“ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለኢትዮጵያ የተሰጡ ቅዱስ አባታችን ናቸው”… ሊቀ ጉባኤ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት ወልዱ

የጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት ዓመታዊ የልደት ክብረ በዓል በመርካቶ ደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ጉባኤ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት ወልዱን ጨምሮ በርካታ ካህናትና ምእመናን በተገኙበት በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተከብሯል።

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ጉባኤ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት ወልዱ በመርካቶ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ያስተላለፉት መልእክት ነው።

በበዓሉ የተገኙት ሊቀጉባኤ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት ወልዱ “አነ ውእቱ ኖላዊ ኄር” በሚል የወንጌል ርእስ መነሻነት እረኝነትን የተመለከተ ሰፊ ትምሕርት ወንጌል የሰጡ ሲሆን በትምህርታቸውም የጻድቁ ልደት የኛም ልደት ነው፣ጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ለኢትዮጵያውያን የተሰጡ ቅዱስ አባታችን ናቸው ብለዋል።

በሰሜን ሽዋ ደብረ ጽላልሽ ከአባታቸው ፀጋ ዘአብ እና ከእናታቸው እግዚእሃርያ የፀሎት ውጤት ሆነው የተወለዱት ጻድቁ አባታችን ተክለሃይማኖት በሦስተኛው ቀን አፋቸው ለምሥጋና መከፈቱን አውስተው ለዚህኛው ዘመን ትውልድ ለሃሜት አፍ ከፋቾች ትልቅ ምሳሌ ይሆናልም ብለዋል።

አክለውም ስለጻድቁ አባታችን ከሰጡት ትምህርት በተጨማሪ ሰላም ለልደትከ ተክለሃይማኖት ሐዋርያ የሚለውን መልክእ ለሕዝቡ ያስቀጸሉበትና ሕዝበ ክርስቲያኑም እየተከተላቸው የተማረበት መንገድ በደስታ ብዙ ምዕመናንን ሲያስነባ አይቻለሁ።

ከሠተ አፉሁ ወልሣኑ ነበበ አእኮቶ ለእግዚአብሔር የሚለውን ወረብ በጥዑም ዜማና ቸብቸቦ በደብሩ መምህራን ቀርቧል።

116 ዓመታት ያስቆጠረው የደብረ አማን ተክለ
ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ከ36 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ሊታደስ መሆኑን የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ገልፀው ለዚህም ምዕመናኑ የተለመደ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

በዕለቱ ታቦታተ ሕጉ ለበዓሉ ከመንበረ ክብራቸው እንደወጡ በዚያው የቤተ ክርስቲያኑ ዕድሣት እስከ ሚጠናቀቅ ድረስ ወደሚቆዩበት መቃኞ በሊቀ ጉባኤ መሪነት ገብተዋል።

ጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ሰፊ የፍቅር ቦታ ያላቸው በመሆኑ በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የሰው ስም እና የተቋማት መጠሪያ ስም ሆነው ያገለግላሉ።

ለተጨማሪ መረጃ የሀገረ ስብከቱን ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ይጎብኙ፣ like እና Join በማድረግ ይቀላቀሉ፣ ለሌሎችም ሼር ያድርጉ!!!

  1. ድረ-ገጽ:- www.addisababa.eotc.org.et
  2. ፌስ ቡክ ገጽ:- www.facebook.com/AddisAbabaDiocese/
  3. ተሌ ግራም ቻናል:- t.me/AddisAbabaDiocese

በተክለሃይማኖት አዳነ ጋዜጠኛ