የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤት በሥሩ ካሉት አድባራትና ገዳማት ጋር በመሆን የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤን እያካሄደ ይገኛል!

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ሥር ከሚገኙት ከሰባቱ ክፍላተ ከተማ አንዱ የሆነው የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤት ከአድባራቱና ገዳማቱ ጋር በመሆን የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤን እያካሄደ ይገኛል።

ጉባኤው እየተካሄደ ያለው በቶታል ደብረ ገነት ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ነው።

ሊ/ት ወንድወሰን ገ/ሥላሴ የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስኪያጅ በጉባኤው ላይ ለተገኙት “የእንኳን ደህና መጣችሁ” መልእክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ስርጭት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊ/ማ ፋንታሁን ሙጬ “የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መጠናከር ለቤተክርስቲያን ሁለንተናዊ እድገት” በሚል ርዕስ ስልጠና ሰጥተዋል።

ሰበካ ጉባኤ ማለት የካህናትና የምእመናን ኅብረት መሆኑን ገልጸው የቤተክርስቲያን አስተዳደር በካህናትና በምእመናን ኅብረት መመራት ውጤቱ ያማረ መሆኑን አብራርተዋል።

የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በ1965 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ መቋቋሙንም ታሪክ ጠቅሰው አውስተዋል።

ሰበካ ጉባኤ የተመሠረተበት ዋና ዓላማ የቤተክርስቲያንን አስተዳደር ለማጠናከር፣ ቅድስት ቤተክርስቲያንን መጠበቅና አገልግሎቷም የተሟላ እንዲሆን ለማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል።

አክለውም የቤተክርስቲያንን አገልጋዮች በሐዋርያዊ ተግባር ማደራጀት፣ ችሎታቸውንና ኑሯቸውን ማሻሻል፤ ምእመናን በመንፈሳዊ ዕውቀት ጎልምሰው በክርስቲያናዊ ሕይወት እንዲኖሩ፤ የቤተክርስቲያንን ሀብት መጠበቅና በገቢ ራሷን እንድትችል ማድረግ ዋና ዋና ዓላማዎች መሆናቸውን ዘርዝረዋል።

ሰበካ ጉባኤ ከመመሥረቱ በፊት የቤተክርስቲያን አስተዳደር መጎዳቱን አውስተው ነገር ግን ሰበካ ጉባኤ ከተመሠረተ በኋላ የቤተክርስቲያን አስተዳደር በእጅጉ መሻሻሉን አብራርተዋል።

በአንዳንድ ምክንያቶች ግን እስከ አሁንም ድረስ የአስተዳደር ችግር በቤተክርስቲያኒቱ መኖሩን አያይዘው ጠቅሰዋል፤ ለዚህም በየገጠሩ ያሉ አብያተክርስቲያናት ዘርፈ ብዙ በሆኑ ችግሮች ውስጥ መገኘታቸው አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሰበካ ጉባኤ የሚጠናከርባቸውን መንገዶች ጠቅሰው ካህናት፣ ምእመናን እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ለሰበካ ጉባኤ ጉባኤ ጉልህ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።

ስልጠናው ከተሰጠ በኋላ ከታዳሚዎች አስተያየቶችና የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

ቀሪ መረጃዎችንም ከደቂቃዎች በኋላ የምናሳውቅ መሆኑን መግለጽ እንወዳለን።

ለተጨማሪ መረጃ የሀገረ ስብከቱን ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ይጎብኙ፣ like እና Join በማድረግ ይቀላቀሉ፣ ለሌሎችም ሼር ያድርጉ!!!

  1. ድረ-ገጽ:- www.addisababa.eotc.org.et
  2. ፌስ ቡክ ገጽ:- www.facebook.com/AddisAbabaDiocese/
  3. ተሌ ግራም ቻናል:- t.me/AddisAbabaDiocese

ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ