“ያለው ቦታ ጠባብ ነው ከማለት ይልቅ ባለው ቦታ ልማትን ማልማት ብልህነት ነው” …ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ

“ያለው ቦታ ጠባብ ነው ከማለት ይልቅ ባለው ቦታ ልማትን ማልማት ብልህነት ነው” ሲሉ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ ገለጹ።

ብፁዕነታቸው ይህንን ያሉት ከብፁዕ አቡነ ናትናኤል የምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ጋር በአፍሪካ ኅብረት ደ/ም/ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል በመገኘት ምእመናንን፣ የልማት ሥራዎችንና በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘውን ሕንጻ በጎበኙበት ወቅት ነው።

በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው ሕንጻ መታሰቢያነቱና ስያሜው በሊቢያ ምድር  ሰማዕታት ለሆኑት ኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክስ ወጣቶች እንደሆነ ተገልጿል።

ብፁዕነታቸው በዚህ በጠባብ ቦታ ይህን የሚያህል ትልቅ ሕንጻ በማነጻችሁ የሚደነቅ ነው ብለዋል።

የሕንጻው ስያሜ ከዓመታት በፊት በሊቢያ ሰማዕታት በሆኑት ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች መሆኑ የሚያስደስት እንደሆነ አያይዘው ጠቅሰዋል።

ዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 4 ቁጥር 4 ላይ ያለውን የእግዚአብሔር ቃል መነሻ በማድረግ ሰፊ ትምህርት ሰጥተዋል።

በተያያዘም ዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ  “አበረታች መድኃኒት” በሚል ስያሜ የጻፉትን መጽሐፍ  ካቴድራሉ አሳትሞ ከመጽሐፉ የሚገኘውን ገቢ ለሕንጻው እንዲያውል በስጦታ አበርክተዋል።

ሕንጻው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኝ ሲሆን ለካህናት ማረፊያ፣ ለሰንበት ት/ቤት ወጣቶች መማሪያ፣ ለስብሰባና ለመንፈሳዊ ትምህርት ሥልጠና፣ ለቢሮና መሰል አገልግሎቶች እንደሚውል ተገልጿል።

የካቴድራሉ አስተዳዳሪ መ/ሳ ቀሲስ አለማየሁ ዘውዴ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ በቦታው ተገኝተው ምእመናንንና የካቴድራሉን የልማት ሥራዎች በመጎብኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፤ ምሥጋናም አቅርበዋል።

በመ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ

ፎቶ በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ