የኢትዮጵያና የሱዳን የሕዝብ ለሕዝብ የሰላም ግንባታና የጋራ ጥቅም ግንኙነት የልዑካን ቡድን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ጋር ውይይት አደረገ
በማኅበራዊና ሃይማኖታዊ ዕሴቶች ዙሪያ የሕዝቦች ለሕዝቦች ሀገራዊ ግንኙነትን ለማበለፀግ ሲንቀሳቀስ የቆየው ሱዳናዊ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በሰላም ግንባታና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተውን ባህል አጠናክሮ ለመቀጠል ይቻል ዘንድ ቅዳሜ ግንቦት 6 ቀን 2008 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር በሚገኘው በምሳካዬ ኅዙናን ገዳም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተወካዮች ጋር ሰፋ ያለ ውይይት አካሂዷል፡፡
ይህ ታላቅ ሀገራዊ የሕዝብ ለሕዝብ የሰላም ግንባታና የጋራ ጥቅም ውይይት በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የተቋቋመው አቢይ ኮሚቴ ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡
በብፁዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት መልካም ፈቃድና የበላይ መመሪያ ሰጪነት ከተቋቋመው ዐቢይ ኮሚቴ መካከል አባሠረቀ ብርሃን ወልደ ሰሙኤል የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የትምህርትና ሥልጠና መምሪያ ዋና ኃላፊ፣ መልአከ ብርሃን ፍስሐ ጌታነህ፤መ/ኃ መሠረት አያሌው የጠ/አ/ኃ/ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ዋና ኃላፊ፣ አቶ ተስፋዬ ውብሸት የቤቶችና ሕንጻዎች ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ይገኙበታል፡፡
የምሳካዬ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም ጽ/ቤት መርሐ ግብሩ የሚካሄድበትን ማዕከል በማመቻቸትና አስፈላጊውን ሁሉ በማሟላት ከፍተኛ የሆነ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡
ይህ የሕዝብ ለሕዝብ የሰላም ግንባታና የጋራ ጥቅም ሱዳናዊ የልዑካን ቡድን ከ76 ያላነሱ አባላትን ያቀፈ ሲሆን በሀገራዊ የሰላምና የጋራ ጥቅም በማበልፀግ እንቅስቃሴው በኢትዮጵያ የስምንት ቀናት የጉብኝትና የውይይት ተግባር ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
የልዑካን ቡድኑ ከሱዳን ከፍተኛ የመንግሥት አመራር፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከምሁራን፣ ከንግዱ ማኅበረሰብ፣ ከአርቲስቶች፣ ከዩኒቨርስቲ ምሁራን፣ ከወጣቶች፣ ከሃይማኖት ተቋማት የተውጣጣ ሲሆን የሱዳን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤም የጉብኝቱ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ የሕዝቦች ለሕዝቦች የሰላም ግንባታና የጋራ ጥቅም ግንኙነት ቡድን በኢትዮጵያ ቆይታው ከኢትዮጵ ምድርባቡር ከፍተኛ ባለስልጣኖች፣ ከትራንስፖርት ምንስትር፣ ከአዲስ አበባ መስተዳደር፣ ከውጭ ጉዳይ ምንስትርና ከክልል ትግራይ ርዕሰ መስተዳደር ጋር ውይይት ማድረጉን ምንጮቻችን አረጋግጠዋል፡፡
በተጨማሪም የልዑካን ቡድኑ በትግራይ ክልል የአብራሃና አፅብሐ ውቅር ቤተ ክርስቲያንንና በአዲስ አበባ የተገነቡ የኮንዶሚኒየም ሕንጻዎችን ጎብኝቷል፡፡ የልዑካን ቡድኑ ለኢትዮጵያ 25 እስኮላር ቪፕ እንደፈቀደም ምንጮቻችን ገልፀዋል፡፡ የኢትዮጵያና የሱዳን የሕዝቦች ለሕዝቦች የሰላም ግንባታና የጋራ ጥቅም ግንኙነት ቡድን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር ያደረገው ውይይት በጉብኝቱ እና በውይይቶቹ በመርሐ ግብር ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን ለዚህ መርሐ ግብር ስኬት ያበረከታቸውን አስተዋፅኦ አስመልክቶ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት ንቡረዕድ ኤልያስ አብርሃ በሰጡት ማብራሪያ በኢትዮጵያና በግብፅ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን የተደረገውን የሰላም ግንባታና የጋራ ጥቅም ግንኙነት አስመልክቶ ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ከመጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን ሰዓት ድረስ ጠንከር ያለ አስተዳደራዊ አመራር በመስጠት ታላቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን ለዚህ የሕዝቦች ለሕዝቦች የሰላም ግንባታና የጋራ ጥቅም ግንኙነት ራሱን የቻለ ኮሚቴ ሰይማ ጉዳዩን ስትከታተለው ቆይታለች፡፡ ያሁኑ የልዑካን ቡድኑ መርሐ ግብር የተሳካ እንዲሆን ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡ የሕዝቦች ለሕዝቦች የሰላም ግንባታና የጋራ ጥቅም ግንኙነት እንዲፈጠርም ቤተ ክርስቲያናችን ጠንክራ ትሠራለች፡፡ የልዑካን ቡድኑም በሀገራችን ያሉትን የታሪክ ቦታዎችን፣ ትምህርት ቤቶችንና የልማት ተቋማትን ጎብኝቷል በማለት የልዩ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት ንቡረዕድ ኤልያስ አብርሃ ለዝግጅት ክፍላችን አብራርተዋል፡፡
በማያያዝም ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነተ ዋና ሥራ አስኪያጅና የወላይታ ዳውሮ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በጋራ ውይይት መርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት የቀደሙት አባቶቻችን ከጎረቤት ሀገራት ጋር ለታሪክ ዕድገት የውጭ ግንኙነታቸውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ጠብቀውና ተንከባክበው ለማቆየት መቻላቸው፣ በተለይም በመልካም ጉርብትና ከታወቀው ከሱዳን ሕዝብ ጋር ያለን ትስስር ከፍተኛና ታሪካዊ ነው፡፡ የኢትዮጵያና የሱዳን ሕዝቦች ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ ጀምሮ መነሻው ከኢትዮጵያ ምድር በሆነው በዐባይ ወንዝ ውሀ በጋራ ሲጠቀሙ ኑረዋል፡፡ ይህም ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ እንደሚዘልቅ ጥርጥር የለውም፡፡
በማናቸውም የዓለም ታሪክ ውስጥ ዓለም አቀፍ ግንኙነትና ወንድማማች ትስስር ምንጊዜም የነበረና የሚኖር ነው፡፡ የግንኙነቱ ደረጃ የተለያየ ይሁን እንጂ መንፈሳዊም ሆነ ሥጋዊ ዓለም በራሱ የተመሠረተ ግንኙነት አለው፡፡ ይህን ሀገራዊ ጉብኝት ሕዝቦችን ከጎረቤት ሀገራት ጋር የተሻለ ማኅበራዊና ሃይማኖታዊ ዕሴቶችን እንዲቀዳጅና እርስ በርሱ እንዲከባበር ለማድረግ ጉብኝቱ አመቺ ከመሆኑም ባሻገር ከምናዳርገውም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንደ አንድ ድጋፍ ይሆናል፡፡ በተለይም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ራሳቸውን፣ ጎረቤቶቻቸውንና ሀገራቸውን ለሚወዱ ለሚያበረታታና ለሚያነቃቃ ተግባር ዐቢይ ሚና የሚጫወት ነው፡፡ ከማንኛውም የአዳም ዘር ጋር ብቻ ሳይሆን የዚህች ውብና አስደናቂ ዓለም ጥበበኛ ፈጣሪ ከሆነው አምላካቸው ጋር እንዲቀራረቡ የሚረዳ ነው፡፡ እንደሚታወቀው የጋራ ጥቅም መርሆ የሆነው ከሰዎች ሁሉ ጋር አንድነት፣ ክብርና ዕኩልነት ሲኖር ነው የተሟላ ትርጉምን የሚያገኘው፡፡ እያንድአንዱ ማኅበራዊ ገፅታ ሲይዝ ብቻ ነው፡፡ ቀዳሚ በሆነውና ሰፊ ተቀባይነት ባለው ሁኔታ ሲታይ የጋራ ትቅሞች ሰዎች እንደ አገርም ሆነ አንደ ግለሰብ ወደግባቸው እንዲደርሱ ያደርጋቸዋል፡፡
የጋራ ጥቅም የሚጠበቀው የሕዝብ ለሕዝብ ሰላማዊ ግንኙነት ሲኖር ነው፡፡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም ባላቸው ድርጅቶች ከከተሞች፣ ከአካባቢዎችና ከመንግሥታት አንስተው የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች ባለፈው ባደረጉት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና የጉብኝት ልውውጥ ከታሪካዊ ጉዳዮች በሻገር በማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሲወያዩ ኢትዮጵያና ሱዳን በዐባይ ወንዝ በጋራ እንዲጠቀሙ አድርጎ ፈጣሪ አያይዞ የፈጠራቸው ሀገራት በመሆናቸው በዐባይ ውሃ በጋራ የመጠቀም ተፈጥሮአዊ መብት አላቸው፡፡
እግዚአብሔር በተፈጥሮ አንድ ያደረገውን ማንም ይህን ተፈጥሮአዊ ግንኙነት መቃወም ወይም መለያየት አይችልም፡፡ ይህ ጉብኝት ከሁሉም መልካም ጎረቤት ሀገሮች ያለውን ማኅበራዊ ግንኙነት ሁሉ የበለጠ ያጠናክረዋል፡፡ እንዲህ ዐይነቱን የመልካም አርአያ የሆነውን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዐወንታዊ መልኩ ይምትቀበለውና የምትደግፈው በመሆኑ እንኳን ወደምንኖርባት ኢትዮጵያ በሰላም መጣችሁ? በአንድ ዋንጫ የሕይወት ውሃ ቀድተን የምንጠጣበት የዐባይ መፍለቂያ ወደሆነችው ሀገራችን በመምጣታታችሁ ቤተ ክርስቲያን ደስተኛ ናት፡፡ ስለጋራ ልማትና በውስጧ ስላለው ሰላማችን ለመላው ሱዳንና ለዓለም እንድታበስሩ ስንነግራችሁ በታላቅ ወኔና ሀገራዊ ስሜት ነው፡፡
እግዚአብሔር የኢትዮጵያንና የሱዳንን ሕዝብ ይጠብቅልን በማለት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ሰፋ ያለ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ከሱዳናዊ የልዑካን ቡድን መካከል የአንድ ሃይማኖት ተቋም ተወካይ በብፁዕነታቸው የተላለፈውን የሰላም ግንባታና የጋራ ጥቅም ግንኙነት መልእክት አስመልክተው ባስተላለፉት ቃል የልዑካን ቡድኑ ከብፁዕነታቸው በተላለፈው መልእክት የረካ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በመጨረሻም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ለሱዳናዊ የሕዝቦች ለሕዝቦች የሰላም ግንባታና የጋራ ጥቅም ግኙነት ልዑካን ቡድን ልዩ ልዩ ስጦታዎችን ካበረከተላቸው በኋላ የምሳ ግብዣ በማድረግ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኖአል፡፡