የ፳፻፲፰ ዓ/ም የጥምቀት በዓልን ሥርዓቱን ጠብቆ በሰላም ማክብር እንደሚገባ ተገለጸ

የ፳፻፲፰ ዓ/ም የጥምቀት በዓል አከባበርን አስመልክቶ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ መሪነት ታኅሣሥ ፲፬ ቀን ፳፻፲፰ ዓ/ም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በጽርሐ ተዋሕዶ አዳራሽ የምክክር ጉባኤ ተካሂዷል።
የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት በየዓመቱ ከጥር ፲-፲፪ ቀን በመላው ኢትዮጵያና ከሀገር ውጭም በመላው ዓለም በደመቀ ሁኔታ እንደሚከበር የሚታወቅ ነው።
በተለይ በአዲስ አበባ በጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክሃይማኖት፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች፣ ልዩ ልዩ የክብር እንግዶች፣ በተገኙበት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ማኅበረ ካህናትና ምዕመናንና መዕመናት፣ የሰንበት ት/ቤቶች፣ ወጣቶች፣ በተገኙበት መንፈሳዊ ሥነ- ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ በድምቀት የሚከበር በዓል ነው።
የዘንድሮ የ፳፻፲፰ ዓ/ም በዓለ ጥምቀትም መንፈሳዊ ትውፊቱና ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ በሰላም ለማክበር በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መሪነት ከሚመለከታቸው አካላት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በጽርሐ ተዋሕዶ አዳራሽ የምክክር ጉባኤ ተካሂዷል።
በተዘጋጀው ጉባኤ ላይ በዲ/ን ዶ/ር በለጠ ብርሃኑ የጥምቀት በዓል አከባበር ተግዳሮቶችና የመፍትሔ ሐሳቦች በሚል ርእስ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቧል።
ዶኮተሩ ከጥምቀት አከባባር ታሪካዊ ዳራ ተነሥተው እስከ አሁን ባለው ሂደት በአጠቃላይ 6 ዋና ዋና ነጥቦች አንሥው አብራርቷል።
በዓሉ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና ብሄራዊ ገጽታ ያለው መሆኑን እና በኢኮኖሚም ዓለም አቀፋዊ የቱሪስት መስሕብ ያለው መሆኑን ተናግሯል።
ዶክተሩ ስለ ችግሮቹና ፈተናዎቹ ሲያብራሩ በዓሉ በተወሰነ መልኩ ከመንፈሳዊ ገጽታ ይልቅ ዓለማዊ ይዘት የሚታይበትና የሚጎላበት ሁኔታና ጊዜ እንዳለው ገልጸዋል።
ዶክተሩ የመፍትሔ ሓሳቦችንም ያቀረቡ ሲሆን መነፈሳዊ ሥርዓቱ ጠብቆ እንዲከበር የሁላችን ድርሻ መሆን እንዳለበት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የካህናት አስተዳደር ምክትል መምሪያ ኃላፊ የሆኑት ሊቀ ማእምራን ብርሃነ መስቀል ገበየው በአዲስ አበባ ከተማ
የ፳፻፲፰ ዓ/ም የጥምቀት በዓል አከባበር አስመልክቶ ከከተራ አስከ ፍጻሜ በወጣው መርሐ ግብር ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የዐዲስ አበባና የሀድያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የጥምቀት በዓል የምንደምቅበት፣ ማንነታችን የሚገለጥበት በዓላችን ስለሆነ ከአለባበስ ጀምሮ እስከ ሰዓት አከባበር ያለው ሂደት በኹለመናው መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ መከበር እንዳለበት አሳስበዋል።
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የሁለቱ አህጉረ ስብከቶች ኃላፊዎች በዚህ መልኩ ስለ በዓሉ ለመወያየት መገናኘታቸው በዓሉ ያማረና የሠመረ እንዲሆን ስለሚያደርገው እጅግ መልካም መሆኑን ተናግረዋል።
ብፁዕነታቸው የበዓሉን ድባብ ለማበላሸት ብዙ ጥረት የሚያደርጉ፣ ወረቀት እስከ መበተንና ብዙ የተለያየ ዘዴ እየተጠቀሙ የበዓሉን ይዘት መቀየር የሚፈልጉ አካላት ሲለሚኖሩ በዓሉን በደመቀ መልኩ ለማክበርና በሰላም ለማሳለፍ ሁላችን በንቃትና በጥንቃቄ መከታተል ይገባል ብለዋል።
በመጨረሻም የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ እኛ ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነትና መንፈሳዊ አገልግሎት የምንሠራ የክርስቶስ ወታደሮች ነን፤
ዓላማችን መንፈሳዊ አገልግሎት በመስጠት ሰውና እግዚአብሔርን ማገናኘት ነው፤ ተቀዳሚ ሥራችንም የቤተ ክርስቲያን ትውፊት፣ ቀኖና እና ሥርዓት በማክበርና በማስከበር ቤተ ክርክቲያንን የምናገለግል ነን ብለዋል።
ብፁዕነታቸው በዓሉን ለማክበር በአንድ ልብ በአንድ ሓሳብ ሆነን ነቅተን ኃላፊነታችን እንድነወጣ ይገባል ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በጉባኤው ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የዐዲስ አበባና የሀድያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያው ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ምሕረት ገ/መድኅን ንጉሤ(ቆሞስ)፣ የሸገር ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የሁሉቱም አህጉረ ስብከት የዋና ክፍል ሐላፊዎች፣ የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆችና የሥራ ሐላፊዎች፣ የገዳማቱና አድባራቱ አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎች የሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቃነ መናብርት፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ሰብሳቢዎችና የሚመለከታቸው ሁሉ ተገኝተዋል የአትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን ድርጅት ዘግቧል።