ደብረ ዘይት ( የዐቢይ ጾም አምስተኛ ሳምንት)

            ትርጉም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የዐቢይ ጾም አምስተኛ ሳምንት ደብረ ዘይት ይባላል። ስያሜውም የተገኘው ከቅዱስ ያሬድ ነው።

ደብረ ዘይት ማለት የወይራ ዛፍ ያለበት ተራራ ማለት እንደሆነና  ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ አቅጣጫ በኩል እንደሚገኝ የመጽሐፍ ቅዱሰ መዝገበ ቃላት ይገልጻል።

እንደ ማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24 ገለጻ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ የሚከተሉትን ዋና ዋና ትምህርቶች አስተምሯል፦

  1. ስለ ዓለም ፍጻሜ የመጀመሪያ ምልክቶች ተናግሯል፦

ክርስቶስ በደብረዘይት ተቀምጦ ሳለ ደቀመዛሙርቱ የዓለም መጨረሻው ምልክቱ ምን እንደሆነ? ጠይቀውት ነበር።

እርሱም ለጥያቄያቸው መልስን የሰጠ ሲሆን በስሙ በመምጣት የሚያስቱ እንዳሉ፣ የጦርም ወሬ እንደሚሰማ፣ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ እንደሚነሣ፣ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ እንደሚሆን፣ የብዙ ሰዎች ፍቅርም እንደምትቀዘቅዝ ከነገራቸው መልሶች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው። እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው በማለት ነግሮአቸዋል። ሰለሆነም እኛም ይህንን በዓል ስናከብር የዘመኑ ፍጻሜ ምልክቶች ምን ያህል እየተፈጸሙ መሆናቸውን እያስተዋልን ወደ እግዚአብሔር አብዝተን የምንቀርብበት እንደሆነ ልንገነዘብ ይገባል።

  1. ስለ ዳግም ምጽአቱ (ተመልሶ እንደሚመጣ) አስተምሯል፦

ደቀመዛሙርቱ ስለ ዓለም ፍጻሜ ብቻ ሳይሆን መምጣቱንም በተመለከተ ጥያቄ አቅርበው ነበር።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቁጥር 39 ላይ በኖኅ ዘመን የነበረውን ታሪክ ጠቅሶ “የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ፥ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል ” በማለት እንደሚመጣ ብቻ ሳይሆን እንዴትና በምን መልኩ እንደሚመጣ ተናግሯል። በሥርዓተ ቅዳሴውም  “እግዚአብሔርሰ ገሃደ ይመጽእ ወአምላክነሂ ኢያረምም እሳት ይነድድ ቅድሚሁ” እየተባለ ይሰበካል (መዝ 49፥2-3)።

3.  ተዘጋጅተን እንድንጠብቀው አዟል፦

ቁጥር 42 ላይ እንዲህ ብሏል ” ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲሚመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ ” ነቅቶ መጠበቅ መንፈሳዊ ብልህነት ነው። ቁጥር 44 ላይም ” ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና ” ብሏል። ሙሽራው ክርስቶስ ሲመጣ ሁላችንም በመንፈሳዊ ሕይወታችን ውብ ሆነን ልንጠብቀው ይገባል።

“ተዘጋጅታችሁ ኑሩ” የሚለው የጌታችን ትዕዛዝ የቤተክርስቲያን የሁልጊዜም መልእክት ነው!

ተዘጋጅቶ መኖር በየትኛውም የሥራና የሙያ ዘርፍ ወሳኝ ነገር ነው፤ ተማሪ የተማረውን ትምህርት በሚገባ አጥንቶ ለፈተና ዝግጁ ካልሆነ ወደ ሚቀጥለው ክፍል ማለፍ አይችልም። ለእርሻ የሚሆኑ በሬዎችንና ቁሳቁሶችን አስቀድሞ ያላዘጋጀ አርሶ አደር የእርሻ ወቅት ሲደርስ ማረስ አይችልም፤በሌሎች የሥራ መስኮችም ያሉ እንዲሁ።

በመንፈሳዊ ሕይወትም ተዘጋጅቶ መኖር ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ጉዳይ ሲሆን የሚከተሉትን ነጥቦችም በውስጡ ይይዛል፦

ሀ. በጽኑ እምነት መኖር፦

ክርስቶስ ወደዚህ ምድር የመጣበት ዋና ዓላማ እኛ በእርሱ ቤዛነት በፍጹም ልባችን አምነን ከኩነኔ እንድን ዘንድ ነው። ለዚህም ነው ” እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም “(ሮሜ  8፥1) የሚለው። በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት ማለት በእርሱ አምኖ በትክክለኛው መንፈሳዊ ሕይወት  መኖር ማለት ነው። እግዚአብሔርን የምናስደስተው በእምነት ስንኖር ነው።  እምነት ከሌለን እርሱን ደስ ማሰኘት አንችልም፤ ለዚህም ነው  “ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም” (ዕብ 11፥6) ተብሎ በቅዱሱ መጽሐፍ የተጻፈው። ስለሆነም በጽኑ እምነት መኖር ከሁላችንም የሚጠበቅ ነው።

ለ. በንስሐ ሕይወት መመላለስ፦

ሁላችንም በዚች ፈታኝ ዓለም ላይ ስንኖር በማሰብ፣ በመናገርና በማድረግ ኃጢአትን እንሠራለን። አግዚአብሔር ደግሞ በባህርይው ቅዱስ ስለሆነ ኃጢአትን ይጸየፋል። ስለሆነም ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ለማድረግ ዘወትር በንስሐ ሕይወት በመመላለስ በቅድስና ሕይወት መኖር ያስፈልጋል።

” ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ በብርሃን ብንመላለስ ለእያንዳንዳችን ኅብረት አለን፥ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል “(1ኛዮሐ1፥7) ስለሚል ቃሉ እርሱ መድኃኔዓለም በዕለተ አርብ ባፈሰሰው ደሙ እንዲያነጻን “ዘወትር ጠዋት ማታ ያለማቋረጥ ባፈሰስከው ደምህ ይቅር በለን፤ አንጻን ልንለው” ይገባል።

ሐ. ቅዱስ ሥጋውንና ደሙን መቀበል፦

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውንና ደሙን እንድንቀበል አዞናል። ስለሆነም ሥርዓተ ቅዳሴውን እየተከታተልን ብቻ ወደ ቤታችን መሄድ ሳይሆን ንስሐ በመግባት ቅዱስ ሥጋውንና ደሙን መቀበል ይኖርብናል።

መ. በፍቅር ሕይወት መመላለስ፦

ፍቅር የእግዚአብሔር ባህርይ ነው፤ እኛም በፍቅር እንድንኖር አዞናል። ፍቅር በብዙ ሰዎች ዘንድ እየቀዘቀዘች ባለችበት ወቅት በፍቅር መኖር ታላቅ መታደል መሆኑን ተረድተን በፍቅር ልንኖር ይገባል። እግዚአብሔር አምላካችንን በፍጹም ልባችን በመውደድ እንዲሁም አጠገባችን ያለውን ወንድማችንን በመውደድ ፍቅርን በሕይወት ልንኖረው ይገባል።  “በፍቅሬ ኑሩ” (ዮሐ 15፥9) የሚለውን ትዕዛዝ ፈጽመን ቢሆን ኖሮ ዛሬ ላይ በሀገራችንም ሆነ በዓለም ላይ የንጹሐን ደም አይፈስም ነበር። ዘወትር በፍቅር ሕይወት በመመላለስ ጥላቻ እንዲወገድ የበኩላችንን ድርሻ ልንወጣ ያስፈልጋል።

ሠ. በተስፋ መኖር፦

በመንፈሳዊው ዓለም በተስፋ መኖር ማለት በተረጋገጠና እውነተኛ በሆነ ተስፋ መኖር ማለት ነው። መንፈሳዊው ተስፋ እንደምድራዊው ተስፋ ይሆናል ወይም አይሆንም በሚሉ ሁለት ሃሳቦች የተከፈለ አይደለም። ፈተናዎችና መከራዎች እንኳን አብዝተው ሊያስጨንቁን ቢሞክሩ ” እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ” (ማቴ 11፥28) ብሎ ጌታችን የተናገረውን በማሰብና በመረዳት በእርሱ እርፍ እያልን በተስፋ መኖር ይገባናል። በተስፋ መኖር በምድራዊውና በሚጠፋው ነገር እንዳንወስድ ያደረግናል።

ጠቅለል ባለ መልኩ የደብረዘይትን በዓል በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የምናስበው ሳይሆን ዘወትር ዕለት ዕለት ያለመዘንጋት በልባችን በማስታወስ በታዘዝነው መሠረት ተዘጋጅተን በመኖር ሁለተኛ ወደ እኛ ተመልሶ የሚመጣውን ንጉሣችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በንቃትና በናፍቆት ሆነን የምንጠብቅበት ታላቅ መልእክት የተላለፈበት ነው።

             ከጾሙ በረከት ያሳትፈን!!

             ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

        በመ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ