“የወለዱትን ማሳደግ ከባድ በሆነበት በዚህ ዘመን ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ሕጻናትን ሰብስቦ ማሳደግ ሀገራዊና መንፈሳዊ ኃላፊነትን መወጣት ነው”። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ

“የወለዱትን ማሳደግ ከባድ በሆነበት በዚህ ዘመን ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ሕጻናትን ሰብስቦ ማሳደግ ሀገራዊና መንፈሳዊ ኃላፊነትን መወጣት በማለት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ገለጹ።
ቅዱስነታቸው ይህንን ያሉት በዛሬ ዕለት የሰበታ ጌቴሴማኒ ቤተ ደናግል ወጠባባት የእናቶች ገዳምንና በዚያ የሚያድጉ ሕጻናትን በመጎብኘት ቡራኬ በሰጡበት መርሐ ግብር ላይ ነው።
ቅዱስነታቸው ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና መንበረ ፓትርያርክ የየመምሪያው ሓላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ጋር በሰበታ ጌቴሴማኒ ቤተ ደናግል ወጠባባት የእናቶች ገዳም ተገኝተው በዓለ ልደትን ከሕጻናት ጋር አክብረዋል።
በመርሐግብሩ ላይ የተገኙት ብፁዕ አቡነ ቶማስ በገዳሙ እያደጉ ያሉት ሕጻናት በልብስና በምግብ እንዳይራቆቱ ብቻ ሳይሆን በመንፈስ ድሆች እንዳይሆኑ በማስተማር እያገለገላችሁ ላላችሁ እናቶች ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነው ሲሉ አስተምረዋል ።
በመቀጥልም :- በገዳሙ ውስጥ እየኖሩ ከአንድ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል በመማር ላይ የሚገኙ በደረጃ በከፍተኛ ደረጃ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች ከቅዱስነታቸው እጅ የማበረታቻ ሽልማት ተቀብለዋል ።
ብፁዕ ወቅዱስ ቅዱስ ፓትርያርኩ :- የወለዱትን ማሳደግ ከባድ በሆነበት በዚህ ዘመን ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ሕጻናትን ሰብስቦ ማሳደግ ሀገራዊና መንፈሳዊ ኃላፊነትን መወጣት ነው። እኛም በየጊዜው እየመጣን እንጎበኛችኋለን በማለት አባታዊ የማጽናኛ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በመጨረሻም ቅዱስነታቸው :- በሰበታ ጌቴሴማኒ ገዳም በኮሪደር ልማት ተነሺ የሆኑ የአገልግሎት እንዲሁም የልማት ቦታዎችን ጎብኝተዋል። ©ኢኦተቤ ቴቪ