የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም ከፍተኛ የአብነት ትምህርት ቤትና የዕጓለ ማውታና አረጋውያን መጦሪያ ምትክ ቦታ የወሰን ችካል ተከላ ተከናወነ
የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም ከፍተኛ የአብነት ትምህርት ቤትና የዕጓለ ማውታና አረጋውያን መጦሪያ ምትክ ቦታ የወሰን ችካል ተከላ ተከናወነ።
በሊቀ ሊቂውንት አባ ገብረ አብ በኋላ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ አስተባባሪነት በ፲፱፻፳፭ ዓ/ም ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ላለፉት ፺፪ ዓመታት ለኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን በርካታ ሊቃነ ጳጳሳትንና እንዲሁም ሊቃውንትን እያበረከተ የሚገኝ ታላቅ የትምህርት ማእከል ነው።
ገዳሙ ከትምህርት ቤቱ ጎን ለጎን የዕጓለ ማውታና የአረጋውያን መጦሪያ (ጡረታ ቤት) በመኖሩ ብዙ ሕጻናትን እንደእናትና አባት አሳዳጊ፤ የደከሙ አረጋውያንን እንደልጅ ጧሪ በመሆን እያገለገለ መቆየቱ ታሪኩ ያስረዳል።
ይሁንና በመንግሥት የኮሪደር ልማት አማካኝነት ጥንታዊው ትምህርት ቤት ከነበረው 10,248 ካሬ ሜትር ሙሉ ይዞታ በመንገዱ ፊት ለፊት 2,935 ካሬ ሜትር እንዲሁም የጡረታ ቤቱ 2,456 ካሬ ሜትር በኮሪደር ልማቱ መፍረሱ ተገልጿል።
በመሆኑም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ሐላፊዎች ከገዳሙ አስተዳዳር ጋር በመሆን ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር የተወያዩ ሲሆን በፈረው ቦታ ምትክ እንዲሰጥ ስምምነት ላይ መደረሱም ተነግሯል።
ትምህርት ቤቱ በመንገድ ፊት ለፊት ለተወሰደበት 2935 ካሬ ቦታ በትምህርት ቤቱ በጀርባ በኩል ወይም በስተምሥራቅ በኩል በፈረሰው ቦታ ምትክ (2935 ካሬ ሜትር) በዛሬ ዕለት የወሰን ችካል ተከላ ከክፍለ ከተማው በመጡ ባለሙያዎች ተከናውኗል።
በተመሳሳይ የገዳሙ የዕጓለ ማውታና አረጋውያን መጦሪያ (ጡረታ ቤት) በፈረሰው 2456 ካሬ ሜትር ቦታ ምትክ ከዋናው አስባልት መንገድ በቀረበ በመልኩ የተሰጠ ሲሆን በምትክነት በተሰጠው የ2456 ካሬ ሜትር የወሰን ችካል ተካላ መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት ተከናውኗል።
በምትክነት በሰጠው የገዳሙ ቦታ ተገኝተው ጉብኝት ያደረጉት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ እዚህ ደረጃ ለመድረስ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር በርካታ ውይይቶችና ምክክሮች መደረጋቸውን አስታውሰዋል።
አክለውም በተሰጠው ቦታ የወሰን ችካል መቸከሉ ጥሩ ውጤት መሆኑን ገልጸው በቀጣይ በሚደረጉ የታላቁ ትምህርት ቤት ዕድገትና ተግባራት ሁሉም ሊተባበር እንደሚገባ አሳስበዋል።
በመንግሥት በኩል ለተደረገው ለእስካሁኑ መልካም ትብብርና ድጋፍ አመስግነው በቀጣይ የሁለቱም ቦታዎች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተዘጋጅቶ በቅርብ ቀናት ለገዳሙ እንደሚሰጥና በገዳሙ ጥንታዊ ትምህርት ቤት ቀጣይ እንቅስቃሴም ድጋፍን እንደሚያደርግ ይጠበቃል ሲሉ ገልጸዋል።
የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት አሳሳቢነት እንደታነጸና በታኅሣሥ ፫/፲፱፳ ዓ/ም በእጨጌ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቡራኬ ቅዳሴ ቤቱ እንደተከበረ ከገዳሙ የተገኘው ታሪክ ያስረዳል።
©የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ