የዛሬው የ39ኛው የሰበካ ጉባኤ ስልጠና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት አስተባባሪነት በሳሪስ ም/ቅ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤ/ክ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ተካሄደ

በዛሬው ዕለት መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም የመ/ፓ/ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ ላዕከ ሰላም ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ዋና ክፍል ኃላፊ መልአከ ብርሃን ሳሙኤል ደምሴ፣ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሰ፣ የሀገረ ስብከቱና የክፍለ ከተማው የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ሥር የሚገኙ የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎች፣ ቁጥጥሮች፣ ሒሳብ ሹሞች፣ የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች እና የስብከተ ወንጌል ኃላፊዎች በተገኙበት በሳሪስ ምዕራፈ ቅዱሳን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤ/ክ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት አስተባባሪነት ተካሂዷል።
የመ/ፓ/ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ ላዕከ ሰላም ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ያበረከተችውን አስተዋጽኦ በዳሰሳዊ ጽሑፍ በሰፊው አብራርተዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሀገርን እንደ ሀገር ያቆመች እንደሆነች፣ሀገርንና መንግሥትን በጸሎት የምታስብ መሆኗን፣በመሠረተ ልማት፣ በኢኮኖሚው ዘርፍና በትምህርት እድገት በኩል ያበረከተችውን አስተዋጽኦ በሰፊው ገልጸዋል።
የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ምክትል አካዳሚክ ዲን መጋቤ ሐዲስ ጸጋው ወ/ትንሣኤ “ካህናትና የካህናት ተልዕኮ” በሚል ርዕስ ዳሰሳዊ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን ስለ ክህነት ምንነት፣ስለ ካህናት አገልግሎት ታሪካዊ ዳራ፣ስለ ካህናት ኃላፊነትና ተግባር፣ በ1ጢሞ ምዕ 3 ላይ በመመርኮዝ የካህናት መስፈርቶች ምን እንደሆኑ፣ የካህናት የመጀመሪያው አገልግሎት ወንጌልን መስበክ እንደሆነ፣ ትውልዱን በመልካም ስነ ምግባር ኮትኩቶ ማሳደግ፣ ከገዢነት መንፈስ ይልቅ በፍቅር መንፈስ ምእመናንን ማገልገል፣በዚህ ዘመን ያለው የካህናት ሕይወት ምን እንደሚመስልና ዛሬ ለቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጋት ካህን ሐቀኛና አገልጋይ መሆን እንዳለበት በሰፊው አብራርተዋል።
በመ/ፓ/ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ማስተባበሪያ ዋና ኃላፊ ሊቀስዩማን ወ/ሰንበት አለነ “መልካም እረኛና አስተዳደር”በሚል ርዕስ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ዋናው የካህን ሥራ እረኝነት እንደሆነ ገልጸው ነገር ግን በአሁን ጊዜ በአብዛኛው የእረኝነት አገልግሎት ተዘንግቶ አብዛኛው ካህን በአስተዳደር ሥራ ላይ መሠማራቱን ገልጸዋል። የመጀመሪያው የካህን አገልግሎት ለምእመናን ወንጌልን መስበክ፤ ምእመናንን መጠበቅ፤ ቀጥሎም የአስተዳደሩ ሥራ በሁለተኛ ደረጃ የሚከናወን እንደሆነ አብራርተዋል። አያይዘውም ምእመናን የሚጠይቁትን ጥያቄዎች በአግባቡና በወቅቱ መመለስ፣ ፍቅረ እግዚአብሔርንና ፍቅረ ቢጽን በትውልዱ ልቦና ውስጥ እንዲሰርጽ ማስተማር የካህን አገልግሎት እንደሆነ ገልጸዋል።
የመ/ፓ/ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ዋና ጸሐፊ ሊ/ካህናት ቁምላቸው ደረሰው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን “የሰበካ ጉባኤ አጀረጃጀት ትናንትናና ዛሬ” በሚል ርዕስ ስለ ሰበካ ጉባኤ ምንነት፣ስለ መንፈሳዊ ሰበካ ጉባኤ ታሪካዊ ዳራና ሰበካ ጉባኤ ለቤተክርስቲያን ቁልፍ የሆነ አስተዳደር መሆኑን አውስተዋል።
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ዋና ክፍል ኃላፊ መልአከ ብርሃን ሳሙኤል ደምሴ መርሐግብር መሪነት በቀረቡት ዳሰሳዊ ጽሑፎች ላይ ውይይት ተካሂዷል።
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሰ የክፍለ ከተማውን ጥሪ አክብረው በስልጠናው ላይ የተገኙትን የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎች፣ ቁጥጥሮች፣ ሒሳብ ሹሞች፣ የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች እና የስብከተ ወንጌል ኃላፊዎችን በሙሉ አመስግነዋል።
በመጨረሻም በአርቃቂ ኮሚቴ የአቋም መግለጫ ተነቦ መርሐግብሩ በጸሎት የተዘጋ ሲሆን መርሐግብሩ በሌሎች ክፍላተ ከተማ እንደሚቀጥልም ተገልጿል።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ