“ይእዜ አስተርአየ እግዚአብሔር ዮም እምቅድስት ድንግል፤ ዛሬ እግዚአብሔር ከቅድስት ድንግል በሥጋ ተወልዶ ታየ” ሃይ.አበው ዘቴዎዶጦስ
ተወዳጅ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ
እንኳን ለ፳፻፲፯ ዓ.ም የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በሰላምና በጤና አደረሰን አደረሳችሁ !
አባቶቻችን ሊቃውንት እንዳስተማሩን በዛሬው ዕለት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተዋረደውን የእኛን ሥጋ በመዋሐድ ከወድቀት ወደ ከፍታ፤ ከመዋረድ ወደ ክብር ከፍ አድርጎናል።
ሁሉን ቻይ የሆነው አምላካችን ከአዳም ባሕርይ ከተገኘች እመቤታችን እንበለ ዘርዕ ነፍስንና ሥጋን ተዋሕዶ አከበረን።
ለአንዲት ሰከንድ ቆም ብለን እናስብ የምንናገረው አምላክ ሰው የመሆኑን ምሥጢር ነው፤ የኃጢአትን ቁራኝነት የሚያጠፋ ጌታ በጨርቅ ተጠቀለለ፣ የማይወሰን እርሱ በእመቤታችን ማኅፀን ተወሰነ፣ ከጌትነቱ ሳይለወጥ ወይም ሳይለይ ከሰው ተወለደ እያልን ነው !
ታዲያ ይህ ሁሉ የሆነው ለምንድነው? በጨርቅ የተጠቀለለው ጌታ የብርሃንን ጸጋ ሊያጎናጽፈን አይደለምን? በማኅፀን የተወሰነው ጌታ መንግስቱን ወራሾች ሊያደርገን አይደለምን? ይህ ሁሉ የተከፈለ ዋጋ ስለ ማን ነው? ስለ እኛ አይደለምን?
ተወዳጆች ሆይ !
በዚህ ሁሉ ያከበረንን አምላክ ውለታውን በምን እየመለስን ነው? ወንድማችንን በመጥላት? እርስ በእርስ በመለያየት እና በመገዳደል? ይህ ሁሉ ከጌታችን ትምህርት እና ሰው የመሆኑ አላማ ጋር አያለያየንም? ዛሬ በዚህች ዕለት እና ሰዓት የመወለዱን ዜና ስናነሳ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ሕግ ወጥቶ እርስ በእርሱ በጦርነት እና በመለያየት ውስጥ መሆኑን ስናስብ የሰላም ጌታ የመወለዱንና ለዘመናት በምድራችን የነበረውን ጨለማ የገፈፈ አምላክ ሰው የመሆኑ ድንቅ ምሥጢር በምድራችን ያልተሰበከ እስከሚመስል ድረስ መንገዳችን ተለያይቶ ይገኛል።
በዚህ እውነተኛ ቸር ጠባቂያችን ብርሃናዊ ልደቱን ባየንበት እና በቀደሙ አባቶች የተሰበከልን የልደቱ ምሥጢር በሚነገርበት በዓል ከክፉ ልማድ ጋር የመኖርን የቀደመ ግብር ትተን በክርስቶስ ኢየሱስ አዲሱን ሕይወት ልንጀምር ይገባናል።
በመጨረሻም በዓለ ልደትን በምናከብርበት ወቅት እግዚአብሔር አምላካችን በሀገራችን እየታየ ከሚገኘው የተፈጥሮ አደጋ እንዲሰውረን በጸሎት በመትጋት፤ የተራቡና የተጠሙ ወገኖችን በማሰብ በበጎ ሥራ በመትጋት ሊሆን እንደሚገባ አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
መልካም የልደት በዓል
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ !
+ አባ ሄኖክ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ታኅሣሥ ፳፰ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም
አዲስ አበባ፤ኢትዮጵያ
©የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ