የደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ደብር በልማትና በሰላም መስፈን አርአያነት ያለው ተግባር እያከናወነ መሆኑ ተገለጸ
“ወርሐዊ የገንዘብ ገቢው በእጥፍ አድጓል”
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥር የሚገኘው የደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ደብር በልማት ሥራዎች፣ በመልካም አስተዳደር ተግባርና በሰላም መስፈን ላቅ ያለና አርአያነትን የሚያሳይ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡
በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ቀደም ሲል ተፈጥሮ በነበረው አለመግባባት የልማት እንቅስቃሴው ተዳክሞ የነበረ ሲሆን በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ያላሰለሰ ጥረትና ክትትል በአሁኑ ጊዜ ሰላም ሰፍኖአል፣ የልማቱ እንቅስቃሴው አንሰራፍቶአል፣ በዕለት፣ በሳምንት እና በወር ከምዕመናን የሚገባው የገንዘብ መጠንም በእጥፍ አድጓል፡፡
የሀገረ ስብከታችን የሚዲያ ክፍል አርብ ታህሳስ 22 ቀን 2008 ዓ.ም ከቦታው ድረስ በመሔድ የደብሩ አስተዳዳሪ የሆኑትን መልአከ ብርሃናት ዘመንፈስ ቅዱስ ገ/አምላክን እና የደብሩ ዋና ጸሐፊ የሆኑትን ሊቀ ስዩማን ኃይለ ሚካኤል ወሰኔን በማነጋገር የሚከተለውን ሙሉ ሐሳብ አቅርበናል፡፡
ሥራ ባቆሙ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ አባላት ምትክ ከሀገረ ስብከቱ ሁለት፣ ከነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አንድ፣ በድምሩ ሦስት የሰላም ልዑካን ከአዲሱ የደብሩ የሥራ አመራር ጋር በመሆን፣ በመውጣት በመውረድ፣ በመጣርና በመጋር የመጀመሪያ ሥራ የተደረገው የትርምስ ማስወገድ እና የሰላም ማስፈን ተግባር ነው፡፡
ሰላም የበረከት ሁሉ መገኛ እንደመሆኑ መጠን የሰላሙ መስፈን ተግባር ከተረጋገጠ በኋላ በአንድ ግለሰብ እጅ ስር ወድቆ የነበረውን የደብሩን ይዞታ ለማስከበር፣ የደብሩ የሥራ አመራር ለሀገረ ስብከቱ ባቀረበው አቤቱታ መሠረት ሀገረ ስብከቱ ለክቡር አቶ ደሪባ ኩማ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ከንቲባ አቤቱታ በማቅረብ በከንቲባው በኩል ለአዲስ አበባ መሬትና ልማት ማናጅመንት መመሪያ ተላልፎ በክትትል ላይ ይገኛል፡፡
ይህም ሒደት ለምዕመናኑ ተገልጾ አስፈላጊ የሆነው ድጋፍ እየተደረገበት ነው፡፡ በራሳቸው ፍቃድ ሥራቸውን አቁመዋል የተባሉትን የሰበካ ጉባኤው አባላትን አስመልክቶ ጉዳዩን ለደብሩ ዋና ፀሐፊ ባቀረብንላቸው ጥያቄ መሠረት በሚቀጥለው ጥር ወር 2008 ዓ.ም አዲስ የሰበካ ጉባኤ ይመረጣል፡፡
ለሰበካ ጉባኤ አባልነት መመረጥም ሆነ ማስመረጥ የሚችሉት በደብሩ ጽ/ቤት ከስድስት ወራት በፊት በአባልነት የተመዘገቡና በአጥቢያው ነዋሪ የሆኑ፣ የምርጫውም ሒደት በካርድ ሲሆን በደብሩ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ የመምረጥና ማስመረጡ ተግባር ይፈጸማል፡፡
ቀደም ሲል የነበሩት የሰበካ ጉባኤ አባላት የቃለ ዓዋዲውን መመሪያ አክብረው ባለመሥራታቸው ከኃላፊነት እንዲገለሉ ተደርጓል፡፡
የደብሩ ንብረቶች የሆኑ 21 ሱቆች ውላቸው አልፎ ስለነበርና ቀደም ሲል ለግለሰቦቹ የተሰጠው ውልም አስገዳጅነት የሌለው በመሆኑ ከግለሰቦቹ ጋር በመወያየትና በመመካከር ምንም ዓይነት ቅሬታ ሳይኖር ውላቸው ታድሷል፡፡
የሙዳዬ ምፅዋት ቆጠራን አስመልክቶ ቀደም ሲል ከሙዳዬ ምፅዋት በቆጠራ የሚገኘው ብር ከመቶ አርባ ሺህ እስከ ሁለት መቶ ሺህ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ከ430 ሺህ እስከ 450 ሺህ ተቆጥሮ በደብሩ ካዝና ገቢ ይደረጋል፡፡
የቆጠራውን ተግባር የሚከታተለው በአካባቢው የሚገኘው የንብ ባንክ ቅርንጫፍ ሲሆን የባንኩ ባለሙያዎች ገንዘቡን በማሽን ቆጥረው በደብሩ አካውንት ገቢ እንዲሆን ያደርጋሉ፡፡ ልዩ ልዩ ቋሚና አላቂ ንብረቶችም በአግባቡ ተቆጥረው በሞዴል 19 ገቢ ከሆኑ በኋላ በሞዴል 22 ወጪ ተደርገው በኮሚቴ ተገምተው በሥራ ላይ ይውላሉ፡፡ በአገልግሎት ላይ የሚገኘው የደብሩ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ሕንፃው ያረፈበት ቦታ 10 ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን ቦታው የተገዛበት የሊዝ ክፍያ በውሉ መሠረት ክፍያው መጀመር የነበረበት ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን ነገር ግን እስከ አሁን ድረስ ለስምንት ዓመታት ያህል ምንም አይነት የሊዝ ክፍያ ሳይፈጽም በመዘግየቱ የደብሩ ዘመናዊ ትምህርት ቤት በሀራጅ ሽያጭ እንዲቀርብ በሀራጅ ፋይል ተራ ውስጥ ገብቶ ስለነበር አሁን ያለው የደብሩ የሥራ አመራር በደረሰው ጥቆማ መሠረት ወደ ክፍለ ከተማ ጽ/ቤቱ በመሔድና በመወያየት እስከ አሁን ድረስ ከደብሩ ውጪ 28 ሚሊየን ጠቅላላ የሊዝ ዕዳ ከሊዝ ጽ/ቤት ገቢ ሊሆን የሚገባው ብር አስራ አምስት ሚሊየን መሆኑን በመተማመንና በምክክሩ በመግባባት የመጀመሪያ ክፍያ ሦስት ሚሊየን ስምንት መቶ ሃያ ሺህ፣ በሁለተኛ ዙር ክፍያ አንድ ሚሊየን ሰባት መቶ ዘጠና ሺህ በድምሩ ከአምስት ሚሊየን ብር በላይ ያላነሰ ክፍያ ለሊዝ ዕዳ ተከፍሏል፡፡ ለዘመናዊ ትምህርት የግንባታ ሥራ የነበረበትን የብር አራት ሚሊየን ብድርም በየወሩ ከመቶ ሺህ ብር በላይ በመክፈል እዳው በማገባደድ ላይ ይገኛል፡፡
የቤተ ክርስቲያኑ ቅጽር ግቢ የሚገኘው አስፓልት ፈራርሶና አቧራው እየቦነነ ምዕመናንን ሲረብሽ የነበረውና ብሎም ወደ ኮረኮንችነት ተቀይሮ ያለውን የግቢ ሜዳ በተወሰነ ጥልቀት እንዲቆፈር ተደርጐ ደረጀውን የጠበቀ የአስፓልት ንጣፍ ለማድረግ አቶ ብርሃኑ የተባሉ በጐ አድራጊ በራሳቸው ተነሳሽነትና በግል ውጪ ለመሥራት ለደብሩ በደብዳቤ ጽፈው ባቀረቡት ጠያቄ መሠረት ሥራውን እንዲሠራ ከደብሩ አፋጣኝ ምላሽ በማግኘታቸው ሥራው ተጀምሮ ወደ ማለቂያው ደረጃ ደርሷል፡፡ ለሥራውም ከሁለት ሚሊየን ብር ያላነሰ ወጪ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የቀድሞ የአዲስ አበባ ባላደራ ከንቲባ የነበሩት የአቶ ብርሃኑ ድሬሳ ባለቤት የሆኑት ወ/ሮ ሥምረት አባተ የተባሉት በጐ አድራጊ የደብሩን ቢሮ ለማደስና ማቴሪያል ለማሟላት ቃል የገቡ ሲሆን ሥራውን ለመጀመር የፕሮፎርማ መሰብሰብ ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡
በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የውኃ እጥረት ያለ በመሆኑ ከከርሰ ምድር ውኃ ለማውጣት ደብሩ በጥረት ላይ ይገኛል፡፡
{flike}{plusone}