ደቡብ ክልል የመጀመሪያ የሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ኮሌጅ ተመረቀ!
በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ መመሪያ ሰጭነት በጉራጌ አህጉረ ስብከት ተገንብቶ የተጠናቀቀው መንፈሳዊ ኮሌጅ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በጸሎት ተባርኳል።
ኮሌጁም “ዜና ማርቆስ ዘምሁር መንፈሳዊ ኮሌጅ” ተብሎ ተሰይሟል።
መንፈሳዊ ኮሌጆች ትውልዱን በመንፈሳዊ ሕይወት ለማነጽ ትልቅ ሚና እንዳላቸው ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ጠቅሰዋል።
አያይዘውም ደቀመዛሙርትን በማሰልጠን ምእመናንን በመንፈሳዊ ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ ብዙ መንፈሳዊ ኮሌጆች ለቤተክርስቲያኒቱ እንደሚያስፈልጉም አስገንዝበዋል።
በጸሎት የተባረከውም መንፈሳዊ ኮሌጅ በክልሉ ውስጥ የሚገኙትን አህጉረ ስብከቶች ጨምሮ ለመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም አብራርተዋል።
በመንበረ ጵጵስና ግቢ ውስጥ ለደቀ መዛሙርት የሚሆን የጸሎት ቤት በተጨማሪም የተለያዩ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጡ የልማት ሥራዎች ተመርቀዋል።
ቀዳማዊው ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ሆነው ባገለገሉበት ዘመናቸው ያበረከቱትን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ብፁዕነታቸው አውስተዋል።
ትልቅ ራዕይን አንግበው ከፍተኛ ቦታን ለቤተክርስቲያን በመረከብ ብዙ ትላልቅ ሥራዎችን ሠርተው እንዳለፉም ጠቅሰዋል።
“የብፁዓን አባቶቻችንን ራዕይ በማሳካት ለትወልዱ የተሻለ ነገር እናስረክባለን” ሲሉም ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ገልጸዋል።
የጉራጌ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ስ ሳህሉ ብፁዕነታቸው በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ በሀገረ ስብከቱ ያከናወኗቸውን በርካታ ሥራዎች በሪፖርት አቅርበዋል።
ስብከተ ወንጌልን ከማስፋፋት ጀምሮ መንፈሳዊ ኮሌጅ እና በመንበረ ጵጵስና ግቢ ውስጥ ለመንፈሳዊ አገልግሎቶች የሚውሉ ግንባታዎች እንዳስገነቡ፣ አዳዲስ የተሠሩ አብያተክርስቲያናትን ባርከው ለአገልግሎት እንዳበቁ፣ የተለያዩ የልማት ሥራዎችንም እንደሠሩ ከሪፖርቱ ተደምጧል።
ኮሌጁ ቀደም ብሎ ሐምሌ 15 ቀን 2013 ዓ.ም የተቀበላቸውን ደቀ መዛሙርትም በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
ደቀመዛሙርቱ በትምህርት ቆይታቸው ያገኟቸውን ስልጠናዎች ለምእመናን በማዳረስ መንፈሳዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም ተገልጿል።
በተያያዘም ቅዱስ ሲኖዶስ በዘንድሮው በጥቅምት ወር ባካሄደው ጉባኤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ መንፈሳውያን ኮሌጆችን አሁን ቤተ ክርስቲያኒቱ ከደረሰችበት የእድገት ደረጃ ጋር ለማመጣጠንና ተጨማሪ ኮሌጆች በማስፈለጉ በደቡብ ክልል የሚገኙ ሁለት ካህናት ማሠልናዎች ወደ መንፈሳዊ ኮሌጅ እንዲያድጉ አስፈላጊውም በጀት እንዲመደብላቸው መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡
በዚሁ መሠረት ከቅዱስ ሲኖዶስ ለኮሌጁ 3,000,000 ዓመታዊ በጀት መመደቡን የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በሪፖርት አስደምጠዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ሰ ሳህሉ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ገባኤ አባ ተክለ ሃይማኖት ወልዱ፣ የጉራጌና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አህጉረ ስብከት የዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ ሊ/ት ቀሲስ ታጋይ ታደለ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የክፍላተ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጆች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና ምእመናን ተገኝተዋል።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ
የዜናው ምንጭ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ