የግብፅ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃነጳጳሳትና የምእመናን ልኡካን ቡድን በሊቢያ አሸባሪ ቡድን የተሰውትን ሰማዕታት ቤተሰቦች አፅናኑአቸው!!

2284

ብፁዕ አቡነ የሱፍ በሰሜን አሜሪካ የግብፅ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ቢመን በግብፅ የናካዳ እና ቆስ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ካራስ በግብፅ የማሓላዘኮብራ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ እና ቁጥራቸው ከሃያ ያላነሱ ግብፃውያን ምዕመናን እሁድ ግንቦት 23 ቀን 2007 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ በመገኘት በሊቢያ በአሸባሪ ቡድን የተሰውትን ሰማዕታት ቤተሰቦች በወንጌል ትምህርት አፅናንተዋቸዋል፡፡
ከልዑካን ጳጳሳት መካከል ብፁዕ አቡነ የሱፍ በሰሜን አሜሪካ የግብፅ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀጳጳስ ፣ ሀዘንተኞችን አስመልክተው ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት “የግብፅና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመሠረታቸው አንድ ናቸው፡፡ በሁለቱም ሀገራት ልጆች በደረሰው አሰቃቂ ግድያ በጣም አዝነናል ያሉት ብፁዕነታቸው የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ከሆነው 1ኛ ተሰ 4፤13 ላይ “ነገር ግን ወንድሞች ሆይ ተስፋ እንደሌላቸው እንደሌሎች ደግሞ እንዳታዝኑ አንቀላፍተው ስላሉቱ ታውቁ ዘንድ እንወዳለን፡፡
ኢየሱስ እንደሞተና እንደተነሳ ካመን እንዲሁም በኢየሱስ ያንቀላፉትን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋልና፡፡” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አብራርተው ሀዘንተኞችን አጽናንተዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ የሱፍ አክለው እንደገለጹት በሊቢያ በአሸባሪ ቡድን ተሰውተው ሰማዕትነት በተቀበሉ ዘመዶቻችን እጅግ ብናዝንም ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረን ልንጽናና እንጂ ተስፋ ልንቆርጥ አይገባንም፡፡
ዘመዶቻችን በሰማይ የሚ-አገኙት የተሻለ ዋጋ ብቻ ሳይሆን ክብርም ጭምር ነው፡፡ የሰማዕትነትን ክብር የሚአህል ክብር የለም፡፡ የሰማዕታት ደም የክርስቶስ ደም ነው፡፡ ዘር በሚዘራበት ጊዜ ብዙ ሆኖ ያድጋል፡፡ የሰማዕታትም ደም የዚያን ያህል ነው፡፡
ሰይጣንና የአህዛብ ነገሥታት ክርስትናንና ክርስቲያንን ለማጥፋት ብዙ ጥረት አድርገዋል፡፡ ሰይጣን ተሳክቶለት ክርስቲያኖችን አሳርዶአል፡፡ ነገር ግን ክርስቲያኖች በሰማዕትነት ደም መልሰው ይገናኛሉ፡፡ ይህ ደግሞ በመላው ዓለም ያሉ ክርስቲያኖች ለተሰውት ዘመዶቻቸው ፍቅራቸውን ገልፀዋል፡፡ የእነዚህ ሰማዕታት ሕይወት ጎልቶ የሚወጣው በዘመዶቻቸው ነው፡፡

2219

እንደምታውቁት ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ከአንድ ሺህ ስድስት መቶ ዓመት በላይ በእምነት የተሳሰረ ሕይወት አላቸው፡፡ በማለት ሰፊ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡ በማያያዝም ከግብፅና ከአሜሪካ በመጡ ግብፃውያን ምዕመናን በቤተሰቦቻቸው መሰዋት ምን እንደተሰማቸው ጥያቄዎችን ያቀረቡላቸው ሲሆን የሰማዕታቱ ቤተሰቦችም በበኩላቸው ከግብፃውያን ጋር የደም ዝምድና የተፈጠረ መሆኑን በማብሰር ቤተሰቦቻቸው ቀደም ሲል ለሃይማኖታቸው የላቀ ፍቅር ያላቸው መሆኑን በመግለፅ በደረሰባቸው አሰቃቂ ግድያ በመንግሥተ ሰማያት ያላቸውን ዘለዓለማዊ ክብር በማሰብ ከሀዘናቸው መጽናናታቸውን አብራርተዋል፡፡
ይልቁንም የግብፅ ክርስቲያኖች ከመላው ዓለም በመምጣት ላደረጉት የማፅናናት ሥራ እጅግ በጣም ደስ ያላቸው መሆኑን አክለው ገልፀዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ማትያስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የ30 ሰዎች የሰማዕትነት ማዕረግ ሰጥቷል፡፡ የግብፅ ቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ደግሞ እንጠብቃለን፡፡ ክርስቶስ ወደ ሰማይ በሚአርግበት ጊዜ አፅናኙን እልክላችሁአለሁ ባለው ቃል መሠረት አፅናኙ መንፈስ ቅዱስ በወረደበት ዕለት ይህ የማፅናናት አገልግሎት መደረጉ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ በደንጊያ ሲወገር ለጠላቶቹ ጸልዮአል፡፡ በዚህም የመጀመሪያ ሰማዕት ለመሆን በቅቷል፡፡ የእናንተም ልጆች የሰማዕትነትና ክብር በማግኘታቸው ደስ ሊላችሁ ይገባል በማለት ብፁዕነታቸው ሰፋ ያለ መልእክት ካስተላለፉ በኋላ በካናዳ ውስጥ ብሪቱሽ ኮለቢያ ከምትገኘው የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን የተላከውን የኢትዮጵያ ብር አርባ ዘጠኝ ሺህ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ በሊቀ ማዕምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የሀዘንተኞቹ አስተባባሪ ለሆኑት ለመምህር ዘመድኩን በቀለ ተሰጥቶ ገንዘቡ ወዲያውኑ ለአስር ሀዘንተኞች ተከፋፍሎአል፡፡
በተጨማሪም በግብፅ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃነጳጳሳት በኩል ለእያንዳንዳቸው ሀዘንተኞች አንድ ሺህ የአሜሪካ ዶላር ተለግሶአቸዋል፡፡
በመጨረሻም የግብፅ የጳጳሳትና የምዕመናን ቡድን ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ጋር ሰፋ ያለ ውይይት አካሄደዋል፡፡ ልዑካኑ በዚህ በተቀደሰው በመንፈስ ቅዱስ ቀን እንዲህ አይነቱን ሐዋርያዊ ተግባር በማከናወናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል፡፡
ከዚያም በማያያዝ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የሁለቱን አብያተ ክርስቲያናትና የምዕመናኑን ሕብረት ገልፀው ልዑካኑ ለዚህ ቅዱስ ተግባር ወደ ኢትዮጵያ በመምጣታቸው የተሰማቸውን ደስታ አብራርተዋል ከዚያም በማያያዝ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አዘጋጅነት የእራት ግብዣ ተደርጎ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኖአል፡፡

{flike}{plusone}