ገዳማትና አድባራት

ካቴድራል(የካቴድራል ቤተክርስትያን)

ካቴድራል ማለት ቃሉ ግዕዝ ወይም አማርኛ ሳይሆን ጥሬ ቃሉ ግሪክ ሲሆን ወደ ላቲን ሲተረጎም (cathedra) ካቴድራል ይላል፡፡  ይህም የጳጳስ መቀመጫ (ዙፋን) ማለት ሲሆን በጥንታዊያን ክርስቲያኖች አመለካከት ካቴድራል ማለት የሥልጣን ምልክት ማለት ነው፡፡  የካቴድራል ሕንጻዎች መሠራት ያለባቸው በትልልቅ ከተማዎች ነው እንጂ በአነስተኛ መንደር መሠራት የለበትም፡፡  የካቴድራል ቤተክርስቲያን በጣም ትልቅ ግዙፍ ሕንጻ ነው፡፡ 

ጥንታዊያን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ካቴድራል ተብሎ የተሰጣቸው ስያሜ የለም፡፡  ይህም ቃሉ ያልተለመደ የባዕድ ቃል በመሆኑ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1924 ዓ.ም የተሰራውን የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን እጅግ በሥፋቱ ትልቅ በመሆኑና ውበትን የተላበሰ ዘመናዊ ሕንጻ በመሆኑ ይህን በማየትና በማድነቅ በግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ቤተክርስቲያኑ ለመጀመሪያ ጊዜ የካቴድራል ስም ተሰጠው፡፡

ከላይ እንደተገለፀው ካቴድራል ሲባል ብዙ ምዕመናን የሚይዝ ትልቅና ውበት የተላበሰ በሕንጻ አሠራሩም ካሉት ሦስት ዓይነት የቤተክርስቲያን አሠራር ውስጥ ከምኩራብ (አራት መአዘን)፤ ከክብ ቤተንጉሥ ከዋሻ አሠራር ዓይነቶች ውስጥ ካቴድራል የምኩራብ ከኦሪቱ ትውፊት የተወሰደውን ዓይነት ቅርፅ የያዘ ነው፡፡  ካቴድራል ተብሎ የሚሰየመው ይህ ታላቅ ቤተክርስቲያን ብዙ ምዕመናንን አካቶ ከመያዙም በላይ ሦስት መንበር በቤተ መቅደሱ ወስጥ ሊኖረው ይገባል፡፡  ይህም በክብረ በዓል ጊዜ በሦስቱ መንበር የቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ተከናውኖ ምዕመናን በሥርዓት እንዲስተናገዱ ይረዳቸዋል፡፡ በተለይ የካቴድራል ቤተክርስቲያን ስያሜ መጥቶ በከተማችን ውስጥ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት ከጊዜ ወደ ጊዜ በቁጥር እየጨመረ የመጣውን የምዕመናን ቁጥር በሥርዓት ለማስተናገድ የቤተክርስቲያኑ ስፋት ታላቅ ድርሻ አለው፡፡     በአጠቃላይ በጥንት ጊዜ የሌለው እና አሁን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የመጣው ካትድራል ብሎ ቤተክርስቲያንን መሰየም ዛሬ እየተለመደና ጠቃሚነቱ እየታወቀ በመምጣቱ በከተማችን በአዲስ አበባ በርካታ ታላላቅ ዘመናዊ ካቴድራሎች ታንፀዋል፡፡

ደብር(የደብር አብያተ ክርስቲያን)

ደብር ማለት ቀጥተኛ ትርጉሙን ስንመለከት ተራራ ማለት ሲሆን ይህም ደብረሲና ደብረ ታቦር በሚለው ቃል በትርጓሜ ይዘቱ የሲና ተራራ፤ የታቦር ተራራ ብለን እንረዳለን፡፡  ቤተክርስቲያን በተሠራው ሕንጻና በሕንጻው ወሰን ደብሩ እንዲህ ነው ተብሎ ውስጣዊና ውጫዊ ይዘቱን ለመግለጽ ይቻላል በሌላም መልኩ ቤተክርስቲያን በተራራ ትመሰላለች፡፡  ይህም ተራራ ከሌሎች ሥፍራ ይልቅ ጎልቶ ስለሚታይ ነው፡፡  ቤተክርስቲያንም ከሌሎች ሕንጻዎች ሁሉ ጎልታ፣ ተለይታ ትታያለች፡፡  ይህም የክርስቲያኖች የጋራ ቤት ክርስቶስ በደሙ የመሠረታት የቅድስና ስፍራ በመሆኗ ነው፡፡

ደብረ ማለት ቃሉ ዐቢይ በማለት ሲተረጎም ምሥጢሩ ያስኬዳል ይህም ደብር ተብለው የሚሰየሙት አብያተ ክርስቲያናት ባላቸው የአገልጋይ ካህናት ብዛት ቦታው ዘወትር ስብሃት እግዚአብሔር የማይለይበት ታላቅ የረድኤተ እግዚአብሔር መግለጫ በመሆኑ ታላቅ ቦታ ተብሎ ይጠራል፡፡  ለአበያተ ክርስቲያናት የሚሰጠው ስያሜ የተቀረጸው የቃል ኪዳን ጽላት በቅዱሳን፣ በጻድቃን፣ በመላዕክት፣ በስመ እግዚአብሔር ከሆነ ስማቸው ተጠቅሶ ባላቸው የነጠላ ስም ብቻ ለምሳሌ፡- የቅዱስ ሚካኤል ከሆነ ደብረ ሚካኤል ተብሎ ብቻ አይሰየምም፡፡  ግብራቸውና የሥራ ድርሻቸውን የተገባላቸውን የማይቃጠፍ የዘለዓለም ቃል ኪዳን በመግለፅ ቅዱስ ሚካኤል የምሕረት መልአክ ነውና ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ተብሎ ይሰየማል፡፡  እንደዚህ ሁሉ እያንዳንዱ ባለው የቃልኪዳን ስያሜ ደብረ እገሌ ገዳም  እገሌ ገዳም እገሌ በማለት እየተገለፀ አብያተ ክርስቲያናቱ ስያሜ ያገኛሉ፡፡  በስመ እግዚአብሔር ስም የታነጹ ደብሮች የአምላክን ስም በመግለጽ በስያሜዎች ይጠራሉ፡፡  ይህም ለምሳሌ ደብረ ምጽላል እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን ሲል ምጽላል ማለት መጠጊያ፣ መሸሸጊያ ማለት ነው፡፡  እግዚአብሔር አምላካችን ለዓለሙ ሁሉ መጠለያ፣ መሸሸጊያ ጋሻችን ነውና፡፡   

ገዳም (የገዳም አብያተክርስቲያናት)

ገዳም ማለት ምድረ በደ ማለት ነው፡፡  በገዳም የእኔ የገሌ የሚሉት ንብረት የሌለበት ሁሉ በማህበር በአንድነት በጸሎት በሥራ እየተጉ ፍጹም የዓለምን ኃላፊነት ተረድተው የማታልፍ የእግዚአብሔር መንግሥት እንዳለች በመገንዘብ ዘወትር በቀኖና ተወስነው የሚኖሩባት የቅዱሳን መኖሪያና ጸጋ እግዚአብሔር የማይለይበት ሲሆን በአንፃሩም ከሁሉ የከበደ የአጋንንት ጸር የሚበዛበት ቦታ ነው፡፡  ገዳምና ገዳማዊ ሕይወት አስፈላጊ በመሆኑ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ አርአያ ሆኖን በመገዳመ ቆሮንቶስ(በምድረ በዳ) ከዲያብሎስ የፈተን ዘንድ ተቀመጠ(ማቴ.4፡1-11)ፈታኝ ዲያቢሎስንም ድል አደረገው ገዳማዊ ሕይወትና ገዳም አስፈላጊ ሆኖ የመሠረተልን አምላካችን አርአያችን ኢየሰስ ክርስቶስ ነው፡፡  እኛም እርሱን በመከተል ገዳማዊ ሕይወት ለትሩፋት መሥሪያ፣ ለንስሐ ሕይወት መቆያ ለበረከት ለረድኤት አስፈላጊነቱን አምነን እንጠቀምበታለን፡፡

እንደ ቤተክርስቲያን ሥርዓት አብያተ ክርስቲያናት ገዳም፣ ደብር፣ ካቴድራል ገጠር ተብለው ተሰይመው ይጠራሉ፡፡  ይህ ስያሜ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚሰጠው ካላቸው ይዘት አኳያ ተጠንቶና ተመዝኖ ነው፡፡ በመሆኑም ገዳም የሚባለው ስያሜ የሚሰጠው ቤተክርስቲያኑ መነኮሳት ብቻ የሚኖሩበት ሁሉም በፀሎት በማህሌት፣ በመንፈሳዊ አገልግሎት በሕብረት የማይነጣጠሉበት በመቁነን፣ በድርጎ፣ ተወስኖ በመነኮሳት ብቻ የሚተዳደር ቦታ ነው፡፡ በገዳም ወንድና ሴት በአንድነት የማህበራዊ አገልግሎት አይገናኙም፡፡ የሴት ገዳምና የወንድ ገዳም ተለይቶ በመወሰን የተከፈለ ነው፡፡  በወንዶች ገዳም የወንዱ ገዳም አስተዳዳሪ፣ አባ ምኔት (የገዳም አባት) ተብሎ ሲጠራ የሴቶች ገዳም ደግሞ እመ ምኔት (የገዳም እናት) ተብለው ይጠራሉ፡፡  በከተማችን ውስጥም በዚህ በአዲስ አበባ ያሉት ከፊል አብያተ ክርስቲያናት ልክ ከከተማ ውጪ እንዳሉት ትላልቅ ገዳማት በሥርዓት የተስተካከሉና በመጠኑም ቢሆን ገዳማዊ ይዘት ስላላቸው ገዳም ተብለው  የተሰየሙ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት አሉ፡፡   

ቤተ ክርስትያን

ቤተክርስቲያን ማለት ሁለት ትርጉም ይዞ በዘርፍና በባለቤት የተቀመጠ ስም ነው፡፡ አንደኛው ትርጉም ቤተክርስቲያን ሲል የክርስቲያን ቤት የክርስቲያን መሰብሰቢያ የክርስቲያን መገናኛ ማለት ነው፡፡  ይህም ክርስቲያኖች በአንድነት በመሰብሰብ ወደፈጣሪያቸው ወደ ልዑል እግዚአብሔር የሚፀልዩበት የመድኃኒታቸው የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስጋ ክቡር ደም የሚቀበሉት የሚሰግዱበት ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት የፀሎት ቤት ማለት ነው፡፡  ኢሳ. 56፡7፣ኤር. 7፡10-11፣ ማቴ 21-12፣ ማር 11፡17፣ ሉቃ 1946

ሁለተኛው ትርጉም ቤተክርስቲያን ሲል የክርስቲያን ወገን ክርስቲያን የሆነ ሁሉ የሚጠራበት ስም ነው፡፡ ይህም ምሳሌ ትውፊቱ የመጣው ቤተያዕቆብ፣ ቤተ አሮን፣ ቤተ እስራኤል (የያዕቆብ ወገን የአሮን ወገን፣ የእስራኤል ወገን ማለት እንደሆነ ሁሉ ቤተክርስቲያን ሲል የክርስቲያን ወገን የሚለውን ያመለክታል) መዝ 117፡3 113፡1፡1 ማቴ 16፡18፡18፡17፣ የሐዋ 18 የመጀመሪያዋ ቤተክርስትያን በፊልጵስዮስ ሀገር እንደተሠራች የቤተክርስቲያን ታሪክ ቢያስረዳም ሐዋርያትና ሌሎች ክርስቲያኖች በሐዋርያው በማርቆስ እናት በማርያም ቤት እየተሰበሰቡ ለአመልኮ እንደ ቤተክርስቲያን ይገለገሉበት ነበር፡፡ የሐዋ 12፡12 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓተ ትምህርት ሦስት ዓይነት የቤተክርስቲያን አሠራር እንዳለ እንረዳለን፡፡  

  1. አራት መአዘን (ከምኩራብ የተወሰደ) Cote from Jewish sinagogi
    የአሠራሩ ይዘትን በተመለከተ የአራት መዓዘን ቅርፅ (የምኩራብ ዓይነቱ) የተወረሠው ከአይሁድ ምኩራብና በዘመነ ክርስትናም የታላቁ ቆስጠንጢኖስ እናት እሌኒ በኢየሩሳሌም ካሠራችው ቤተክርስቲያን የተቀዳ ነው፡፡
  2. ክብ ቅርፅ ባለሦስት ዙሪያ ክፍል (ቤተ ንጉሥ) Circel cote from king palace
    ዙሪያ ክብ አሠራር (ቤተንጉሥ) ውስጡ በሦስት ግድግደ የተከፈለ ሲሆን ስያሜው የተወረሰው ከግብሩ ከሚሠጠው አገልግሎት የተወረሰ ነው፡፡
  3. የዋሻ ቤተክርስቲያን አሠራር ናቸው (በመጋረጃ የተከፈለ) The cave churchs 
    ዋሻ ሥራ ይህ አሠራር ውስጡ በመጋረጃ ብቻ የተከፈለ ሆኖ ራሱን ችሎ በዘመነ ሐዲስ መናንያን በበረሃ የሚገለገሉበት ቤተክርስትያን ነው፡፡

ቤተክርስቲያን የተመሠረተችው በሰዎች አስተያየትና ፈቃድ  ወይም በትግል ጥረት የተመሠረተች ተቋም ሳትሆን አምላክ በደሙ  የመሰረታት መታደስ መለወጥ የሌለባት አምሳያዋም ሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም ነው፡፡ በአጠቃላይ ቤተክርስቲያን ማለት ስብሃተ እግዚአብሔር የሚደርስበት አማናዊ ቅዱስ ስጋውና ክቡር ደሙ የሚቀርብበት በማህበር ፀሎት የአምልኮተ እግዚአብሔር ሥርዓት የሚየርስበት የቃል ኪዳን ጽላቱ የሚገኝበት ክርስቲያኖች የሚሰበሰቡበት ቤት ማለት ነው፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶኮክስ ትምህርት፤ እምነትና ትውፊት መሰረት ታቦት የሌለበት ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን አይባልም፡፡