የኢየሱስ ክርስቶስን የስቅለት በዓል አስመልክተው ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ያስተላለፉት መልእክት

ፍጹም ፍቅር

ጊዜው ከዛሬ 2000 ዓ.ም ገዳማ በፊት ነበር ዕለቱ ደግሞ ዕለተ አርብ ። ለዘመናት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ዕንቅፋት ሆኖ የቆየው የኃጢአት ግድግዳ የፈራረሰበትና በአንጻሩ ደግሞ ጽኑ የምሕረትና የጽድቅ ድልድይ የተገነባበት፣ በሥልጣን ላይ የነበረው ሞት በጊዜ ገደብ ምክንያት ሥልጣኑን ለሕይወት ያስረከበበት፣ ዓመተ ፍዳም ከአቅም ማነስ የተነሣ መንበረ መንግሰሥቱን ለመሪው ለዓመተ ምህረት የለቀቀበት ክስተቶች የተከናወኑበት ዕለት ነው። ታዲያ እነዚህ ሁሉ የሆኑት በዘፈቀደና በአጋጣሚ ሳይሆን በዕለቱ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በከፈለው መለኪያ በሌለው ፍጹሞ በሆነ ፍቅር ነው።

ብዙ ጊዜ ሰው ሰውን ሲወድ መስፈርት ያስቀምጣል። ደም ግባትን፣ ዝናን፣ ሥልጣንን፣ የሥጋ ዝምድናን ወዘተ..። ለዚህም ነው አንድን ሰው እከሌን የምትወደው ለምንድነው ብለን ስንጠይቀው ምክንያቶችን የሚደረድርልን ። ከዚህ የምንረዳው እውነት ሰው ሰውን የሚወደው በሚለካ ነገር መሆኑን ነው። የክርስቶስ ፍቅር ግን ከዚህ ፍጹም ይለያል። ክርስቶስ ሲሞትልን ከእኛ የሚወደድ ነገር አግኝቶ አይደለም። እርሱ እንዲሁ ወደደን እኛን ለመውደድ ምክንያት አልፈለገም። መጽሐፍም እንዲህ ሲል ያረጋግጥልናል ” በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።”(ዮሐ 3:16)።
በእምነት ከማስተዋል በስተቀር የክርቶስን ፍቅር ስፋቱን፣ ርዝመቱን፣ ከፍታውንና ጥልቅነቱን ለክተን ይህን ያህል ነው ብለን መግለጽ የምንችልበት መለኪያ መሣሪያ የለንም። ሐዋርያውም በመልእክቱ ” ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል፥ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ፥ እስከ እግዚአብሔርም ፍጹም ሙላት ደርሳችሁ ትሞሉ ዘንድ “( ኤፌ 3:18-19) ይለናል። ፍጹም የሆነውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅና ለማስተዋል ዘወትር ቅዱስ ቃሉን ያለመታከት በጽኑ እምነት በማንበብ መትጋት ይኖርብናል።

በበደልነው ጊዜ አላጠፋንም ፤ ምሕረቱንና ቸርነቱን አበዛልን፤ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካለው ነገር ሳይሆን ራሱን ነው በመስቀል ላይ አሳልፎ የሰጠን። መጽሐፉ ቅዱስ “አንዱ ስለሁሉ ሞተ” (2ኛ ቆሮ 5፥14) በማለት የክርስቶስን የፍቅር ጥግና ከፍታ ያስረዳናል። መዳናችን፣ ከዘለዓለም ሞት መትረፋችን፣ ከገሃነም እሳት ማምለጣችን፣ ሰላምና እረፍት ማግኘታችን በእርሱ በመድኃኔዓለም ቤዛነትና የደም ዋጋ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ እንዲህ ብሏል “ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን በጸጋ ድናችኋልና” (ኤፌ 2፥4-5 )። እኛ በበደላችን ሙታን በነበርን ጊዜ እርሱ ለእኛ ጸጋችን(ስጦታችን) ሆኖ ተሰቅሎ ሞቶ አዳነን።

በመጨረሻም በልባችን ልብ ልንለው የሚገባን ነገር ቢኖር አባትና እናት ልጆቻቸው ቢታመሙ ሐኪም ወይም ጸበል ሊወስዷቸው ይችላሉ እንጂ ነፍሳቸውን ለልጆቻቸው አሳልፈው አይሰጡም። እርሱ መድኃኔዓለም ግን እራሱን አሳልፎ በመስጠት ከኃጢአት በሽታ አከመን። ደረቅ አዲስ ኪዳን በመባል የሚታወቀው ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ 53 ላይም እንደተገለጸው “በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን” ይለናል። እኛ መቁሰል ሲገባን ፍቅር ባህርይው የሆነ ጌታ ስለእኛ ቆሰለ። ይህንን ፍጹም የሆነውን የክርስቶስን ፍቅር ዘወትር ያለመዘንጋት በእምነት በማሰብና እኛም በተሰጠን ጸጋ ለሌሎች በተግባር የሚገለጥ ፍቅርን በመስጠጥ መልካም በሆነ መንፈሳዊ ሕይወት ልንጓዝ ይገባል በማለት አባታዊ መልእክቴን አስተላልፋለሁ።


ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ