የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አሁናዊ ፈተና እና ችግር መነሻ ምክንያቱ የስብከት ወንጌል አገልግሎት መዳከም መሆኑ ተገለጸ
ታህሳስ 5 ቀን 2013 ዓ/ም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብከት ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ ዋና ክፍል ኃላፊ መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ እና የሀገረ ስብከቱ ዋና ፀሐፊ መ/ር ታዲዎስ ሽፈራው እንዲሁም የሰባቱም ክፍላተ ከተማ የስብከተ ወንጌል ኃላፊዎች እና የሁሉም አድባራትና ገዳማት የስብከተ ወንጌል ኃላፊዎች በተገኙበት በሀገረ ስብከቱ የስብሰባ አዳራሽ አዲስ ከተመደቡት የሀገረ ስብከቱ ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተስማና ሌሎችም የሥራ ኃላፊዎች ጋር ትውውቅ ተደርጓል።
በአድባራትና ገዳማቱ የስብከት ወንጌል እንቅስቃሴ ዙሪያም አጭር ዳሰሳዊ ጥናት ቀርቧል፡፡በመርሐ ግብሩ ላይ የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን መልእክት መሠረት ያደረገና”ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ መኖር” (ፊልጵ.1:27) የሚል አጭር ዳሰሳዊ ሐሳብ በሀገረ ስብከቱ ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ ዋና ክፍል ኃላፊው መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ የቀረበ ሲሆን በቀረበው ዳሰሳዊ የመነሻሐሳብ ላይ ለቤተ ክርስቲያን የተሰጠው የስብከተ ወንጌል አገልግሎት አደራ ትልቅና ዘላለማዊ ነው፡ ሕይወት የሚድንበትን ይህንን መለኮታዊ ስጦታ ለማገልገል መመረጥ ደግሞ ትልቅ ዕድል ነው።
ስለሆነም እኛ የቅዱስ ወንጌሉ አገልጋዮች በዕውቀትና በሕይወት የተደገፈ አገልግሎት በመስጠት፡ቅዱስ ወንጌሉን እንደሚገባ በመስበክና በመኖር እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱሳዊ የአገልጋይነት ሕይወትን በመለማመድና አርአያ በመሆን እንደቃሉ የሚኖሩና የሚመላለሱ ኦርቶዶክሳዊ ምእመናንን እናፈራ ዘንድ ታላቅ አደራና መንፈሳዊ ግዴታ አለብን ብለዋል፡፡
አያይዘውም ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት መስጠት: በየጊዜው የሚደረግ የአገልጋይነት ዝግጅት ማድረግ: የመልካም ሥነ-ምግባር ባለቤት መሆን: የጸሎት ሕይወትንመለማመድ ለአገልግሎቱ ያለንን ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ማሳደግ ከአንድ መንፈሳዊ አገልጋይ የሚጠበቁ መንፈሳዊ ግዴታዎች መሆናቸውን አስረድተው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አሁናዊ ፈተና እና ችግር መነሻ ምክንያቱ የስብከት ወንጌል አገልግሎት መዳከም መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ በቅድስት ቤተክርስቲያናችን ትልቅ ሥፍራከሚሰጣቸው የአገልግሎት ዘርፎች መካከል የስብከተ ወንጌል አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎች ከሆናችሁት ከእናንተ ከወንድሞቼና አባቶቼ ጋር በዚህ መልኩ ስለተዋወቅን ደስ ብሎኛል፡ በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት በአደባባይ ከምናከብራቸው በዓላት መካከል አንዱ የሆነውን የጥምቀት ክብረ በዓል በቀጣይ ሳምንት እናከብራለን፡ይህንን ዓለም አቀፋዊ በዓልበያላችሁበት ቦታ በበላይነትእንድትመሩ ለሕዝበ-ክርስቲያናችንም የሚገባውን የወንጌል አገልግሎት ዘመኑን በዋጀ መልኩ እንድትሰጡ አሳስባለሁ ሲሉ መመሪያ አስተላልፈዋል፡፡
መ/ር ሽፈራው እንደሻው የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ
ፎቶ-በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ