“ጻድቅ መሆን የክርስቲያን ሁሉ ግዴታ ነው” ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ

“ጻድቅ መሆን የክርስቲያን ሁሉ ግዴታ ነው” ሲሉ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ገለጹ።

ብፁዕነታቸው ይህንን ያሉት በቀን 12/09/2013 ዓ.ም በደብረ አሚን ተክለሃይማኖት ገዳም ተገኝተው የጻድቁን የአቡነ ተክለሃይማኖትን የፍልሰተ ዐፅሙን ክብረ በዓል ባከበሩበት ነው።

ጻድቅ ማለት እውነተኛ ማለት ነው፤ እውነት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ባሕርይ ነው፤ እርሱ እውነት ስለሆነ ርኩሰትንና ውሸትን ይጸየፋል በማለት ተናግረዋል።

ጻድቃንም መሠረታቸው ክርስቶስ ስለሆነ በእርሱ አምነው ከሥጋቸው፣ከሰይጣንና ከዚህ ዓለም የመጣባቸውን ፈተና በጸጋው ኃይል በመቋቋም ክርስትናን በእውነት ኖረው አሳይተውናል ሲሉ ገልጸዋል።

አክለውም ጻድቃን ኃላፊ ለሆነው ለምድራዊው ሀብት፣ሥልጣንና ክብር ብለው እግዚአብሔር የማይፈቅደውን ነገር አላደረጉም፤ በእግዚአብሔር ላይ ባላቸው እምነት ጸንተዋል፤ ከእነርሱ ፍላጎት ይልቅ የአምላካቸውን ፈቃድ ፈጽመዋል፤ ከልባቸው ክፉ ነገር እንዳይወጣ ተጠንቅቀዋል፤ ክፉን በክፉ አልተቃወሙም ፤ ለሰላምና ለፍቅር ዋጋ ሰጥተዋል፤ ለእውነት በመቆም ለእውነት ኖረዋል በማለት አብራርተዋል።

አያይዘውም ጻድቅ መሆን የክርስቲያን ሁሉ ግዴታ እንደሆነ አብራርተዋል። በዚህ ዘመን ለእግዚአብሔር አለመታዘዝ፣ርኩሰት፣ ክፋት፣ተንኮልና ውሸት ቢበዛም ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ግን እውነተኛ በመሆን በእግዚአብሔር ፊት መመላለስ አለበት ብለዋል።

ክርስቲያኖች የሆንን ሁሉ የጻድቃንን ክብረ በዓል ስናከብር እነርሱ ክርስቶስን በፍጹም ልባቸው እንዳመኑት ሁሉ እኛም በፍጹም ልባችን ክርስቶስን አምነን የእነርሱን የኑሯቸውን ፍሬ እየተመለከትንና በእምነታቸው እየመሰልናቸው ክርስትናን በሕይወት በመኖር እውነተኞች መሆን እንዳለብን ብፁዕነታቸው አስተምረዋል።

በክብረ በዓሉ ላይ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅን ጨምሮ የጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች፣የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ፣ ሊቀ ጉባኤ አባ ተክለሃይማኖት የአዲስ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የገዳሙ አስተዳዳሪ መልአከ አሚን ቆሞስ አባ ኃይለማርያም በፈቃዱ፣ የአድባራትና የገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ የገዳሙ ሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና ምእመናን ተገኝተዋል፡፡

ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ