“ግበሩኬ እንከ ፍሬ ሠናየ ዘይደልወክሙ ለንስሓ ፤ እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ” ማቴ ፫፥፰
ጥምቀት በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተፈጸመልን የድኅነት ምልክታችን፣ መሸጋገሪያችን እና ጠላትን ድል መንሻችን ነው።
ሐዋርያው እንደተናገረ ከመድኃኒታችን ጋር በትንሣኤው ተባባሪ ለመሆን በጥምቀት መቀበር ተገቢ ነውና (ቆላ ፪፥፲፪) ቤተ ክርስቲያናችን የዕዳ ደብዳቤያችን የተቀደደበትን፣ ልዑል አምላካችን በፍፁም ትህትና በፍጡር እጅ የተጠመቀበትን አብነት አድርገን እንድንመለከት ታስተምረናለች።
የበረሃው ኮከብ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የንስሐ ጥምቀት በሚያጠምቅበት በዚያን ወራት ከክፉ ሥራ መራቅ ብቻ ሳይሆን በጎ ሥራ መጨመር እንደሚገባ ሲያስተምር ተመልክተናል። (ማቴ ፫፥፰)
ተወዳጆች ሆይ !
በአዲስ ሕይወት እንመላለስ ዘንድ ካለፈው ዘመን የስሕተት ሥራ በመውጣት በንስሐ ታጥበን ተስፋ ለምናደርጋት ለማትጠፋው የእግዚአብሔር መንግስት ራሳችንን ልናዘጋጅ ያስፈልጋል።
በየዓመቱ የጥምቀት በዓል መከበሩም ጌታችን ከሠራት አርአያነት ካለው የጥምቀት ሥርዓት ልጅነትን እንደምናገኝ ከመዘከር በተጨማሪ የንስሐ ሕይወትን ልምድ እናደርግ እና በረከትን እናገኝ ዘንድ ነው።
የዚህን ዓመት በዓለ ጥምቀት ካለፈው መለያየታቸን ተመልሰን ሀገራችን ብሎም ዓለም ሁሉ ላይ የጦር መሣሪያ ድምፅ ሳይሰማ፣ ሕጻናትና እናቶች በሰቀቀን ውስጥ ሳይሆኑ የምናከብረው በዓል ቢሆን ደስታችን ወደር አልነበረውም። ሆኖም የምንፈጽማቸው ሁሉ የንስሐን ልብ እንዳላገኘን አመላካች በመሆናቸው በዓሉን ስናከብር ለንስሐ ተዘጋጅተን የሚገባውን ፍሬ በማድረግ መሆኑን መዘንጋት የለብንም።
በመጨረሻም በዓለ ጥምቀትን በምናከብርበት ወቅት ሠላም የራቃት ሀገራችን በእኛ ንስሐ ወደ ሰላም እንደምትመለስ በመረዳት፣ በፍጹም ክርስቶሳዊ ፍቅር እርስ በእርሳችን በመዋደድ እና በመተሳሰብ ሊሆን ይገባል።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ !
መልካም በዓለ ጥምቀት
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አሜን
+ አባ ሄኖክ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ጥር ፲ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም
አዲስ አበባ፤ኢትዮጵያ