የጃንሜዳ ባህረ ጥምቀት ምዕራፍ አንድ የግንባታ ሥራ ተጠናቆ ለበዓል አከባበር ሥርዓቱ ዝግጁ ሆነ
ከአንድ ወር በፊት የ2014 ዓ.ም የጥምቀት በዓልን በማስመልከት በዘመናት አገልግሎት ምክንያት በእጅጉ ተጎሳቁሎ የነበረውን የጃንሜዳ ባህረ ጥምቀትን ለማደስ በተደረገው እንቅስቃሴ በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔና በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አሳሳቢነት የግንባታ ሥራው የተጀመረው የጃንሜዳ ባህረ ጥምቀት ምዕራፍ አንድ የግንባታ ሥራ መጠናቀቁና ለጥምቀት በዓል ዝግጁ መሆኑ ታውቋል።
በምዕራፍ አንድ የግንባታ ሥራ ከተከናወኑት ተግባራት መካከል የባህረ ጥምቀቱን ገንዳ በአዲስና ዘመናዊ መንገድ የመገንባት፣ የኤሌክትሪክ እና የውኃ መስመር ዝርጋታ ሥራዎች እንዲሁም ቅጽረ ጊቢውን የማስዋብና ቡራኬ ማከናወኛ ስፍራዎችን የማስጌጥ ሥራዎች በሚገባ ተከናውነዋል።ከዚሁ ጋር በተያያዘም የጸበል መርጫ መስመሮች የተገጠሙ ሲሆን ብቃት ያላቸው የውኃ መሳቢያ ሞተሮች ገጠማም ተከናውኖ ዝግጁ መሆኑን የማረጋገጥ ሥራም ተከናውኗል።
በአጠቃላይ የዘንድሮን የጥምቀት በዓል በጥሩ ሁኔታ ለማክበር የሚያስችሉ የግንባታ ሥራዎች፣ የታቦታት ማረፊያ ቦታዎች፣ የክብር እንግዶች የሚስተናገዱባቸው መድረኮችና የድምጽ ማጉያ መስመር ዝርጋታዎች ተከናውኗል።
ቀሪ የግንባታ ሥራዎችና ይዞታውን የማስከበር ተግባራትም በዓሉ ከተከበረ በኋላ ተጠናክረው መቀጠል ይችሉ ዘንድ አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተሠርተዋል።
ምንጭ፦የኢኦተቤ ህዝብ ግንኙነት ፌስቡክ ገጽ
በተክለሃይማኖት አዳነ ጋዜጠኛ
ለተጨማሪ መረጃ የሀገረ ስብከቱን ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ይጎብኙ፣ like እና Join በማድረግ ይቀላቀሉ፣ ለሌሎችም ሼር ያድርጉ!!!
- ድረ-ገጽ:- www.addisababa.eotc.org.et
- ፌስ ቡክ ገጽ:- www.facebook.com/AddisAbabaDiocese/
- ተሌ ግራም ቻናል:- t.me/AddisAbabaDiocese