷12-15፣18÷23-35)።

ወገኖቼ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅሩና ይቅርታው ገብቶን ከሆነ በመጀመሪያ እግዚአብሔር አብ በልጁ  ስለ ወደደንና ስላደረገልን ይቅርታ፣ እንዲሁም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ብሎ የተቀበለውን ስደት፣ መከራ፣ ሥቃይ፣ ግርፋት፣ መስቀል፣ በሞቱ ሞታችን ደምስሶ ሕይወታችን የሆነልን በታላቅ ፍቅሩና ይቅርታው  መሆኑንን ተረድተን አምነን ቃሉ በማክበር እርሱን ዘወትር እያመሰገን፣ ለሌሎች  ይቅርታ በማድረግና በመዋደድ በሰላምና በፍቅር እንኑር፣ እግዚአብሔርንም ከዚህ የሚበልጥ የሚያስደስተው አንዳች ነገር አይኖርምና።                          

4.ምጽዋት

ምጽዋት ማለት ለተቸገሩ አዝኖ መስጠት፣ ድሆችን በልግስና መርዳት ማለት ነው፡፡ (ዘዳ.15÷11) ኢየሱስ ክርስቶስ በሐዲስ ኪዳን ስለ ምጽዋት ሲያስተምር ለሰዎች ትታዩ ዘንድ ምጽዋታችሁን በፊታቸው እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ፡፡ ያለዚያ በሰማያት ባለው አባታችሁ ዘንድ ዋጋ የላችሁም፡፡ እንግዲህ ምጽዋት ስታደርግ ግብዞች በሰው ዘንድ ሊከበሩ በምኩራብ፣ በመንገድም እንደሚያደርጉ በፊትህ መለከት አታስነፉ፡፡ እውነት እላችኋለሁ ዋጋቸውን ተቀብለዋል፡፡ አንተ ግን ምጽዋት ስታደርግ ምጽዋትህ በስውር እንዲሆን ቀኝህ የምትሠራውን ግራህ አትወቅ፡፡ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጽ ይከፍልሃል፡፡ (ማቴ.6÷1-4) ምጽዋት ለበደል ማስወገጃ ይሆናል (ዳን.4÷27) ጌታችንና መድኃኔታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎች ይዩልን ብላችሁ መልካም ሥራችሁን በሰው ፊት ከማድረግ ተጠንቀቁ ብሎ አስተምሯል፡፡ ምንም አይነት ሥራ ብንሠራ እግዚአብሔር የሚመለከተው ሥራውን ሳይሆን ለመሥራት የተነሣንበትን ዓላማ ወይም ምክንያት ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ከሥራው ይልቅ ሥራውን ልንሠራ የተነሣንበት ምክንያት ትልቅ ዋጋ አለውና፡፡

ለራሳችን ምስጋና ለማግኘት አንድ ትልቅ ሥራ ብንሠራ እግዚአብሔር አይደሰትም፤ ይህ ራስ ወዳድነት ነውና፡፡ እግዚአብሔር የሚፈልገው ከልባችን ጻድቃን እንድንሆን ነው፤ ከጻድቅ ልብ የሚመነጩ መልካም ሥራዎች እግዚአብሔርን ያስደስቱታል፡፡ዋናው አሳብ ሰዎች የእኛን መልካም ሥራ አይተው በሰማይ ያለውን አባታችንን እንዲያከብሩ ነው (ማቴ.5÷16)

ከሰዎች ምስጋናን የምንፈልግ ከሆነ ሽልማታችን እርሱ ብቻ ይሆናል፡፡ በመንግሥተ ሰማይ ከእግዚአብሔር እጅ የምናገኘውን ሽልማት እናጣለን፤ የሰዎች ምስጋና አላፊና ጠፊ ነው፤ ከእግዚአብሔር የሚገኘው ሽልማት ግን ዘለዓለማዊ ነው፤ ሰው ዓለምን ቢያተርፍ ነፍሱንም  ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል? (ማቴ.16÷26)

ስለዚህ መልካም ሥራችንን በምንሠራበት ጊዜ ድምጻችንን አጥፍተን በድብቅ መሥራት አለብን፤ ለሌሎች ሰዎች መናገር የለብንም፤ ለራሳችንም እንኳ መናገር አይገባንም፤ ቀኝ  እጅ የሚወክለው ኩራታችንን ነው፤ ራስ ወዳድነታችንንም ያሳያል፤ በሌለ አነጋገር ግራ እጅ ሰዎች ስለሚሰጡት ስጦታ ወይም በጎ ተግባራ መቁጠር የለባቸውም ማለትን ሊያሳይ ይችላል፤እግዚአብሔር ከልባችን የሰጠነውን በማሰብ ሽልማት ይሰጠናል (ሉቃ.14÷13) (ቆላ.3÷23)

በሐዋርያት ዘመን በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ምዕመናን ሃብተቸውን ለድሆች ያካፍሉ ነበር (የሐሥ.4÷32) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በየአብያተ ክርስቲያናቱ እየዞረ ለድሆች ገንዘብ ይሰበስብ ነበር፤ የሚነግዱትንም ከሚያትርፉት ለድሆች እንዲሰጡ አስተምሯል (ሮሜ.15÷25) ላይ እንደተብራራው “አሁን ግን ቅዱሳንን ለማገልገል ወደ ኢየሩሳሌም እሄዳለሁ፤ መቄዶንያና አካይያ በኢየሩሳሌም ቅዱሳን መካከል ያሉትን ድሆች ይረዱ ዘንድ ወደዋልና፡፡” ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ (በ1ቆሮ.16÷1-4) አክሎ እንደገለጸው “ለቅዱሳን ገንዘብ ስለ ማዋጣት ለገላትያ አብያተ ክርስቲያናት እንደ ደነገግሁት እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ”ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን  ከሰጠው አደራ አንዱ ድሆችን መመገብ ነው፤

በሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስ ዘመነ ስብከት የደቀ መዘሙርት ቁጥር እየጨመረ በሄደበት ወቅት ከግሪክ የመጡ አይሁድ በይሁዳ ይኖሩ በነበሩት አይሁድ ላይ ያጉረመረሙ ነበር፤ ምክንያቱም በየዕለቱ በሚከናወነው ለመበለቶች ምግብ የማደል አሠራር ላይ ከእነርሱ ወገን የሆኑት መባለቶች ችላ ተብለው ነበር፡፡ ስለዚህ ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያትና ሌሎች ደቀ መዛሙርት በአንድነት ተሰብስበው እኛ የማዕዱን አገልግሎት ለማስተናገድ ስንል የእግዚአብሔርን ቃል አገልግሎት መተው አይገባንም፤ስለዚህ ወንድሞች ሆይ ከእናንተ መካከል በመንፈስ ቅዱስ እና በጥበብ የተሞሉ ለመሆናቸው የተመሠከረላቸውን ሰባት ሰዎች ምረጡ፤ ይህንንም የመመገብ አገልግሎት ለእነርሱ እንሰጣለን እኛ ግን በጸሎትና በቃሉ አግልግሎት እንተጋለን በማለት የቤተ ክርስቲያን ዋና የአገልግሎት ዘርፍ በሆነው ድሆችን የመመገብ ሥራ ብቻ ተወስነው አገልግሎት የሚሰጡ ሰባት የምግብ ኮሚቴዎች እንደተቋቋሙ እንረዳለን፡፡

ስለዚህ ከላይ በተብራራው መሠረት የምጽዋት አሰጣጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥርዓቱን ተከትለን ምጽዋታችንን ለድሆች ልንሰጥ ይገባናል፡፡