የደብረ ታቦር በዓል በደብረ ምጥማቅ ሰአሊተ ምሕረት ካቴድራል በደማቅ ሁኔታ ተከበረ!!

0498

በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን የሚከበረው የደብረ ታቦር በዓል በዘንድሮው 2007 ዓ.ም በሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ከቀኑ 11፡00 ጀምሮ በልዩ ሥነ ሥርዓት ተከብሯል፡፡
በበዓሉ አከባበር ወቅት ፕንግ ድርብ (ልብሰ ያሬድ) የለበሱ የአብነት ተማሪዎች “አሀደ ለከ ፣ ወአሀደ ለሙሴ ፣ ወአሀደ ለኤልያስ፣  ንግበር ማህደረ” የሚለውን የወንጌል ቃል በዜማ ያቀረቡ ሲሆን በተመሳሳይ የደብሩ የሰንበት ት/ቤት መዘምራን አማን በአማን ተሰብሐ በደብረ ታቦር የሚል ዝማሬ አሰምተዋል፡፡ በካቴድራሉ ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በዓሉን የተመለከተ ድራማ ቀርቧል፡፡ የበዓሉን ሥነ -ሥርዓት ለመከታተል የመጣው ምዕመናን ቁጥር ከ30,000 ሺህ በላይ  ይገመታል፡፡ የአካባቢው ክፍለ ከተማ የሥራ ኃላፊዎችም የበዓሉን ታላቅነት ግምት ውስጥ በማስገባት በካቴድራሉ ተገኝተዋል፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ በበዓሉ ላይ ተገኝተው የሚከተለውን መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን በሕይወት እንድንኖር የፈቀደልን እኛ ስለጠየቅን ብቻ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የጠየቁትን ስለማይረሳ ነው፡፡ እምቢም አይልም ሁሉንም በደስታ እንድናደርገው ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር የሚፈልገው እኛ ደስ እንዲለን ነው፡፡በዚህ ሰዓት ፣ በዚህ አውደ ምሕረት ላይ ተሰብስበን ስንታይ እንዴት እናምራለን? ስለዚህ ለአምላካችን ለእዚአብሔር ክብርና ምስጋና ይድረሰው!!
የዚህ ቦታ ስፋት ከሁለት መቶ ሺህ ካሬ ሜትር በላይ ነው ይሁን እንጂ እግዚአብሔርን የምናምን ሰዎች ሞልተነው ቦታው ጠቦን ይታያል፡፡ በዓለም ላይ ያለነው ክርስቲያኖች እኛ ብቻ አይደለንም ፤ ነገር ግን ነጫጭ ልብሳችንን ለብሰን በእምነት አደባባይ የተገኘንና የታየነው እኛ ብቻ ነን፡፡ በዚህም የእግዚአብሔር ሕዝቦች መሆናችን ይታወቃል፡፡
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር እንደተገኘ ፣ ሙሴና ኤልያስም ከነበሩበት ቦታ ተመልሰው እንደመጡ ፣ ቅዱስ ጴጥሮስም ለነሱ ቤት ለመሥራት ፍላጎት እንዳሳየ ፣ በመጽሐፍ የምናነበው እኛ ብቻ አይደለንም፤ ሁሉም ሰው ያነበዋል፡፡ ነገር ግን በዚህ ባማረ ሁኔታ የሚያከብሩት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች ብቻ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር እኛን በሀብት ሳይሆን ፣ በሌላ መለኪያ ሳይሆን ፣ በእምነት የእርሱ እንድንሆን ስላደረገን ክብርና ምስጋና ይግባው ፤ እንደዚህ እንደተገኘን ሁልጊዜም ለቤተ ክርስቲያን ማሳብ ይገባናል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ዕለት ዕለት የሚያሳስበኝ የአብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ ነው ብሎ እንደገለጸው በዚህ ዘመን የቤተ ክርስቲያን ድምፅ የሚመስል ያላቸው ሰዎች አብረውን አሉ ፤ እነዚህ ክፍሎች የቤተ ክርስቲያናችንን ፈተና አብዝተውታል ፤ እኛ እስከ አሁን ድረስ የቆየነው የአባቶቻችንን እግር ጠብቀን ነው ፤ የእነሱን ትምህርት ተምረን ነው፤ እነሱ ያስተማሩንን ደግመን ነው ፤ ይህንን እንድንጠራጠረው የሚያደርግ አዲስና እንግዳ ትምህርት ይዘው የተቀላቀሉን በርካቶች ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ እንዲጠፉ አንመኝም ፤ ነገር ግን ልብ እንዲሰጣቸው እግዚአብሔርን እንጠይቃለን፡፡

0472

በመንፈስ ቅዱስ መንበር ላይ የተቀመጡትን ቅዱሳን አባቶቻችንን ፣ የሚባርኩንን ፣ ክህነት የሚሰጡንን ፣ የሚያቆርቡንን ካህናት  እንድንጠራጠራቸው ግፊት የሚያደርጉ በጣም በርካታ ሰዎች በከተማው ውስጥ አብረውን አሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያን ስም ብዙ ነገር ይናገራሉ ፤ በቤተ ክርስቲያን ስም እንግዳና አዳዲስ ትምህርት ያሰራጫሉ ፤ የሚያስደነግጥና ጥርጣሬን የሚፈጥር ትምህርት ለማስተማር ይሞክራሉ ፤ ጥረትም ያደርጋሉ፡፡
ስለዚህ ልባችን ሳይደነግጥ የአባቶቻችንን እግር ብቻ ተከትለን ፤ በእጃችን ላይ ያለውን ሞባይል ሳይሆን የቤተ ክርስቲያንችንን ድምጽ ብቻ ሰምተን እንድንኖር መትጋት ያስፈልገናል፡፡  በአሁኑ ሰዓት በጣም ብዙ ነገር ነው የምንሰማው ፤ ሊቃነ ጳጳሳቱን፣አስተዳዳሪዎችን፣ንስሐ አባቶቻችንን እንድንጠራጠር የሚአደርጉ ግለሰቦች አሉ፡፡
ስለዚህ ክፉውን ከበጎው እንድንለይ እግዚአብሔር ልቡናውን ይስጠን ለሚቀጥለው ዘመን እግዚአብሔር በሰጠን ጊዜ ፣ እግዚአብሔር በሰጠን የሥራ ቦታ አገልግለነው ቤተክርስቲያናችንን በተሻለ ቦታ ላይ አግኝተናት፣  ደስ ብሎን እንድናገለግል መትጋት ያስፈልጋል ፤ መሰብሰብ ብቻ በቂ አይደለም፡፡
እግዚአብሔርን የሚያስደስተው ሥራ ነው ፤ የሰው ልጅ ወደዚህ ዓለም የመጣበት ዋና ዓላማ እንዲሠራ ነው ፤ ሠርተህ ኑር ተብሎ ነው ወደዚህ ዓለም የመጣው፡፡
ይህን ካቴድራል እንደሞዴል መውሰድ እንችላለን ፤ ቤተ ክርስቲያኑ ከተመሠረተ በጣም ረጅም ዕድሜ አለው ፤ በዚህ አሁን በምናየው መልኩ ከፀዳ ፣ ካማረና ከተዋበ ግን ቅርብ ጊዜው ነው ፤ በዚያኛው ዘመን የነበሩት አባቶች በጊዜአቸው ሠርተዋል፤ አሁን የሚሠራው ግን እጅግ የተሻለ ነው ፤ በዚህ ምክንያት የምንሰበሰብ ሰዎች ቁጥራችን ብዙ ሆኖአል ፤ ይህንን የሥራ ጊዜ ፣ ይህንን የሥራ ትጋት ፣ ለወንድሞቻችን ፣ ለእህቶቻችን ፣ እዚህ ለሚያገለግሉ ካህናት ሁሉ የሰጠ እግዚአብሔር ክብርና ምስጋና ይገባዋል!!
ስለዚህ የሥራ ፍላጎታችንን አጠናክረን መቀጠል አለብን፤ የምንቆምበት ሜዳ ፣ የምንቀመጥበት ወንበር ብቻ ሳይሆን አባቶቻችን የሚኖሩበት አካባቢ እንደዚህ ጽዱና ያማረ መሆን አለበት፡፡ በዚህ ካቴድራል የተጀመረው የአብነት ትምህርት በየአጥቢያው እንዲስፋፋ ተግተን መሥራት ይኖርብናል፡፡
ስለዚህ እዚህ የተገኘን ሁላችን ይህንን ኃላፊነት ተጋርተን መሄድ አለብን ፤ መሥመራችንን እንዳንስት የቤተ ክርስቲያናችንን ድምጽ ሰምተን መጓዝ አለብን ፤ አምላካችን እግዚአብሔር ለሚቀጥለው ዓመት እንደሚያደርሰን አንጠራጠረውም፤ እስከዛሬ ድረስም የቆየነው በጉብዝናችን ሳይሆን እርሱ ስለጠበቀን ነው፡፡
ስለዚህ በሚቀጥለው ዓመት እግዚአብሔር ጠብቆን በዚህ መድረክ ላይ ሲያገናኘን ዛሬ የምንገባው ቃል ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጌአለሁ የምንልበት እንዲሆን ያስፈልጋል ፤ እኛ የእግዚአብሔር ንብረቶቹ ነን ፤ ልንጠራም እንችላለን፡፡
ለቤተ ክርስቲያን መሻሻል ጉልበታችንን ፣ ዕውቀታችንን ልንሰጥ ይገባናል ፤ ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን ይዘዋቸው የገቡ አጓጉል አስተሳሰቦች ፣ አጓጉል አሠራሮች ፣ እግዚአብሔር የማይወዳቸውና የቤተ ክርስቲያን ያልሆኑ ነገሮች እንዲወገዱ ልንተባበር ይገባናል ፤ ይህንን እናስተካክልላችሁአለን ከሚሉ እና ከመዋቅር ውጪ ከሚኖሩ ሰዎች እንዳንተባበር አደራ እላለሁ፤ ሰለጠን የሚሉ ሰዎች ቤተ ክርስቲያንን የትም አላደረሷትም ፤ ኋላ ቀር እየተባሉ የሚሰደቡ አባቶቻችን ግን ቤተ ክርስቲያናችንን ከነክብሯ ጠብቀው እዚህ አድርሰውልናል ፤  ሥርዓትና እምነት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊአስገባን ይችላል ፤ እኛ ብዙ ነንና እኛን ስሙን ከሚሉ ሰዎች ራሳችንን ልንጠብቅ ይገባል፡፡
 ዘመኑ የፈጠራቸው እኛ የምንገለገልባቸው ነገሮች ሁሉ ለመጥፎ ነገር እየዋሉ ስለሆነ የቤተ ክርስቲያንን ድምጽ ብቻ መስማት አለብን በማለት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ሰፋ ያለ መልእክት ካስተላለፉ በኋላ ከምዕመናን የተሰበሰበው የችቦ ደመራ ተለኩሶ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኖአል፡፡    {flike}{plusone}