የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አደረገች

“በጎውን ማን ያሳየናል” በሚል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል መነሻነት ወቅታዊና አንገብጋቢ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ መምህራነ ቤተክርሰቲያን፣ የዘርፉ ምሁራን ፣የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በጎልደን ቱሊፕ ሆቴል ሰፊ ምክክርና ውይይት ተከናውኗል፡፡
መርሐ ግብሩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ የተዘጋጀ ሲሆን የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኒቱ የመገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት የበላይ ኃላፊ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ማቴዎስ የምክክር መድረኩ የተዘጋጀበትን ምክንያትና ዓላማ ለጉባኤው ታዳሚዎች የመክፈቻ ንግግር ሲያደርጉ በአሁን ወቅት ቤተ ክርሰቲያን በዘርፈ ብዙ ቸግሮች እየተፈተነች መሆኗን ገልጸው ይህንን አስፈሪና ክፉ ጊዜ የምንሻገርበትና የምናልፍበት በጥበብ የሚሠራ መርከብ ያስፈልገናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠል፤ በምእመናን ላይ እየደረሰ ያለው ግድያ ፤መፈናቀል ፤ስደት ከምንጊዜውም በላይ እየባሰና እየጨመረ ስለመጣ “እንደ ኖህ የመዳኛ መርከብ ለመሥራት ነው” ይህንን የውይይት መድረክ ያዘጋጀነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩም ባደረጉት ንግግር ይህ እየተባባሰ የመጣው የአብያተ-ክርስቲያናት መቃጠል፤ የወንድሞችና የእህቶች መገደል፤የምእመናን መፈናቀል ዕለት ዕለት የሚያሳስባቸው ጉዳይ መሆኑን ገልጸው ለሐገርም ትርፍ የሌለውና ትልቅ ኪሳራ በማለት ገልጸውታል፡፡ አያይዘውም እነዚህን ችግሮች ከቤተ-ክርስቲያን የምናርቃቸው ቁጭ ብለን በሰከነ አዕምሮ ስንወያይ ነው በማለት ለጉባኤው አባታዊ ምክራቸውንና መልእክታቸውን ለግሰዋል፡፡ መንግሥትም ሐገሪቱን በሕግና በሥርዓት ማስተዳደር እንዳለበት በአጽንዖት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ያሬድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለምእመኖቿ ሰላምን ከመስበክ በዘለለ ሠይፍን ይዛ ሰልፍ ያደረገችበት ጊዜ እንደሌለ ጠቅሰው መንግሥትና የመንግሥት አካላት ሕግን በማስፈጸም ቤተክርስቲያንና ምእመናን ላይ የሚደርሰውን ግፍና መከራ መታደግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡


በመርሃ ግብሩ ላይ ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመጡ የሕግና የታሪክ ምሁራን ወቅቱን ያገናዘቡ የተለያዩ ርእሰ ጉዳዮችን የያዙ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ አሁን ባለንበት ወቅት እንደዚህ ያሉ የውይይት መድረኮች ከምንጊዜውም በላይ አስፈላጊና ወሳኝ በመሆናቸው በተደጋጋሚ ሊደረጉ እና ወደ ተግባር ሊቀየሩ ይገባል እንላለን፡፡


መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ የሀገረ ስብከቱ ሪፖርተር