የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በዓል በርእሰ ኣድባራት ወገዳማት ኣክሱም ፅዮን በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ዋለ

0343

በየዓመቱ ህዳር 21ቀን የሚከበረው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም መታሰብያ በዓል በዘንድሮ ዓመት ብፁዕ ወቅዱስ ኣቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘኣክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ብፁዓን ኣበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ሊቃውንተ ቤተ-ክርስተያን እና በርካታ ምእመናን በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሯል ።የቦታውን ጥንታዊነት እና የታሪክ አዘል ቅርሶች ምንጭ መሆኑን የተረዱ በርካታ የዓለም ቱሪስቶች ለጉብኝት  ተገኝተዋል።በዓሉ በተከበረበት ወቅት የገዳሙ ሊቃውንት በመጀመርያ ሓወልቱ በቆመበት ቦታ ላይ ታቦተሕጉ     ለእግዚኣብሔር የሚለውን ያሬዳዊ ዝማሬ ካቀረቡ በኋላ  ሙራደቃል (ቤተቀጢን) በመባል በሚታወቀው ማለትም ቅዱስ ያሬድ የዜማ ድርሰት በደረሰበት ቦታ ላይ ቀዳሚሃ ለፅዮን የሚለው ያሬዳዊ ወረብ በድጋሚ በሊቃውንቱ ተዘምሯል። በመቀጠልም በሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ኲሉ ዘጌሰ ኃቤሃ ኢይጻሙ የሚል እና ዋካ ይእቲ ገበዘ ኣክሱም የሚል  ያሬዳዊ ዝማሬ ቀርቧል። በገዳሙ የቅኔ ሊቃውንት በርካታ ቅኔያት የቀረቡ ሲሆን ከቀረቡት ቅንያት መ/ር ኣስካለ በረከት ውብነህ  የተባሉት ሊቅ ያሰሙትን  መወድስ እንደ ሚከተለው አቅርበነዋል ።
አንቲ ጽዮን ዘኣስተርአይኪዮ ፣ለገብረ ኣዶናይ ሓዝቅኤል በፈለገ ኮቦር ነቅዕ።ወለ መቃርዮስ አብ ዘአስተፍሳሕኪዮ ቆዕ።ማትያስ ፓትርያርክ ዘሃደረ መስለ አራዊት በፍቅር ቅብዕ።ወዘተናገረ ለክብርኪ ጎርጎርዮስ አብ ነባቤ መለኮት እግዚእ ።ዲዮስቆሮሲሂ ሊቀ  ጳጳስ ዘልቡናሁ ጥቡዕ ።ዘተሰደ በፍቅርኪ እምነ ሀገሩ ኀበ ካልዕ።ወካልዕ ማትያስ መልእልተ ምስዋዕ።ዘርእየኪ በእዴኪ እኂዘኪ ቈፅለ  አውልዕ። 
የገዳሙ ዋና ኣስተዳዳሪ ንቡረእድ መሃሪ የገዳሙ ጥንታዊነት የተመለከተ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን በሪፖርቱ ማጠቃለያ አሰንያ እግዚኦ በስምረትከ ለፅዮን የሚለውን የመጽሓፍ ቃል ጠቅሰዋል።
በቡፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የከፋ ሸካ ቤንች እና ማጂ አህጉረ ስብከት ፣የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ሊቀ ጳጳስ በዓሉን አስመልክተው ትምህርተ ወንጌል ካቀረቡ በኋላ የክልል ትግራይ ርእሰ መስተዳድር ክቡር ኣቶ ኣባይ ወልዱ የቅርስ ጥበቃን ፣ የቱሪስት ፍሰትን ፣ ወቅቱ ያመጣውን የድርቅ ሁኔታ ኣስመልክተው ለተሰበሰበው በርካታ ህዝብ መልእክት ኣስተላልፈዋል። በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ኣቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘኣክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ባስተላለፉት ኣባታዊ  መልእክት  እንኳን ለታላቁ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምበዓል በሰላም ኣደረሳችሁ!!
ዛሬ በማክበር የምንገኘው የፅላት ፅዮንን እና የአሰርቱ ቃላትን በዓል ነው።
1.ከኔ በስተቀር ሌላ ኣምላክ ኣታምልክ 2. የእግዚኣብሔር ስም በከንቱ ኣትጥራ 3. ሰንበትን ኣክብር 4. አባትህ እና እናትህ ኣክብር …..ተብለው በመጽሓፍ የተጠቀሱትን የእግዚኣብኤር ትእዛዛት ቅድስነታቸው  አብራርትዋል ።
አዲሱ ትውልድን ኣስመልክተው ባስተላለፉት መልእክት ጤንነታችሁን ጠብቁ ፤ ትምህርታችሁን  ጠንክራችሁ  ተማሩ ፤ አገራችሁን አልሙ ፤ ዋስትና የሌለበት ሃገር አትሂዱ በማለት ሰፋ ያለ ኣባታዊ ትምህርት ካስተማሩ በኋላ የበዓሉን ፍፃሜ ሁኗል።
በተመሳሳይ ዜና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘኣክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመሆን እሁድ ህዳር 19 ቀን 2008 ዓ.ም  ከኣዲስ ኣበባ ተነስተው  ከረፋዱ 3:00 ሰዓት ሲሆን ኣፄ ዮሃንስ አየር ማረፍያ የደረሱ ሲሆን ከዚያው ተነስተው  በቅጥታ ወደ ርእሰ ኣድባራት ወገዳማት ኣክሱም ፅዮን ቤተ-ክርስትያን በመድረስ የኪዳን ጸሎት አድርሰው እንዳበቁ ወደ አድዋ ከተማ የጉብኝት  ጉዞ ኣድርግዋል።አድዋ ከተማ  መግቢያ ላይ እንደደረሱ በርካታ ካህናት ምእመናን  ደማቅ ኣቀባበል ኣድርዋችዋል።  ቅዱስነታቸው በሰረገላ ላይ ተቀምጠው ከተማዋን በግልፅ እየባረኩ  ከ6 ኪ.ሜ ያላነሰ በሰረገላ ተጉዘዋል።በኣድዋ እንዳ ስላሴ ሰለተደረገው ታላቅና ደማቅ ኣቀባበል ቅዱስነታቸው ምስጋናቸው አስቀድመዋል።
አድዋ የታሪክ ከተማ መሆንዋን በትምህርታቸው ኣብራርትዋል። ከዚያም በአድዋ ከተማ የሚገኘውን የአዲ አቡን ደብረ ማርቆስ ኣቡነ ተክለሃይማኖት ገዳምን ጎብኝተዋል። በገዳሙ የሚገኙ ጥንታውያን የብራና መጻሕፍት ፣ ከነገሥታት የተበረከቱ የብር ዘውዶች ፣ መስቀሎች ፣ ቃጭሎች፣ ፅዋዎች እና የአባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን አርዌ ብርት ተጎብኝተዋል።
በመቀጠልም በቀጥታ ወደ እንዳ ኣባ ገሪማ ገዳም በመጓዝ በገዳሙ በቅርስነት የሚገኙት በርካታ ቅርሶች ተጎብኝተዋል።ከተጎበኙት ቅርሶች መካከል ብፁዕ ወቁዱስ ኣቡነ  ጳውሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በስጦታ ያበረከቷቸው የወርቅ እና የብር መስቆሎች ፣ ሃይከኖች ፣አልባሳት እና ሌሎችም ልዩ ልዩ ስጦታዎች እና መጽሓፈ ሓዊ ፣የጊዮርጊስ ወልደ አሚድ መጽሓፍ እና የዮሴፍ ወልደ ኮርዮን የተባሉ ጥንታውያን የብራና መጻሕፍት እና ከነገሥታት የተበረከቱ  ዘውዶች ኩስኩስቶች ተጎብኝተዋል። በማግሥቱ ህዳር 20 ቀን 2008 ዓ.ም ከአድዋ ከተማ በ20 ኪ.ሜ ርቀት በሚገኘው ወደ ቅዱስ አፍጼ ገዳም በመጓዝ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ መሰዋእተ ኦሪት የተሰዋበትን ሙክራብ ጎብኝተዋል። በገዳሙን የሚገኙ በርካታ እድሜ ጠገብ ልዩ ልዩ ቅርሶች ተጎብኝተዋል ለእንዳ ኣባ ገሪማ እና ለየሓ ቅዱስ አፍጼ ገዳማት ለእያንዳንዳቸው ብር 30 ሺህ ተበረክቷል። ከቅዱስ አፍጼ ገዳም ጉብኝት በአድዋ ከተማ የሚገኘው የአልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ተጎብኝቷል። በቡዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሠራተኞችም የተሰማቸውን ደስታ በታላቅ እልልታ አሰምተዋል።
በመጨረሻም ቅዱስነታቸው  ወደ ርእሰ ኣድባራት ወገዳማት ኣክሱም ፅዮን ቤተ-ክርስትያን የተጓዙ ሲሆን በኣክሱም ከተማ በፖሊሲ ኦልኬስትራ ትግራይ ፣ በሰረገላ ላይ ተቀምጠው ሕዝቡን እየባረኩ ወደ ቤተ-ክርስተያን ገብተው የኪዳን ጸሎት ካደረሱ በኃላ በአውደ ምሕረቱ ለተሰበሰበው ሕዝብ ቃለ ቡራኬ እና  ትምሕርተ ወንጌል አስተላልፍዋል።

                                                                                                            መ/ር ሣህሉ አድማሱ(ከአክሱም ፅዮን)

{flike}{plusone}