የወጣቶች እንቅስቃሴ
ስመ ጥር የሆነችው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ቀዳማዊትና ጥንታዊት፣ ሰማዊትና ሐዋርዊት፣ ብሔራዊትና ሉዐአላዊት፣ የሥልጣኔና የሥነ ምግባር ምንጭ ፣ የሕግና ሥነ ሥርዓት አውጭ፣ የተቀደሰ ባህልና ሥነ ጽሁፍ ባለቤት፣ የኪነ ጥበብና ተግባረ ዕድ፣ የታሪክና ቅርስ ባለቤት ሆና ለውዲቱ እናት ሀገራችን ጠብቃ አውርሳለች፡፡ስለሆነም የታሪክ አደራ ያለባቸው የዘመኑ ወጣቶች ተተኪዎችን ለማፍራት የአባቶቻቸውን አደራ እየተወጡ ይገኛሉ፡፡
በመሆኑም በ1930ዎቹ የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ከአባቶቻቸው የወረሱትን አሰራር ተከትለው በተለያዩ ማህበራት ስም ሲደራጁ የነበራቸው ዋና ዓላማ ትውልዱን አቀራርቦ አንድ ወጥ የሆነ ትውልድ ለመፍጠር ነበር፡፡ ይህን የመሰለ ትውልድ ለማምጣት ሰንበት ት/ቤቶች ባለፉት ዓመታት በአባቶቻቸው ሥር በመታዘዝ፣ ከሀገረ ስብከቱ መመሪያን በመቀበል፣ በሙሉ ዕውቀታቸው፣ ገንዘባቸውና ጊዜቸው መሰዋዕት ከፍሏል እየከፈሉም ይገናሉ በዚህ ተጋድሏቸው ምክንያትም ከመካከለኛው መ.ክ.ዘ በኋላ ቀዝቅዞ የነበረውን የሰብካተ ወንጌል መርሐ ግብር እንቀሳቅሰዋል፣ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ዘመናዊ በሆነ የትምህርት አሰጣጥ መንገድ ለወጣቱ ትውልድ እንዲዳረስ አደርገዋል፣ ልዩ ልዩ የትምህርት መጻህፍትን በማዘጋጀት ፣ ወጣቱ ትውልድ በዝማሬ እና ሰብከተ ወንጌል አገልግሎት እንዲሳተፍ አድርገዋል በማድረግ ላይም ይገናሉ፡፡ ኮርሶችን፣ ሴሚናሮችን ሥልጠናዎችን፣ ጉዞዎችን በማዘጋጀት ምእመናን ትምህርተ ቤተ ክርስቲንን ምቹ በሆነ መንገድ እንዲያገኙ አድርገዋል በማድረግ ላይም ይገኛሉ፡፡
ከዚህ መንፈሳዊ አገልግሎት ጎን ለጎን በቤተ ክርስቲያኒቱ በሀገረ ስብከቱ ስር በሚተዳደሩ ገዳማትና አድባራት በሚደረገው ሁሉንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ በግንባር ቀደም ከሚጠቀሱ አንዱ አካል ወጣቶች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በአስፈለገው መንገድ ሁሉ በመላላክ፣ በመዝሙር፣ በሥነጽሁፍ፣ በድራማ፣ በግጥም፣ ልጆችን በማስተማርና ስብከተ ወንጌልን በሚስፋፋት ፣ የቅጽረ ቤ/ክ ጽዳት በማጽዳት፣ የቤተክርስቲንን አልባሳት በማጠብ፣ ንጣፎችን በማንጠፍና በመጎዝጎዝ፣ ሥነ ሥርዓትን በማስከበር ፣ ነዳያን በመርዳት፣ አጽረራ ቤ/ክ በመካላከል ሥራ ዘብ በመቆም በማናቸውም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን የልማት ሥራ አጋዥ በመሆን በዐፀዱ ተከላና እንክብካቤ፣በዘመናዊ የጽህፈትና ሒሳብ ሥራ ፣እንዲሆም በተግባረ እዱና በኪነ ጥበቡ ሥራ በጥበበ እዱ፣ ሥዕሉ፣ የስፌትና ጥልፍ ሥራ በመሥራት ለቤተ ክርስቲኒቱ የገቢ ምንጭ በመፍጠር ወጣቱ/ ሰንበት ት/ቤቱ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡
ምንም እንኳን በሁሉም ትላልቅ ገዳማትና አድባራት ሰ/ት ቤቶች አገልግሎቱ አዘውትሮ የሚሰጥና የተለመደ ቢሆንም ለምሳሌ ያህል የመ/ቅ/ሥ/ካቴድራል እና የምስካዬ ሕዙናን ተምሮ ማስተማር ሰንበት ት/ቤቶች ለህብረተሰቡ የሚሰጡትን አገልግሎቶች ብንመለከት፡-
- ያሬዳዊ ዜማን በጥናትና በማስጠናት በቤተ ክርስቲያኑ አገልግሎት በተለይ በቅዳሴ ጊዜ ተሰጥዎ እንዲቀበሉ ከማድረጉም በላይ ጋብቻቸውን በቤ/ክ ለሚፈጽሙ ሙሽሮች መዝሙር በመዘመር፣ በከበሮና በሽብሻቦ በማጀብ ጥሩ መንፈሳዊ አገልግሎት ሰለሚሰጡ ብዙ ሙሽሮች ጋብቻቸውን በካቴድራሉና በገዳሙ እዲፈጽሙ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛሉ፡፡
- የድራማና የሥነ ጽሑፍ ክፍሎች በማቋቋም የተለያዩ ድራማዎችን በማዘጋጀትና በታላላቅ በዓላት ለአካባቢው ህብረተሰብ በማሳየት ሥነ ጽሑፎችንም በማቅረብ ሃይማኖታዊና ማህበረሰባዊ እውቀትን በማስፋፋት ላይ ይገኛሉ፡፡
- በሰበካ ጉባኤና በልማት ኮሚቴ አባልነት በመሳተፍ ወሳኝና ቁልፍ የሆኑ የልማት ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡
- የሰንበት ት/ቤቶች አባላት የቤተ ክርስቲያኒቱን የሞራል እሴቶች ጠብቀው ሕይወታቸው ግብረ ገብነት ባለው መንገድ እንዲመሩ የዲስፕሊን ኮሚቴ በማቋቋም የሚሰሩ ሲሆን አንዳንድ ወጣቶች የግብረ ገብነት ችግር ሲገጥማቸው ወደ ዲስፕሊን ኮሚቴው ቀርበው መንፈሳዊና ሥነ-ልቦናዊ ምክር በመቀበል በዚህ ረገድ ላጋጠማቸው ችግር መፍትሄ በማግኘት የቤተክርስቲያንን ሕብረተሰብ የሞራል ደረጃ ጠብቀው በማስጠበቅ አርአያነት ያለው ህይወትና ሥራ ሠርተው እንዲኖሩ በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡
በአጠቃላይ እነዚህ ሰንበት ት/ቤቶች ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ወጣቶች እንቅስቃሴ በትምህርትም ሆነ በሥራ መስክ ግባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ስለሆነም ሰንበት ት/ቤቶቹ ብዙ ገጽታ ያላቸው አዳዲስ መርሐ ግብሮች በማውጣትና ተግባራዊ በማድረግ ለቤተክርስቲያኗ እና ለሀገሪቱ በሞራ የተገነባ አስተማማኝ ተከታይ ትውልድ እንዲኖራት የበኩላቸውን ድርሻ አበርክተዋል፣ በማበርከት ላይም ይገኛሉ፡፡