የጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት የዕረፍት በዓል በመርካቶ ደብረ አሚን ተክለሃይማኖት ገዳም ተከብሮ ዋለ
ነሐሴ 24 ቀን 2013 ዓ.ም
( አዲስ አበባ፡ ኢትዮጵያ )
ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ዕለቱን በተመለከተ ትምህርት አስተላልፈዋል።
ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ይህንን ዓለም በመናቅና ሕይወታቸዉን ለእግዚአብሔር በመስጠት እንደኖሩ ገልጸዋል።
ጻድቁ በጾም፣ በጸሎትና በምስጋና ሕይወት እንደኖሩም ጠቅሰዋል።
አያይዘውም ወንጌልንም በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ ለምእመናን መስበካቸውን አውስተዋል።
በመድኀኒታችንና በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተለያዩ ተአምራትን ስለማድረጋቸውም ገልጸዋል።
ነሐሴ 24 ቀን በዓለ ዕረፍታቸው ስለሆነ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ ታስቦ ይውላልም ብለዋል።
ጽድቅ የክርስቶስ ባሕርይ ስለሆነ በእርሱ በፍጹም ልባቸው አምነው እንደ እርሱ ፈቃድ የሚመላለሱ በጸጋው ጻድቃን እንደሚባሉ አብራርተዋል።
ክርስቲያኖች የሆንን ሁሉ የጻድቃንን ክብረ በዓል ስናከብር እነርሱ ክርስቶስን በፍጹም ልባቸው እንዳመኑት ሁሉ እኛም በፍጹም ልባችን አምነን ባማረ መንፈሳዊ ሕይወት እንድንመላለስ አጽንኦት ሰጥተው መልእክት አስተላልፈዋል።
አያይዘውም ኢትዮጵያ በቅዱሳንና በጻድቃን ጸሎት ከፍ ብላ የታየችበትን ዘመንም ጠቅሰዋል።
አሁን ካለው ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አያይዘው ከልብ ሆነን ሳናቋርጥ ወደ እግዚአብሔር ልንጸልይና ልናነባ እንዲሁም ንስሐ ልንገባ ያስፈልጋል ብለዋል።
ዛሬ ላይ ለምን መከራችን በዛ? ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል ሲሉም ተደምጠዋል።
ረሃቡ፣ ጦርነቱና የኑሮ ውድነቱ የመጣው መተሳሰብ ስለጠፋ ነው ብለዋል።
ወደ ቤተክርስቲያን ስንመጣ እግራችን ብቻ ሳይሆን ልባችንም አብሮ ይምጣ በማለት ገልጸዋል።
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተለይ በአሁን ሰዓት ወጣቱ እራሱን ከክፍ ነገር አርቆ የጻድቃንን መንገድ በመከተል ለእግዚአብሔር እንዲታዘዝ አባታዊ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።
ሊቀ ጉባኤ አባ ተክለሃይማኖት የአዲስ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ” እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች “(ዮሐ 12፥24) በሚል ርዕስ ተነስተው ትምህርተ ወንጌል አስተላልፈዋል።
ገዳሙ 115 ዓመት ያስቆጠረ መሆኑን የገዳሙ አስተዳዳሪ መልአከ አሚን ቆሞስ አባ ኃይለማርያም በፈቃዱ ጠቅሰዋል።
አያይዘውም ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ ጥንታዊ ከመሆኑ የተነሣ ዕድሳት ሊደረግለት እንደሆነ ገልጸዋል።
ዕድሳቱ ሲጀምር ምእመናኑ በገንዘብ፣ በሃሳብ፣ በሙያና በተለያዩ ቁሳቁሶች ዕርዳታ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጥተዋል።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ