የጥቅምት 2011 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተጀመረ

                                                       መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን

  • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ራብዓይ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፤
  • ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅና በክልል ትግራይ ደቡባዊ ዞን ማይጨውና ደቡባዊ ምሥራቅ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
  • ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
  • ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ወኤጲስ ቆጶሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤
  • በአጠቃላይ በዚህ ዓመታዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ ሥርዐት የተገኛችሁ ኹሉ፤

ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ባለችው ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያናችን፣ ሃይማኖታዊ አገልግሎታችንን እየባረከ ዘወትር የማይለይ እግዚአብሔር አምላካችን፣ አሁንም ለበለጠ ሐዋርያዊ ሥራ እንድንመካከር በስሙ ስለ ሰበሰበን ስሙ የተመሰገነ ይኹን፡፡

በቤተ ክርስቲያናችንም ኾነ በዓለም አቀፍ ክርስቲያናዊ አስተምህሮ እንደሚታወቀው፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ መሠረቱ ክርስቶሳዊ አስተምህሮ፣ ሐዋርያዊ ትውፊትና ቀኖና ቅዱሳን አበው ነው፡፡

ክርስቶስ መድኃኒታችን፣ በስሜ በምትሰበሰቡበት እኔ በመካከላችሁ እኖራለሁ፤ ብሎ ቃል ኪዳን ገብቶአል፤ ይህን ተከትሎም የመጀመሪያው ሲኖዶሳዊ ጉባኤ፣ በቅዱሳን ሐዋርያትና በቀሲሳን ኅብረት በቅድስት ሀገር በኢየሩሳሌም ማእከላዊነት፣ በቅዱስ ያዕቆብ እኁሁ ለእግዚእነ ርእሰ መንበርነት፣ በዘመነ ሐዋርያት እንደተካሔደ፣ ወአንገለጉ ሐዋርያት ወቀሲሳን ከመ ይርአዩ ዘይገብሩ በእንተዝ ነገር፤ ሐዋርያትና ቀሳውስትም ስለዚህ ነገር ለመመካከር ተሰባሰቡ ተብሎ በቅዱስ መጽሐፍ ተመዝግቦአል፡፡ የተወሰነው ውሳኔም፣ መንፈስ ቅዱስ ያለበት መኾኑን ለማመልከት፣ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናል ተብሎ ተገልጾአል፡፡ (የሐዋ ሥራ 15፥6-29)ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በቤተ ክርስቲያናችን ያጋጠሙ ፈተናዎችን ለማየት፣ ላለፈው እርማትና ማስተካከያ ለመስጠት፣ ለሚቀጥለው የሥራ አቅጣጫን ለማስቀመጥ፣ ተላውያነ ሐዋርያት በየጊዜው ሲኖዶሳዊ ጉባኤ ያካሒዱ እንደነበር ኹላችንም የምናውቀው ነው፤ በተለይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በዓለ ቅዱስ መስቀል በተከበረ በኻያ አምስተኛ ቀን ጥቅምት ዐሥራ ኹለት እና የትንሣኤ በዓል በዋለ በኻያ አምስተኛው ቀን በርክበ ካህናት፣ በድምሩ በዓመት ኹለት ጊዜ እንዲካሔድ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መደንገጉ በፍትሕ መንፈሳዊ ተጽፎ ይገኛል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ዋና ዓላማ፣ ቤተ ክርስቲያን፥ ከዓላውያን፣ ከአረማውያንና ከከሐድያን በየጊዜውና በየአቅጣጫው የሚሰነዘርባትን ጥቃት በሃይማኖት ጽናት ለመቋቋም፣ በድንበር፣ በወንዝ፣ በባሕር፣ በየብስ፣ በዘር፣ በጎሣ፣ በፆታ፣ በቀለም፣ በሀብት፣ በሥልጣን፣ በዕውቀት፣ በጉልበት፣…ወዘተ ሳትገደብ መንግሥተ እግዚአብሔርን በዓለም ዙሪያ ኹሉ ለመስበክ፣ ለምእመናን መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎትን ለማበርከት፣ በሰው ልጆች መካከል እኩልነት፣ ሰብአዊነትና ፍትሕ እንዲሰፍን የበኩሏን አስተዋፅኦ ለማድረግ እንድትችል ነው፡፡

ሐዋርያዊት፣ዓለም አቀፋዊት፣ አንዲትና ቅድስት የኾነችው ቤተ ክርስቲያናችን የክርስቶስን አስተምህሮ፣ የቅዱሳን ሐዋርያትና የቀደምት ቅዱሳን አበውን ፈለግ ተከትላ፣ እነኝህን ዓላማዎች በመፈጸም ለኹለት ሺሕ ዘመናት ያህል ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ስታገለግል ኖራለች፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ጥንታዊውን የሐዋርያት ትውፊት፣ ቀኖና እና ሥርዐት ጠብቃ በማስጠበቅ ያልተበረዘ፣ ያልተከለሰና ያልተሸራረፈ ሃይማኖታዊ አስተምህሮን በመከተል በዓለም ውስጥ የተዋጣላት ብቸኛዋ ቤተ ክርስቲያን እንደኾነች ኹሉም የዓለም ክርስቲያኖችና ተመራማሪዎች ያረጋገጡት እውነት ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን በምትከተለው ጥንቁቅ አስተምህሮና የማይናወጽ ጽንዐ ሃይማኖት፣ ለሀገሪቱ አንድነትና ነጻነት፣ የግልዋ መለያ ለኾኑ ባህላዊ፣ ቁሳዊና መንፈሳዊ ቅርሶች መጠበቅ የአንበሳዋን ድርሻ ወስዳ እስከ ዛሬ በድል ለመዝለቅ የቻለች ብቸኛ ኃያል እርስዋ እንደኾነች ማንም አይክደውም፤ ቤተ ክርስቲያናችን ይህ ጽናቷ በአፍሪቃ ክፍለ ዓለም እና በኦሪየንታል አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ የቁጥር አንድ ደረጃን፣ በአጠቃላይ በኦርቶዶክሱ ዓለም ደግሞ በታሪክና በዶግማ ባይኾንም በቁጥር ብቻ ከሩስያ ቤተ ክርስቲያን ቀጥላ የቁጥር ኹለት ደረጃን ይዛ ትገኛለች፤ይህ ጥንካሬና ጸጋ በቀደምት ኢትዮጵያውያን ተጋድሎ የተገኘ ደማቅና አኩሪ ታሪክ መኾኑን ኦርቶዶክሳውያን ብቻ ሳይኾኑ መላ ኢትዮጵያውያን ሊያውቁት፣ ሊኮሩበት፣ ሊንከባከቡትና ሊጠቀሙበት የሚገባ የጋራ ሀብት ነው፡፡

ምክንያቱም፣ ኹሉም ኢትዮጵያውያን በዚህ ሀብተ ጸጋ ሲጠቀሙ ኖረዋል፤ አሁንም እየተጠቀሙ ነውና፤ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ካህናትና ምእመናንም ይህን ሐቅ ለኢትዮጵያውያን ኹሉ የማሳወቅ ሓላፊነት ስላለባቸው በዚህ ዙሪያ በሰፊው ሊሠሩበት እንደሚገባ ሳንመክር አናልፍም፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤

የዘንድሮ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ ልዩ የሚያደርገው፣ ቤተ ክርስቲያናችን ሐዋርያዊ ተልእኮዋን በአግባቡ እንዳትወጣ ዕንቅፋት ኾኖ የቆየው የመለያየት ጠንቅ ተወግዶ፣ በምትኩ አንድነትዋ ገሐድ ኾኖ በምሕረተ እግዚአብሔር በተጎበኘችበት ወቅት የሚካሔድ ጉባኤ መኾኑ ነው፡፡

ይህን ዕድል በመልካም ጎኑ የምንመለከተው ኾኖ፣ በተቃራኒው ደግሞ ቤተ ክርስቲያናችን በከፋ መልኩ የተደፈረችበት፣ ካህናቶቻችንና ምእመናን ልጆቻችን ለሰው ኅሊና በሚከብድ ድርጊት በአሠቃቂ ጭካኔ የሰማዕትነት ጽዋ በተቀበሉበት ማግሥት የሚካሔድ ጉባኤ መኾኑ ነው፡፡

በመኾኑም፣ ከዐሥር ዓመታት በፊት በጂማና በኢሉባቦር አህጉረ ስብከት፣ በጉራጌና በአርሲ ነገሌ፣ በቅርቡም በባሌ ተቃጥቶ በነበረው አደገኛ ሙከራ፣ ከኹሉም የባሰ ደግሞ በሶማሌ ሀገረ ስብከት የተፈጸመው ጣራ የነካ ግፍና ጭካኔ፣ እልቂትና ውድመት ቤተ ክርስቲያናችንን ክፉኛ የጎዱና የተዳፈሩ ኾነው ተገኝተዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ችግሩ ወደ ሌሎችም እንዳይስፋፋና የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል በከፍተኛ የሓላፊነት ስሜት ሐዘንዋን በልብዋ አምቃ ለማለፍ ብትሞክርም፣ ድፍረቱ ከቀን ቀን እየባሰ፣ ዕልቂቱም እየጨመረ፣ ተጽዕኖው እየተባባሰ በመሔዱ ልትታገሠው ከማትችልበት ደረጃ እየደረሰ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ለኢትዮጵያውያን ኹሉ በፊደልዋ ማዕድ ዕውቀትን እየመገበች፣ በታቦትዋ አዝማችነት ለነጻነትና ለወገን ክብር መተኪያ የሌለው መሥዋዕትነት እየከፈለች፣ የኹሉንም እምነቶች ነጻነት ሳትጋፋ፣ አንዱን እንኳን ሳትጫንና ክብሩን ሳትነካ በሺሕ ለሚቆጠሩ ዘመናት እንዳልዘለቀች ኹሉ፣ ዛሬ በኢትዮጵያውያን ወገኖችዋ ስትቃጠል ማየት አሳፋሪና የድፍረት ድፍረት ነው፤ የቤተ ክርስቲያናችን ተከታይ ምእመናንና አገልጋይ ካህናት በነጻነት የማስተማር፣ የማምለክና የመኖር ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን በሚቃረን አኳኋን በሚደርስባቸው ተጽዕኖ ከቀዬአቸው እየተፈናቀሉ እንዲወጡና ሃይማኖቱ እንዲዳከም የሚደረጉ ደባዎች እየተበራከቱ ነው፡፡

ይህ ኹሉ እየኾነ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ለካህናትና ለምእመናን አስተማማኝ የኾነ መፍትሔ አበጅቶ ዘላቂ ዋስትና የማያረጋግጥ ከኾነ በታሪክና በእግዚአብሔር ዘንድ ተወቃሽ መኾኑ አይቀርም፤ በመኾኑም ቅዱስ ሲኖዶስ ይህን መሰሉ ችግር ተወግዶ ካህናትና ምእመናን ያለምንም ተጽዕኖና ስጋት በነጻነት ሥርዐተ አምልኳቸውን የሚፈጽሙበትና የመኖር መብታቸው የሚከበርበት ድባብ ለመፍጠር በየአካባቢው ጠንካራ የግንኙነት መረብ ዘርግቶ የቅድመ ትንበያ ሥራ በመሥራት፣ እንደዚሁም ከፍትሕና ከጸጥታ አካላት ጋራ በቅንጅት በመሥራት፣ በቤተ ክርስቲያንና በአማንያን ላይ የሚሰነዘረውን ጥቃት አስቀድሞ ማምከን የሚቻልበትን አሠራር መቀየስ የግድ ይላል፡፡

ያለንበት ወቅት፣ ሀገራችን በብሩህ ተስፋና በስጋት መንታ መንገድ ላይ የቆመችበት ጊዜ እንደኾነ በግልጽ የሚታይ ነው፡፡ በመኾኑም ስጋቱ ተወግዶ ብሩህ ተስፋው ብቻ እንዲፈነጥቅ፣ ቀጣዩ ዘመን ለሕዝባችን ወንድማማችነትና እኩልነት፣ ለሀገር አንድነትና ለዜጎች ደኅንነት ያለዕረፍት ድምፃችንን ከፍ አድርገን የምንሰብክበት፣ ከማንም የፖሊቲካ ርእዮተ ዓለም ገለልተኛ በመኾን በአስታራቂነት ብቻ የምንቆምበት ጊዜ እንደኾነ መገንዘብ ይኖርብናል፡፡

እኛ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፣ ካህናት፣ መምህራንና ሰባክያን የኹሉም ፖሊቲከኞች አባቶች መኾናችን አውቀን ኹሉንም በአባትነት መንፈስ መመልከት፣ ማስተማርና መምከር እንጅ አንዱን አግልሎ ሌላውን አቅርቦ ማየት፣ ከሃይማኖት አስተምህሮ ጋራ የማይሔድ ስለኾነ ልንጠቀቅበት ይገባል፡፡

የቤተ ክርስቲያናችንን አስተዳደር ክፉኛ እያስተቸ ያለው የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የሀብት አያያዝ ክፍተት፣ የምእመናን ፍልሰት፣ የተልእኮ ሐዋርያት አለመጠናከር፣ በውስጥም በውጭም ከቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውጭ በግላቸው አስተዳደራዊ መዋቅርን ከላይ እስከ ታች እየዘረጉ ቤተ ክርስቲያንን የሚጋፉ ልዩ ልዩ ማኅበራት፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን በሚፈቅደው መሠረት፥ በሕግ፣ በመሪ ዕቅድ፣ በፖሊሲ፣ በደንብና በመመሪያ መልክ እያስያዙ የቤተ ክርስቲያንን ሉዓላዊነት፣ አንድነት፣ ክብርና መብት መጠበቅ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያናችን አጠቃላይ አሠራር የዘመነና የሠለጠነ፣ ግልጸኝነትና ተኣማኒነት ያሰፈነ፣ በልጆቻችን ምእመናን ዘንድ አድናቆትን፣ ተቀባይነትንና ይኹንታን ያተረፈ እንዲኾን ለማድረግ ኹሉን የቤተ ክርስቲያን ሥራዎች ያካተተ፣ ጥልቅና ችግር ፈቺ የኾነ፣ ሰፊና ረዥም ጊዜ የሚያገለግል መሪ ዕቅድ የሚዘጋጅበት መደላድል መፍጠር አለብን፤ ይህም ጊዜ ሳይወስድ በፍጥነት ተሠርቶ ለቀጣዩ ስብሰባ እንዲቀርብ ዛሬ መወሰን አለብን፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን የተዋጣለት መሪ ዕቅድ ሲኖራት፣ በርግጠኝነት ኹሉንም ችግሮች ተቋቁመን የተሻለ ልማትና ዕድገትን በኹሉም አቅጣጫ እናስመዘግባለን፤ የምንጓዝበትን ፍኖተ ምሕዋርና የምንደርስበት ጫፍም በትክክል ማወቅ እንችላለን፤ ፈጣን፣ ሐዋርያዊ፣ መንፈሳዊ፣ አስተዳደራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትንም እናስመዘግባለን፡፡

ስለኾነም፣ የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደራዊ ችግርን ለመፍታት የምንችለው በመሪ ዕቅድ በመመራትና መልካም አስተዳደርን በማበልጸግ እንደኾነ፣ ከዚህ ውጭ ግን ሌላ አማራጭ ሊኖር እንደማይችል መገንዘብ ይኖርብናል፡፡

ሌላው በዚህ ጉባኤ ሳናነሣው የማናልፈው ዐቢይ ነጥብ፣ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ነው፤ የታሪክ አጋጣሚና የትውልድ ዕድል ጉዳይ ኾኖ አሁን ላለንበት ኹኔታ ብንዳረግም፣ ከኢትዮጵያ የተነጠለ የኤርትራ ታሪክ፣ ከኤርትራ የተነጠለ የኢትዮጵያ ታሪክ ፍጹም እንደሌለ እኛ ብቻ ሳንኾን ዓለም በሙሉ የሚያውቀው ሐቅ ነው፡፡

ከጅምሩም ግራና ቀኛችን በሚገባ አርቀን ካለማየታችን የተነሣ ለጊዜው ተለያይተን ቆየን እንጅ የሚለያየን ሃይማኖታዊም ኾነ ቀኖናዊ ምክንያት የለንም፤ ምድራዊ መንግሥት በፖሊቲካ ምክንያት ቢለይም እንኳ፣ ለሃይማኖት ድንበር ስለሌለው በአንድነት እየተደጋገፍን መቀጠል ይገባን ነበር፡፡

ይህ እውነታ፣ ለእኛ ለኦርቶዶክሳውያኑ ባያድለንም፣ ሌሎች መሰል አብያተ ክርስቲያናት ግን እስከ አሁን ጠብቀውት እንዳለ ማየት እንችላለን፤ ነገር ግን፣ ላለፈው ክረምት ቤት አይሠራም እንደሚባለው ያለፈውን ለታሪክ ትተን፣ ለወደፊቱ ተጋግዘን፣ ተረዳድተንና ተደጋግፈን፣ የጋራችን የኾነ ሃይማኖትን፣ ታሪክና ባህልን ጠብቀን በማስጠበቅ፣ ኦርቶዶክሳዊውን ሕዝብ ማገልገል እግዚአብሔርና ታሪክ የጣሉብን አደራ መኾኑን መገንዘብ አለብን፡፡

እውነቱን ለመናገር፣ ለኢትዮጵያ ምእመናን ከኤርትራ ምእመናን፣ ለኤርትራ ቤተ ክርስቲያን ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የበለጠ የክፉ ቀን ደራሽ የላቸውም፡፡ በመኾኑም፣ በሁሉም ሃይማኖታዊ የሥራ መስክ ተቃርቦ ለመሥራት ቅዱስ ሲኖዶስ ዝግጁነቱን መግለጽ ይኖርበታል፤ በኹለቱም አብያተ ክርስቲያናት የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖር የጋራ ኮሚሽን አቋቁመን መንቀሳቀስ ይኖርብናል፤”

በመጨረሻም፤

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ፣ ከላይ በዝርዝር የተጠቀሱትን አንገብጋቢ የአገርና የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮችን አንድ በአንድ ተመልክቶና በጥልቀት መርምሮ አገራችንንና ቤተ ክርስቲያናችንን የሚጠቅሙ ውሳኔዎችን ያሳልፍ ዘንድ፣ እንደዚሁም የቤተ ክርስቲያናችንን የቀደመ ክብርና ሞገስ፣ ሉዓላዊነትና አንድነት ጠብቆ ያስጠብቅ ዘንድ ከማሳሰብ ጋራ የጥቅምቱን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በጸሎት መከፈቱን በእግዚአብሔር ስም እናበሥራለን፡፡