የእስክንድርያ ፖፕ እና የመንበረ ማርቆስ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ ዳግማዊ ኢትዮጵያን በመጎብኘት ላይ ናቸው

                                                                                        በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ(MA)

000921

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ ዳግማዊ የአሌክሳንድሪያ ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ማርቆስ መንበረ ፓትርያርክ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በመስቀል ደመራ በዓል ላይ እንዲገኙ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በተደረገላቸው ግብዣ መሠረት ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል።
በዚሁም መሠረት ቅዱስነታቸው መስከረም 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ከሌሊቱ 9:00 ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በሚደርሱበት ጊዜ  በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት  ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆነ በነጋታው ቅዳሜ መስከረም 15 ቀን 2008ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጰሳት ፣  የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማት እና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ መዘምራንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፣ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት፣ ‹‹የእንኳን ደኅና መጡ›› ፕሮግራም ተከናውኗል፡፡ ቅዱስነታቸውም በበአሉ ላይ  ለተገኙ ህዝበ ምእመናን ቡራኬ ሰጥተዋል፡፡
ቅዱስነታቸው  ስለ ሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት ታሪካዊ ግንኙነት በሰፊው ከገለፁ በኋላ ኢትዮጵያ ለዕድገቷ የምታከናውናቸውን ተግባራት የግብፅ ቤተክርስቲያን እንደምትደግፍ ተነግረዋል። “አንድ ከሚያደርጉንና ከሚያስተሳስሩን ጉዳዮች ዋናው ነገር የዓባይ ወንዝ ነው” ያሉት አቡነ ታዎድሮስ “የአገራቱ መሪዎችም ምንም ዓይነት ልዩነትና ፀብ እንደማይፈጥሩ እርግጠኞች ነን” ብለዋል። “የዓባይ ወንዝ እግዚአብሔር በነፃ የሰጠን ስጦታ ነው፣ ሁሉም የሰው ልጆች ከፀሐይና ከነፋስ በነፃ እንደሚጠቀሙ ሁሉ ከዚህም ወንዝ በነፃ ይጠቀማሉ ይህንንም ስጦታ በነፃ እየተጠቀምን በፀጋ እንኖራለን” ሲሉ ነው የተናገሩት።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ አቡነ ማትያስ በበኩላቸው አገራቱ ባህልን፣ ቋንቋን፣ሥነ ጽሑፍን፣ ንግድን፣ መንፈሳዊና ማሕበራዊ ጉዳዩችን ያካተተ የቆየ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰዋል።”ከዚህም ባለፈ የአባይ ወንዝን በጋራ የምንጠጣ ታሪካዊያን ሕዝቦች ነን” ሲሉ ተናግረዋል።

ወንዙን በአግባቡና በፍትኃዊነት ከተጠቀምንበት ለሌሎች አገራት ጭምር የሚበቃ ማለቂያ የሌለው የአምላክ በረከት መሆኑን ገልፀዋል።ይህን ወንዝ በሠላማዊ መንገድ በመጠቀም የሁለቱ አገራት መንፈሳዊና ማኅበራዊ ግንኙነቶች ለዓለም ምሣሌ በሚሆን መልኩ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አባታዊ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስና የግብፅ ኮፒቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናት መንፈሳዊ ግንኙት ከ1 ሺህ 600 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ መሆኑን የታሪክ ድርሳት ያስረዳሉ።
በዚሁ ዕለት የአሌክሳንድሪያ ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ማርቆስ መንበረ ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ ዳግማዊ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ  ጋር ተወያይተዋል።የብያተ ክርስትያናቱ ተቀራርቦ መስራት ኢትዮጵያና ግበጽ የያዙትን አብሮ የመልማት ግብ ለማሳካትና ግንኙነታቸውን ለማዳበር የጎላ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።
አቡነ ታዎድሮስ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ አክሱምን፤ጎንደርን፣  እንዲሁም የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስትያናትን እንደሚጎበኙ ይጠበቃል።
{flike}{plusone}