የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መጠናቀቁን አስመልክቶ ባለ 15 ነጥብ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሕገ ቤተ ክርስቲያንንና ኦርቶዶክሳዊ ቀኖናውን መሠረት ባደረገ መልኩ በዓመት ሁለት ጊዜ ማለትም በጥቅምትና በግንቦት ወር የሚካሄድና በቅዱስ ፓትርያሪኩ የሚመራ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ወይም ስብሰባ ታደርጋለች፡፡
የርክበ ካህናት መምጣትን ተከትሎ በግንቦት ወር የሚደረገው ሁለተኛው የብፁዓን አባቶች የሲኖዶስ ምልዓት ጉባኤ ወይም ስብሰባ ግንቦት 13 ቀን /2011 ዓ/ም በጸሎት ተጀምሮ እስከ ሰኔ 3 ቀን 2011 ዓ/ም የቆየውና ለአሥራ ስምንት ቀናት ያክል ሲካሄድ የሰነበተው ይኸው ጉባኤ የቤተ ክርስቲያንን ክብርና ጥቅም የሚያስጠብቁ የተለያዩ መንፈሳዊና ማኅበራዊ እንዲሁም ወቅታዊ ጉዳዮችን በመዳሰስ ውሳኔዎችን አሳልፎና ለአፈጻጸሙም ያመች ዘንድም በብፁዓን አባቶች የሚመራ የተለያዩ የክትትል ኮሚቴዎችን ሰይሞ ከጨረሰ በኋላ በርካታ የሚዲያ አካላት በተገኙበት ባለ አሥራ አምሥት ነጥብ ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት በዛሬው ዕለት በይፋ ተጠናቋል፡፡
በዚህ ወር የተደረገው ሁለተኛው የአባቶች ሲኖዶሳዊ ጉባኤ ከጥቅምት ወር ከተደረገው ምልዓተ ጉባኤ ልዩ የሚያደርጉትን ጉዳዮች አሳልፏል፡፡ እነዚህም ጉዳዮች ወይም ውሳኔዎች
- ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የሚመሩ ሁለት ብጹዓን አባቶችን ማለትም ብጹእ አቡነ ያሬድን የመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ አድርጎ ሲሾም ብጹእ አቡነ ዮሴፍን ደግሞ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አድርጎ መሾሙ፡፡
- በወቅታዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የቀረቡለትን ጥናታዊ የመነሻ ሐሳቦች መሠረት በማድረግ ጠንከር ያለ ውሳኔ ማሳለፉ፡፡
- በብጹእ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ተሠርተው በደርግ ዘመን መንግሥት የተወረሱባትንና ለ24 ዓመታት ያክል ሲደከምበት ቆይቶ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ዘመነ መንግሥት የተመለሱላትን ሁለቱን መንትያ ሕንጻዎች ከፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ሐላፊ በቅዱስ ፓትርያሪኩ አማካኝነት የባለቤትነት ሰነዱን በምልዓተ ጉባኤው ፊት መረከቧና የመሳሰሉት ናቸው፡፡
በአጀንዳ መልክ ተይዘው የቀረቡትን የቤተ ክርስቲያንና ሀገራዊ ጉዳዮች ምልዓተ ጉባኤው ተወያይቶ ከተማመነባቸው በኋላ ዉሳኔ የተላለፈባቸው መንፈሳዊና ማኅበራዊ እንዲሁም ወቅታዊ ጉዳዮችን በተላለፈው ውሳኔ መሠረት በሥራ ላይ ውለው እናይ ዘንድ ጠንካራና ወጥነት ያለው ክትትል ያሰፈልጋቸዋልና የአፈጻጸሙም ነገር ይታሰብበት እያልን ሙሉውን የቅዱስ ሲኖዶስ ጋዜጣዊ መግለጫ ከታች ባለው ክፍል ስለተያያዘ ታነቡት ዘንድ ጋብዘናል፡፡
የሀገረ ስብከቱ ሚዲያ ክፍል
በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 ድንጋጌ መሠረት ከግንቦት 14-ሰኔ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ የተካሄደውን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አስመልከቶ ከቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ፤
ግንቦት 13 ቀን 2011ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በጸሎት የተጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊና ማህበራዊ ጉዳዩች ላይ ለ18 ቀናት ሲመክር ቆይቶ በርካታ ማህበራዊና መንፈሳዊ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የሚበጁ ጠቃሚ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
በዚህም መሠረት፡-
- ለጉባኤው መክፈቻ የቀረበው ንግግር ቤተ ክርስቲያናችን ለምታከናውነው መንፈሳዊ ተግባራት በእጅጉ ጠቃሚ ሆኖ ስላገኘው በቀጣይ ለሚደረገው የሥራ ስምሪት መመሪያ በማድረግ ጉባኤው አጽድቋል፡፡
- ከግንቦት 2010 – ግንቦት 2011 ዓ.ም. በቋሚ ሲኖዶስና በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተወስነው የተላለፉ ጉዳዮች አፈጻጸማቸው በእጅጉ ውጤታማ መሆናቸውን ጉባኤው ተቀብሎ አጽድቋል፡፡
- የቋሚ ሲኖዶስ ሥልጣንና የሥራ አፈጻጸም አስመልክቶ ተከሰቱ በተባሉ የሥራ አፈጻጸሞችና ታዩ በተባሉ ግድፈቶች ጉባኤው በሰፊው ተነጋግሮ በቀጣይ ማንኛውም መንፈሳዊም ሆነ ማሕበራዊ ጉዳዮች ሕገ ቤተ ክርስቲያኑን መሠረት አድርጐ እንዲሠራ መመሪያ ሰጥቷል፡፡
- በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና በሌሎችም መላው አኅጉረ ስብከት እየታዩ ባሉ ችግሮች ላይ በመነጋገር፣ ለቀጣዩ የቤተ ክርስቲያናችን መልካም አስተዳደር ጠቃሚ ግብአቶችን ማግኘት እንዲቻል ችግሮቹን አጥንተውና ለይተው የሚያቀርቡ ብፁዓን አባቶችና ባለሙያዎች እንዲሰየሙ ተደርጓል፡፡
- ከአገር ውጭና በአገር ውስጥ ባሉ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ተከስተው የነበሩ ችግሮች በአጥኚ ልዑካን ተጣርቶ በቀረበ አጀንዳ ላይ በመነጋገር ለአብያተ ክርስቲያናቱ መፍትሔ ይሆናል የተባለ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡
- የቤተ ክርስቲያኒቱ ቤቶችና ሕንጻዎች ሆነው ሳለ ያለአግባብ ተወርሰው የነበሩ በመንበረ ፓትርያርኩ ኩታ ገጠም የሚገኙ ሕንጻዎች በክቡር የአገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር ቁርጠኛ አመራር በመመለሳቸው፣ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ መንግሥት ለቤተ ክርስቲያናችን መብት መጠበቅ የሰጠውን ትኩረት በማድነቅ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ከፍተኛ ምስጋና አቅርቧል፡፡
- በውጭ አገር የሚገኙ አህጉረ ስብከትን በማጠናከር መንፈሳዊና ማህበራዊ አገልግሎታቸውን ማስፋፋት እንዲቻል ከቃለ ዓዋዲው ጋር እና ከየአገሮቹ መንግሥታት ሕግ ጋር የተጣጣመ ደንብ እንዲዘጋጅና ለጥቅምቱ 2012 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንዲቀርብ ተወስኗል፡፡
- ለተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት፣ ለአብነት ት/ቤቶች፣ ሰው ሠራሽ አደጋ ለደረሰባቸው አብያተ ክርስቲያናት፣ ለተፈናቀሉ ወገኖች፣ ለጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕንጻ ማደሻ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል፡፡
- መንግሥት ዜጐች እንዲቆጠሩ በያዘው መርሐ-ግብር መሠረት የቤተ ክርስቲያኒቱ ተከታዮች በትክክል እንዲቆጠሩ፣ ቆጠራውም በሰላም እንዲከናወንና አገራዊው ተልዕኮውም እንዲሳካ በየአህጉረ ስብከቱ ትምህርት እንዲሰጥ አስፈላጊውም ክትትል እንዲደረግ የኮሚቴ አባላት እንዲሰየሙ ተደርጓል፡፡
- በጉባኤው፡- “ግጭቶችና አፈታታቸው በዓለም አቀፍና በአገር አቀፍ እይታ” በሚል ስለ ወቅታዊ የሀገራችን ሰላምና ሊደረግ ስለሚገባው ሐዋርያዊ ተልዕኮ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ በስፋት በመነጋገር በአገራችን ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲያድግ፣ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ ልማት እንዲጐለብትና ድኀነት እንዲወገድ በሁሉም አቅጣጫ መሥራት እንደሚያስፈልግ ለሚመለከታቸውን ሁሉ ቅዱስ ሲኖዶስ አሳስቧል፡፡
- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ሆነው በከፍተኛ ትምህርት ቤቶች በሚቆዩባቸው ዓመታት ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸው ተከብሮ፣ የእምነት ነጻነታቸው ተረጋግጦ፣ እንደ እምነታቸው ሥርዓት በዓመት ውስጥ ባሉ ሰባት አጽዋማት የመጾም መብታቸው ተጠብቆ፣ አስፈላጊው አቅርቦት እንዲደረግላቸው፣ ሃይማኖታዊ በዓላትንም በሚያከብሩበት ጊዜያት የኖረና የቆየውን ትውፊታዊ አልባሳትን የመልበስ መብታቸው እንዲጠበቅ ለየኮሌጆቹና ዩንቨርሲቲዎች የቅዱስ ሲኖዶሱ ማሳሰቢያ እንዲደርሳቸው ወስኗል፡፡
- የአገራችንን የቱሪስት መስህብነት ምክንያት በማድረግ ዜጐች በቅድስናና በፈሪሃ እግዚአብሔር ተከብረው የሚታወቁባት የአገራችንን ታሪክ የሚቀይር የዜጐችን መልካም ሥነ-ምግባር የሚለውጥ ሕገ ተፈጥሮንና የተቀደሰውን ሥርዓተ ጋብቻን የሚያበላሽ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የተወገዘ ግብረ-ሰዶምን በአገራችን ለማስፋፋት፣ በዚህም የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ቅድስና የሚጐዳ ሕገ-ወጥ ተግባር ለመፈጸም፤ መቀመጫውን በአሜሪካን ሀገር ያደረገው የግብረ-ሰዶማውያን አስጐብኚ ድርጅት በመቃወም ወደ ቅድስት አገራችን ኢትዮጵያ እንዳይገባ፣ ቅዱሳት መካናትንም እንዳይጐበኝ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አውግዟል፡፡
የሀገራችን ዜጐች ኦርቶዶክሳውያን ምእመናንም ከእንዲህ ዓይነት የአገራችንን መልካም ገጽታና መልካም ሥነ-ምግባርን ከሚያበላሽ፣ በሃይማኖት ትምህርት ተጠብቆ የቆየው ባህላችንን ከሚያጠፋ፣ የሀገርና የቤተ ክርስቲያን ጠላት ከሆኑ ወራሪዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ፣ በአገራችንም ይህንን ሕገ-ወጥ ተግባር በመደገፍ እየተባበሩ ያሉት ግለሰቦችና ድርጅቶች ሁሉ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ቅዱስ ሲኖዶስ አበክሮ ያሳስባል፡፡
- ወቅታዊውን የቤተ ክርስቲያን ችግር አስመልክቶ በስፋት ሲነጋገር የሰነበተው ጉባኤ፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንና በምእመናን ተከታዮቿ ላይ እየደረሰ ያለው ፡-
- የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠል፣
- የክርስቲያኖችን መገደል እና ከቄያቸው መፈናቀል፣
- በሃይማኖታቸውና በሃይማኖታዊ ሥርዓታቸው ላይ ተጽእኖ ማድረግ፣
- የአብያተ ክርስቲያናት ነባር የይዞታ ቦታዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ መቀማት፣
- ለቤተ ክርስቲያኒቱ ማህበራዊና ልማታዊ ተግባር በጐ-ፈቃድ አለማሳየትና የመሳሰሉት ሪፖርቶች ከየአህጉረ ስብከቱ ቀርበው ጉባኤው በሐዘን ተመልክቶታል፡፡
በዚሁ ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ አገሪቱንና ሕዝቡን ይመራሉ ተብለው አደራ ለተቀበሉ የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪዎች ሁሉ ማዕከላዊው መንግሥት አስፈላጊውን መመሪያ እንዲሰጣቸው ቅዱስ ሲኖዶስ ጠይቋል፡፡
- በየሦስት ዓመቱ በቅዱስ ሲኖደስ ምልዓተ ጉባኤ የሚመረጡ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ምርጫ አስመልክቶ በሰፊው በመወያየትና አስፈላጊውን ጥናት በማድረግ፡-
- ብፁዕ አባ ዮሴፍ የምሥራቅ ጐጃም ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣
- ብፁዕ አባ ያሬድ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ በማድረግ ለቀጣይ ሦስት ዓመታት እንዲሠሩ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሰይሟል፡፡
ከዚህም ጋር አዲስ የሀገረ ስብከት ደረጃ የተሰጣቸው ዞኖችና መምሪያዎች ላይ ብፁዓን አባቶችን መድቧል፡፡
15. ሀገራችን ኢትዮጵያ ከጥንት ከመሠረት ጀምሮ “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” የሚለውን መርህ ተከትላ፣ ሰላሟን፣ ፍቅርዋንና አንድነትዋን ጠብቃ፣ ከውጭ የሚመጡባትን ባእዳን ወራሪዎች በመመከት ክብርዋንና ልዕልናዋን ለረጅም ዘመናት ጠብቃና አስጠብቃ የኖረች፣ ወደፊትም በዚሁ ጸንታ የምትኖር ታላቅ ሀገር መሆኗ ይታወቃል፡፡
ሕዝቦችዋም በአሁኑ ዘመን የሚታዩትን ያልተለመዱ ባሕርያት በሰከነ መንፈስ ቆም ብለው በመምከርና በመወያየት ወደ ጥንተ ሰላምዋ እንድትመለስ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ከምትሰጠው መንፈሳዊ አገልግሎት በተጨማሪ በማሕበራዊው ዘርፍም ለሀገር ዕድገትና ለሕዝቦች ኑሮ መሻሻል፣ በተለይም ለሀገራዊ ሰላምና አንድነት በመቆም ድርሻዋን እንድትወጣ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ በላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ዓበይት ጉዳዮች ላይ ለ18 ቀናት ያህል በአገር አቀፍ ጉዳዮች በስፋትና በጥልቀት ሲወያይ ሰንብቶ ስብሰባውን በጸሎት አጠናቋል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!
አባ ማትያስ ቀዳማዊፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖ
ሰኔ 3 ቀን 2011 ዓ.ም
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ