የኢትዮጵያ ኦርቶዶስክ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን ሥርጭት አገልግሎት ድርጅት የበላይ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የተመራ የሥራ አመራር ቦርድና አስተዳደር ልኡክ ለብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ የአዲስ ዓመት መልካም ምኞቱን ገለጸ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶስክ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን ሥርጭት አገልግሎት ድርጅት የበላይ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የተመራ የሥራ አመራር ቦርድና አስተዳደር ልኡክ ለብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና ሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የአዲስ ዓመት መልካም ምኞቱን ገለጸ።
ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የምሥራቅ ና የሰሜን አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የመገናኛ ብዙኃኑ የበላይ ሐላፊ የተመራ ልኡኩ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ ጽ/ቤት በመገኘት ለብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ እና የሀዲያና ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንኳን ለ፳፻፲ወ፰ቱ ዓ/ም ዘመነ ቅዱስ ማርቆስ በሰላም በጤና አደረሰዎ በማለት መልካም ምኞቱን ገልጿል።
ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ሊቀ ጳጳስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን በበላይነት የሚመሩት ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ለመገናኛ ብዙኃኑ ብሎም ለሚዲያ ባላቸው መልካም መረዳት ምክንያት EOTC TV የሚጠናከርብትን በተለይም በጾመ ፍልሰታ ለማርያም ድጋፍና ትብብር እንዲደረግለት በማድረግ ትልቅ ሥራ እንደሠሩ ገልጸው አመስግነዋል።
በቀጣይም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቤተ ክርስቲያናችን ልሳን የሆነውን EOTC TV ቴሌቪዥን በአስፈላጊ በሚባለው ሁሉ ትብብርና ድጋፍ እንደሚቀጥል ተስፋቸውን ገልጸዋል።

ሙሉ መልእክታቸው እንደሚከተለው ይነበባል።
እንኳን ለ፳፻፲ወ፰ ዓ/ም ዘመነ ቅዱስ ማርቆስ በሰላም አደረሰዎ።
የዘመናት ባለቤት አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር እንኳን በሰላምና በጤና በመንበረ ጵጵስናዎ ጠብቆ ለ፳፻፲ወ፰ቱ ዓ/ም ዘመነ ቅዱስ ማርቆስ በሰላም አደረሰዎ እያልን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብዙኃን መገናኛ ስርጭት ድርጅት የሥራ አመራር ቦርድ፣አስተዳደር እና በሠራተኞች ስም የመልካም ምኞት መልእክታችንን ስናስተላልፍ ታላቅ ደስታ ይሰማናል።
ብፁዕነትዎ ባሳለፍነው ፳፻፲ወ፯ቱ ዓ/ም በአባትነት የሚመሯቸውን አህጉረ ስብከት፣ ካህናት እና ምእመናን በማስተባበር ለተቋማችን ያደረጉት የአባትነት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ዕውቅና የምንሰጠው የአባትነት ተግባር ነው።
የዚህ ዓይነቱ የቤተ ክርስቲያንን ተቋም የመደገፍ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠልም የቤተ ክርስቲያናችንን ሐዋርያዊ ተልእኮ ከዳር ለማድረስ ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው እምነታችን ጽኑዕ ነው።
ስለሆነም ብፁዕነትዎ እስከ አሁን አባታዊ አመራር በመስጠት ሲያደርጉልን እንደቆዩት ሁሉ በመጪው ፳፻፲ወ፰ቱ ዓ/ም ዘመነ ቅዱስ ማርቆስም ተቋማችን በገንዘብ፣ በቴክኖሎጂ ቁሳቁስ እና ተባብሮ በመሥራት የበለጠ የሚታገዝበትን መንገድ እንደሚያመቻቹልን በመተማመን በድጋሚ እንኳን ለ፳፻፲ወ፰ቱ ዓ/ም ዘመነ ቅዱስ ማርቆስ በሰላም አደረሰዎ በማለት የመልካም ምኞት መልእክታችንን እናስተላልፋለን።
ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ
የኢኦተቤ የመገናኛ ብዙኃን ድርጅት የበላይ ሐላፊና የምሥራቅና የሰሜን አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ጳጉሜን ፭/፳፻፲፯ ዓ/ም