የ 2014 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል አከባበርን በተመለከተ በመካነ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ ቤተክርስቲያን ውይይት ተካሄደ

ነሐሴ 25 ቀን 2013 ዓ.ም
( አዲስ አበባ፡ ኢትዮጵያ )
መጪውን የ 2014 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል አከባበርን በተመለከተ በመካነ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ ቤተክርስቲያን ውይይት ተካሄደ።
በመስቀል አደባባይ የሚከበረውን የዘንድሮውን የመስቀል ደመራ በዓል የሚያዘጋጀው የመካነ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ ቤተክርስቲያን በጥሩ ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።
የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ፀሐይ ቀሲስ በቀለ ተሰማ ለብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ለመ/ር አካለወልድ ተሰማ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅና ለልዑካኑ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል።
ብፁዕነታቸው ደብሩ ለበዓሉ እያደረገ ያለውን ዝግጅት ተመልክተዋል።
ለደብሩ አገልጋዮችና ምእመናን ዕድሉ ስለ ደረሳችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ቤተክርስቲያኑ ጥንታዊ፣ ታሪካዊና አንጋፋ በመሆኑ የዘንድሮውን የመስቀል በዓል እንዲያዘጋጅ መመረጡንም ጠቅሰዋል።
ከደብሩ አስተዳዳር ሠራተኞች፣ ከሰበካ ጉባኤው፣ ከማኅበረ ካህናቱ፣ ከሰንበት ትምህርት ቤቱ ተወካዮችና ከአከባቢው ምእመናን ጋር ስለ መርሐ ግብሩ ውይይትም አድርገዋል።
የደብሩ ምክትል ሊቀ መንበር ተሻለ ዛፉ የበዓሉን ዝግጅት አስመልክቶ በደብሩ ሶስት ትላልቅ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቅሰዋል።
ለበዓሉ የሚመጥኑና ለአገልግሎት የሚውሉ በቂ አልባሳት መዘጋጀታቸውን፣ በአባቶች ያሬዳዊ ዝማሬ ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑና ለአንዳንድ ወጪ የሚውል በቂ ገንዘብ መሰብሰቡን ተናግረዋል።
ብፁዕነታቸው እየተደረገ ያለውን ዝግጅት አድንቀው መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች እንዲስተካከሉ መመሪያዎችን አስተላልፈዋል።
ብፁዕነታቸው ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘም ጥንቃቄ እንዲደረግ ከወዲሁ አሳስበዋል ።
ብፁዕነታቸው በበዓሉ ላይ የሚቀርቡት መንፈሳዊ መርሐግብሮች ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አስተማሪና መካሪ እንዲሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ ደብሩ 115 ዓመት ያስቆጠረ መሆኑን አውስተዋል።
አክለውም ቤተክርስቲያኑ ትላልቅ አባቶችን ያፈራ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ መርሐ ግብሩን በተመለከተ ደብሩ አስቀድሞ በቂና የሚያስደስት ዝግጅት ሲያካሄድ መቆየቱን ገልጸዋል።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ