የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ስድስተኛውን የእምነትና ሥርዓት ዓለም አቀፍ ምክክር መርሐ ግብር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ ፓትርያርክ በተገኙበት በግብጽ አባ ቢሾይ ገዳም ማካሔድ ጀመረ

የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ስድስተኛውን የእምነትና ሥርዓት ዓለም አቀፍ ምክክር መርሐ ግብር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ ፓትርያርክ በተገኙበት በግብጽ አባ ቢሾይ ገዳም ማካሔድ ጀመረ።
የስደስተኛው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት የእምነትና ሥርዓት ዓለም ዓቀፍ ምክክር ጉባኤ ዋና ርእሰ ጉዳይ “የሚታየው አንድነት አሁን የት ነው?” በሚል ሲሆን ክርስቲያናዊ ኅብረትን ለማጠናከር የታሰበ ነውም ተብሏል።
በዚህ ከፍተኛ ትኩረት በሚሰጠው ኢኩሜኒካል እንቅስቃሴ ምክክር መርሐ ግብር ላይ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተሰባሰቡ የነገረ መለኮት ምሁራን፣ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፣ ወጣት ክርስቲያኖች የተገኙ ሲሆን በዋናነት ክርስቲያናዊ ኅብረትን እና አንድነት እንዴት በተግባር በተደገፉ መንገዶች መኖር እንደሚቻል ለጋራ ለመምክር እንደሆነም ተጠቁሟል።
በዚህ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን በመወከል የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የማኅበራዊና ኢኮኖሚ ዘርፍ ም/ሥራ አስኪያጅ ቀሲስ ረዳት ፕሮፌሰር ግርማ ባቱና የቅዱስ ሲኖዶስ ምክትል ጸሐፊ እና የሰሜን አፍሪካ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሃይማኖት ቆሞስ አባ አብርሃም ገረመው ተገኝተዋል ።
ጉባኤው በዋዲ ኤል ናርቱን፣ ግብፅ በአባ ቢሾይ ገዳም እየተካሄደ ሲሆን ከጥቅምት 14-18 ቀን 2018 ዓ/ም እንደሚቆይም ከወጣም መርሐ ግብር ለማወቅ ተችሏል።
የዓመት አብያተ ክርስቲያናት የመጀመሪያው መሥራች ጠቅላላ ጉባኤ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በአምስተርዳም በኦገስት 23 በ1948 ዓ/ም ሲካሄድ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሦስት መቶ ሃያ አንድ ተወካዮች ከ147 አብያተ ክርስቲያናት የተወከሉ ልዑካን ተገኝተዋል፡፡
በዚህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሰሐራ በታች ብቸኛዋ አፍሪካዊት መሥራች ቤተ ክርስቲያን እንደነበረች ታሪክ ያስረዳል።
ለዘገባው
WWC,
Ecuminical news
Coptic media center
north Afirca diocese የፌስቡክ ገጾች ዘገባዎችን ተጠቅመናል።