የከተራ እና የጥምቀት እንዲሁም የቃና ዘገሊላ በዓላት በሰላም መከበራቸውን አስመልክቶ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የተሰጠ መግለጫ

“ይትባረክ እግዚአብሔር፣ አቡሁ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ፤ ዘባረከነ በኩሉ በረከተ መንፈስ ቅዱስ ዘበሰማያት በክርስቶስ ኢየሱስ፣
በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን ፤ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ” (ኤፌ.1፥3/
ብርሃነ ዓለም እየተባለ የሚጠራው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክቱ የተባረክንበት በረከት ምንያህል ትልቅ መሆኑንና ባረኪው እግዚአብሔር በልጁ እንደቀሰን ሲናገር “በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ” (ኤፌ.1፥3/ በማለት አመስግኗል።
የርኅራኄ አባት፣ የመጽናናትም አምላክ እግዚአብሔር አባታችን ምድሪቱን እና እኛን ልጆቹን በምሕረቱ ያልደገፈበት፤ በቅዱሱ መንፈስ ያልባረከበት ዘመን የለም፣ ይልቁንም ከሁሉ በተሻለ ሁኔታ በዘመነ ሐዲስ ኪዳን በተወዳጅ ልጁ ኢየሱስ ክርሰቶስ በሰማያዊ ሥፍራ በመንፈሳዊ በረከት የባረከን መሆኑ ቅዱሱ መጽሐፍ ደጋግሞ ያረጋግጣል።
በክርስቶስ ደም ተመሥርታ ፤በነቢያትና በሐዋርያት አስተምህሮ ላይ የጸናችው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን በምትሰጠው መንፈሳዊ አገልግሎት እና በምትፈጽማቸው ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ከአማኞቿም አልፋ ለረከሰችው ምድር የቅድስና እና የመባረክ ምክንያት ሆና ሽህ ዓመታትን አሳልፋለች፣ ወደፊትም ትቀጥላለች።
በየዓመቱ በአደባባይ ወጥተን አባታችን እግዚአብሔርን በኅብረ ዝማሬ የምናመልክበት የጥምቀት በዓል ከመንፈሳዊ ይዘቱ ባሻገር በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በማይዳሰስ ቅርስነት ተመዝግቦ የሚከበር ሲሆን በዘንድሮው የ2017 ዓ.ም አከባበሩም ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ወጥተው ከተማውን የባረኩበት፣ ክርስቲያናዊ ትብብርና አንድነት የታይበትና ለሀገራችን ብሎም ለመላው ምድራችን የሚተርፍ ጸሎትና ቡራኬ የተፈጸመበት ነው።
የሀገረ ስብከታችን የአስተዳደር ክልል በሆነው አዲስ አበባ ከተማ ላለፉት 3 ቀናት ጃንሜዳን ጨምሮ በ64 ባሕረ ጥምቀታት የተከበረው የከተራ እና የጥምቀት እንዲሁም የቃና ዘገሊላ በዓላት በሚሊየን የሚቆጠሩ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት፣ እጅግ ደማቅ በሆነ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ያለአንዳች የጸጥታ ችግር ተከብሮ ተጠናቋል።
ጥር 13 ቀን ከብረው ወደ መንበራቸው የሚገቡትን ታቦተ ቅዱስ እግዚአብሔርንና ታቦተ ቅዱስ ሩፋኤልን ሳያካትት ለመንፈሳዊ አገልግሎቱ ከመንበረ ክብራቸው ወደ ባሕረ ጥምቀት ከወረዱት ታቦታት ጥር 11 ቀን199 ሲመለሱ ጥር 12 ቀን ደግሞ 59 በድምሩ 258 ታቦታት በተቀመጠው ስዓት በክብር ወደ መንበረ ክብራቸው ተመልሰዋል።
በዛሬ ዕለት ከባሕረ ጥምቀት ወደ መንበረ ክብራቸው የሚመለሱት 26 ታቦታት ሲሆኑ በተቀመጠው የሰዓት መርሐ ግብር መሠረት እንዲገቡ መመሪያ ተላልፏል።
የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በተመለከተም ከወትሮው በተለየ መልኩ ለበርካታ አገልጋዮች ስምሪት ተደርጎ ለበዓሉ ለተሰበሰቡት ምዕምናን ሰፊ ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቷል፤ ወደፊትም በተሻለ አደረጃጀት የሚሠራበት ይሆናል።
አንዳንድ ገዳማትና አድባራት ከባሕረ ጥምቀቱ ባላቸው ርቀት እና የተወሰኑ የሥራ መሪዎች ለተላለፈው መመሪያ ባሳዩት ቸልተኝነት የተነሣ ከተቀመጠው የስዓት ገደብ አምሽተው የገቡ አብያተ ክርስቲያናት መኖራቸውን አረጋግጠናል፤ በቀጣይ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት እንዳይፈጸምም አስተዳደራዊ ዕርምት የሚወሰድ ይሆናል።
በመጨረሻም፦
1.በዓሉ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ የእግዚአብሔር ጠብቆት ለደቂቃዎችም ቢሆን ያልተለየው መሆኑ እንዳለ ሆኖ ከሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች ጀምሮ የክፍላተ ከተማ ሥራ አስኪያጆችና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የሰ/ት/ቤቶች አንድነትና ተማሪዎች ፣ የየአካባቢው ወጣቶችና ልዩ ልዩ ማኅበራት በተደራጀ መልኩ መረጃ በመለዋወጥ፣ በማስተባበር፣ መንገዶችን በማጽዳትና ለጉዞ ምቹ በማድረግ ላበረከታችሁት አስተዋጽኦ ከልብ የመነጨ ከፍ ያለ ምሥጋናችንን እናቀርብላችኋለን።
2.የባሕረ ጥምቀት ይዞታዎችን አስከብሮ ማረጋገጫ በመስጠት፣ ችግር ያለባቸውንም ጭምር ቦታው ድረስ በመሄድ ጊዜያዊ አቅጣጫ በማስቀመጥ፣ የጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት ስቴጅን ለመሥራት የሚያስፈልገውን ወጪ በመሸፈንና በጸጥታው ረገድ በጋራ በመሥራት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤት ክብርት ከንቲባችን ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ላደረጉት ከፍተኛ ድጋፍ እና ትብብር በቅድስት ቤተክርስቲያናችን ስም እናመሰግናለን፤ በቀጣይም የጋራ ትብብር በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ እንደምንሠራ እናረጋግጣለን።
3.የአዱስ አበባ ከተማ የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽ እና አጠቃላይ የፀጥታ መዋቅር ኃላፊዎችና አባላት በሙሉ ከበዓሉ ቀደም ብሎ ከነበረው ቅድመ ዝግጅት ጀምሮ ተደጋጋሚ ውይይቶችንና ምክክሮችን በማድረግ በዓሉ በሰላም እንዲከበር ለሰጣችሁን የጸጥታ ሽፋን ከልብ እናመሰግናለን።
4. የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤው አብያተ እምነትን ከማቀራረብ ጀምሮ ለከተማ አስተዳደሩ የሚቀርቡ የመሬትና ልዩ ልዩ ጥያቄዎችን በማስተባበር እንዲሁም የባሕረ ጥምቀት ይዞታዎችን በማስከበር ከፍተኛ ሚናውን እየተወጣ ለሚገኘው ለአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምሥጋና እናቀርባለን።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት
ጥር 13 ቀን 2017 ዓ.ም
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ