የ2013 አዲሱን ዓመት አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የእንኳን አደረሳችሁ መግለጫ ተሰጠ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የ2013 አዲሱን ዓመት አስመልክተው በሀገራችን በኢትዮጵያና በመላ ዓለም ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵውያት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ቅዱስነታቸው የዘመናት ፈጣሪ የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ 2012 ዓ/ም ወደ ዘመነ ማቴዎስ 2013 ዓ/ም በሰላም አደረሳችሁ በማለት እግዚአብሔር መነሻም ሆነ፥ መገስገሻ እንዲሁም መድረሻም የሌለው፣ ለፍጡር ግን መነሻውም፥ መድረሻውም፥ መገስገሻውም እርሱ ነውና ያለን ብቸኛ አማራጭ የተሰጠንን ጊዜ ሳናባክን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል መሆኑን ገልጸዋል።

የተግባር ተሞክሮ የሚገኘው ከሚመጣው ዓመት ሳይሆን ካለፉት ዓመታት መሆኑነ በመግለጽ ያለፈውን ዓመት ስንመዝነው በሀገራችን ብዙ ችግርና ምስቅልቅል እንዲከሠት ምክንያቶች ሆነን ተገኝተናል። ችግሩም በባዕዳን ሳይሆን ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸምነው ኢሰብአዊ ድርጊት በመሆኑ የምንኮራበት ሳይሆን እጅግ የምናፍርበት ሆኖ ተገኝቶአል ሲሉ ገልጸውታል።

በመሆኑም በርእሰ ዐውደ ዓመት ቀን አዲሱን ዓመት አንድ ብለን ስንጀምር ያለፈውን ዓመት ላፍታ ቆም ብለን በማሰብ ባለፈው ዓመት የተከሠቱትን ድክመቶች በአዲሱ ዓመት ላንደግማቸው ቆርጠን በመወስን አዲሱን ዓመት መልካም ሥራና መተሳሰብ የሚሰፍንበት ለማድረግ አብያተ ሃይማኖት የማይቃጠሉባትና የማይደፈሩባት፥ ዜጎች በወገኖቻቸው የማይሞቱባት፥ የማይፈናቀሉባትና የማይሰጉባት ሀገር ለመገንባትና ሰላሟን ለማረጋገጥ እያንዳንዱ ዜጋ ቃል ኪዳን መግባት እንዳለበት ተማጽነዋል።

በመጨረሻም፦ ግጭት መፍጠር የተሸናፊነት እንጂ የአሸናፊነት መንገድ አለመሆኑን በመረዳት በውይይት ችግርን መፍታት ትልቁ ድል እንደሆነ በመገንዝብ በአዲሱ ዓመት ሁሉም ወገኖች ለሰላም መስፈን ዝግጁ እንዲሆኑ በእግዚአብሔር ስም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን በማለት አዲሱ ዘመን የሰላም፥ የልማትና የአንድነት ዘመን እንዲሆን በመመኘት መግለጫውን በቡራኬ ዘግተዋል።

                                                     መ/ር ኪደ ዜናዊ የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ

ሙሉውን መግለጫ ማንበብ ይችሉ ዘንድ ከታች አስቀምጠነዋል።
ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ
ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት
ዘዕሥራ ምእት ዐሠርቱ ወሠለስቱ ዓመተ ምሕረት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን።

❖ በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
❖ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፣
❖ የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣
❖ በሕመም ምክንት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
❖እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤት የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵውያት በሙሉ!

የዘመናት ፈጣሪ የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ሁለት ሺሕ ዐሥራ ሁለት ዓመተ ምሕረት ወደ ዘመነ ማቴዎስ ሁለት ሺሕ ዐሥራ ሦስት ዓመተ ምሕረት በሰላም አደረሳችሁ።

«ተዘከርኩ ዓመተ ዓለም ወአንበብኩ፤
ዓመተ ዓለምን አሰብሁ፥ አነበብሁም»
(መዝ. //፥)

ሁሉም እንደሚገነዘበው ፍጡር የሆነ ሁሉ የዕድሜ ልክ አለው፤ ፍጡር የሆነ ሁሉ መነሻም፥ መገስገሻም፥ መድረሻም አለው፤ ፍጡር የሆነ ሁሉ ከዚህ ውጭ አይደለም። መነሻም፥ መገስገሻም፥ መድረሻም የሌለው አንድ ብቻ ነው፤ እሱም እግዚአብሔር ነው። ሌላው ፍጡር ግን መነሻውም፥ መድረሻውም፥ መገስገሻውም እግዚአብሔር ነው።

ስፍር ቍጥር ከሌላቸው ፍጡራን መካከል አንዱ ጊዜ ነው። እንደ ቤተ ክርስቲያናችን አቈጣጠር ሳድሲት ተብላ ከምትታወቀው የመጨረሻዋ ደቃቅ የጊዜ ስሌት እስከ ዓመተ ዓለም ያለው ሰፊ የቊጥር ስሌት በተለያዩ ምዕዋዳት እየተሽከረከረ እንደሚኖር እንገነዘባለን።

ይህ የጊዜ እሽክርክሪት በእግዚአብሔር ሕግና ቊጥጥር ሥር ያለ በመሆኑ ፍጡራን ሊቈጣጠሩት አይችሉም። ይሁን እንጂ ባይቈጣጠሩትም ሊጠቀሙበት ይችላሉ ብቻ ሳይሆን እንዲሠሩበት በእግዚአብሔር ታዘዋል።

እግዚአብሔር ፍጥረታትን ሲፈጥር ለፍጡራን ጥቅም እንጂ እንዲሁ ለከንቱ አልፈጠረም። እንደሌላው ሁሉ ጊዜም ሠርተን ልንጠቀምበት እንደተፈጠረ ተግባሩ ራሱ ምስክር ነው። በሰው የሚደርሱ ኪሳራዎች ሁሉ በተለያየ ስልት ሊተኩ ይችላሉ፤ የጊዜ ኪሳራ ግን መተካት አይቻልም። ያለው ብቸኛ አማራጭ ጊዜን ሳናባክን ጥቅም ላይ ማዋል ነው።

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤
የእግዚአብሔር ቃል ዓመተ ዓለምን እንድናስብ የሚያስተምረን ያለ ምክንያት አይደለም፤ ሰው በተፈጥሮ አዋቂ ሆኖ የተፈጠረ ቢሆንም ከተሞክሮ የሚወስደው ዕውቀት ከፍ ያለ እንደሆነ የሚያከራክር አይደለም። የተግባር ተሞክሮ የሚገኘው ደግሞ ከሚመጣው ዓመት ሳይሆን ካለፉት ዓመታት ነው። ስለሆነም እግዚአብሔር ዓመተ ዓለምን እንድናስብ የሚያዘን ካለፈው ዘመን ተሞክሮ ወስደን ድክመትን በጥንካሬ በመለወጥ በቍጭት ለተሻለ ሥራ እንድንነሣ ለማስቻል ነው። ከዚህ አንጻር ያለፈውን ዓመት ስንመዝነው በሀገራችን ብዙ ምስቅልቅል እንዲከሠት ምክንያቶች ሆነን መገኘታችን ይታያል።

የአማንያን ሀገር እንደሆነች ኮርተን በምንመሰክርላት ኢትዮጵያ አብያተ ሃይማኖት ሲቃጠሉ፥ አማንያን ሲገድሉ፥ ዜጎች በተለያየ ምክንያት አካላዊ፥ ሥነ ልቡናዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ሲደርስባቸው በሀገራቸው በስጋትና በጭንቀት ሲኖሩ ተስተውሎአል።

ይህ የተፈጸመው በሌሎች ባዕዳን ሳይሆን ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸምነው ኢሰብአዊ ድርጊት በመሆኑ እጅግ የምናፍርበት ሆኖ ተገኝቶአል።
በመሆኑም ይህንን ሁናቴ ለማስተካከል ባለፉት ወራት በተነሣው ግርግር የሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ያጋጠማቸውን ወገኖች ለመርዳትና ለማቋቋም ቤተ ክርስቲያናችን በምታደርገው መጠነ ሰፊ ርብርብ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ለዚህ ለተቀደሰው ዓላማ እጃችሁን በመዘርጋት እንድትተባበሩ ወቅታዊ መልእክታችን ነው ፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤
በኢትዮጵያ ርእሰ ዐውደ ዓመት ቀን ቆመን አዲሱን ዓመት አንድ ብለን ስንጀምር ያለፈውን ዓመት ላፍታ ቆም ብለን ማሰብ ይኖርብናል። ቀጥሎም ባለፈው ዓመት የተከሠቱትን ድክመቶች በአዲሱ ዓመት ላንደግማቸው ቊርጥ ውሳኔ አሳልፈን ወደ ሥራ መግባት ይገባናል።

በአዲሱ ዓመት አብያተ ሃይማኖት የማይቃጠሉባትና የማይደፈሩባት፥ ዜጎች በወገኖቻቸው የማይሞቱባት፥ የማይፈናቀሉባትና የማይሰጉባት ሀገር ለማረጋገጥ እያንዳንዱ ዜጋ ቃል ኪዳን መግባት አለበት።

ይህ እውን ሊሆን የሚችለው አስተማማኝ ሰላም ሲኖር ነው። ይህ ዓይነቱ አስተማማኝ ሰላም ሊረጋገጥ የሚችለው ደግሞ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ስለ ሰላም፥ ስለ ሀገር አንድነት፥ ስለ ዜጎች እኩልነትና ስለጋራ ጥቅም አንድ ላይ ሆነው በጥልቀት በመመካከር በሚፈጥሩት ሀገራዊ መግባባት እንደሆነ ኢትዮጵያውያን ሁሉ መገንዘብ አለባቸው።

ስለሆነም ኢትዮጵያውያን ሁሉ በዚሁ ዙሪያ በአዲሱ ዓመት በአጽንዖት እንዲያስቡበት እንመክራለን። የእልክና የበቀል አመለካከት ሀገራችንን ዋጋ እንዳያስከፍላት መጠንቀቅ አለብን።

በመጨረሻም፤
በአዲሱ ዓመት በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭም ለሚገኙት ለመላው ኢትዮጵያውያን የምናስተላልፈው ጽኑዕ መልእክት፦ ግጭት መፍጠር የተሸናፊነት እንጂ የአሸናፊነት ፍኖት አለመሆኑ፥ በአንጻሩ ደግሞ በክብ ጠረጴዛ ተወያይቶ ችግርን መፍታት ትልቁ ድል እንደሆነ ግንዛቤ ተወስዶ በአዲሱ ዓመት ሁሉም ወገኖች ለሰላም መስፈን ዝግጁ እንዲሆኑ በእግዚአብሔር ስም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

አዲሱ ዘመን የሰላም፥ የልማትና የአንድነት ዘመን ያድርግልን።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ፤ ይቀድስ።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ።
አሜን።

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
መስከረም 1 ቀን 2013 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያ