የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የሥራ መሪዎች ለብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ደማቅ አቀባበል አደረጉላቸው

0746

                                በመ/ር ሣህሉ አድማሱ

ከሰኔ ሁለት ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥቅምት 2009 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት  የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ሆነው  እንዲሠሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በወሰነው መሠረት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት እና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎች ሠራተኞች በተገኙበት በሀገረ ስብከቱ የመሰብሰቢ አዳራሽ ቅዳሜ ሐምሌ 2 ቀን  2008 ዓ.ም በአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የሚገኙ በርካታ የሥራ ኃላፊዎች ለብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ደማቅ አቀባበል አድርገዋል፡፡
የአቀባበል መርሐ ግብር በተከናወነበት ወቅት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር ጎይቶኦም ያይኑ ባስተላለፉት መልእክት የአዲስ አበባ ከተማ ርእሰ መዲና እንደመሆንዋ መጠን በሀገረ ስብከት ደረጃም የብዙዎች ትኩረት የሚአርፉባት፣ በገቢም ምንጯ ከፍተኛ፣ በሰው ኃይል ፍሰትም ከፍተኛ ቁጥር የሚታይባት ከተማ ሆናለች፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በፋይናንስ አቅም ደረጃ ከሁሉም አህጉረ ስብከት በድምር በዕጥፍ ዕድገት እያስመዘገበ የሚገኝ ሀገረ ስብከት ነው፡፡ ይሁንና አብዛኛው ዕንቅስቃሴው እንደ ሀገረ ስብከት ከዘላቂ ሥራዎች ይልቅ አብዛኛው እንቅስቃሴው በጊዜአዊ ሥራዎች እንቅስቃሴ እንደሚሠራ ለሁሉም ግልፅ ነው፡፡ ሀገረ ስብከቱ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሆነ ገቢ ለመሰብሰብ ተችሏል፡፡
በሰላሙ ዙሪያም ከመቼውም በላይ የተሻለ መረጋጋት እንዳለ ግልፅ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ቢመጣም የሠራተኞች አጠቃላይ የገቢ መጠን ግን ከጊዜው እንጻር እድገቱ እናሳ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ስለሆነም ሀገረ ስብከታችን የሠራተኞችን የገቢ መጠን ለማሳደግ ጥናት እያካሄደ ይገኛል፡፡
ባጭር ጊዜም ተግባራዊ ይሆናል ብለን እናምናለን፡፡ በልማት እንቅስቃሴም ከጊዜአዊ የልማት ሥራዎች ይልቅ በዘላቂ የልማት ሥራዎች ትኩረት በማድረግ ሰፊ የሆነ የልማት ሥራዎች እንዲጀመር ዕቅድ እየተካሄደ ሲሆን በሚቀጥለው ሁለት ሶስት ወራቶች አዳዲስ የልማት ሥራዎች እንደምንጀምር ያቀድን መሆኑን መግለፅ እፈልጋለሁ፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችንና ቅዱስ ሲኖዶስ የሀገረ ስብከቱን የሥራ እንቅስቃሴ በትኩረት በመገንዘብ በተደራጀ መልኩ እንዲሠራ፣ የተሻለ ልማት እንዲፈጠር የብሉያትና የሐዲሳት ታላቁ ሊቅ የሆኑት አቡነ ሕዝቅኤል በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ረዳት ሊቀ ጳጳስ ሆነው በመመደባቸው ደስታ ተሰምቶናል፡፡

0713

በዕቅድ ላይ ያሉት ሥራዎችም ፍጻሜ እንደሚአገኙ ስናምን በአሁኑ ሰአት በሀገረ ስብከቱ ያለው የተሻለ መረጋጋትና ሰላም የተሻለ የልማት ፍሬ እንዲአፈራ የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴአችን በተሻለ መልኩ መቀጠል ይኖርብናል፡፡ ለዚህም ደግሞ ታላቁ የወንጌል ገበሬ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል መመደባቸው ታላቅ ዕድል ነው፡፡
ስለሆነም ብፁዕ አባታችን አቡነ ሕዝቅኤል እንኴን ደስ አልዎት? የሕክምና ሥራዎትን አጠናቅቀው እንኳን በሰላም መጡ በማለት መልካም የሥራ ጊዜ እንዲሆንልዎት በራሴና በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ስም በታላቅ ትህትና እገልጻለሁ ብለዋል፡፡
በመቀጠልም ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት መልእክት “ይትሬሣህ እግዚአብሔር በተግባሩ” እግዚአብሔር በሥራው ደስ ይለዋል፡፡ ዓለምንና ሰውን በመፍጠሩ ደስ ይለዋል፡፡ በሚሠራው ሥራ ሁሉ ይደሰታል፡፡ የእግዚአብሔር አምላክ ፍቃዱ ሆኖ በቅዱስ አባታችንና በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ በዛሬው ዕለት ወደ ሀገረ ስብከቱ ይዘናቸው የመጣነው ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ከእናንተ ጋር አብሮ ለመሥራትና ከቅዱስ አባታችን መመሪያ ለመቀበል ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንን የተቃናችና የጠነከረች ለማድረግ ከላይ እስከ ታች ባንድ ድምፅ ሆኖ በመግባባትና በመነጋገር አንድ ልብ ሆኖ መሥራት ያስፈልጋል፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሁሉንም አቀፍ የሆነ ብሔር ብሔረሰቦች ያሉባት ታላቅ ከተማ ናትና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መልካም አስተዳደር ካለው ሁሉም ሀገረ ስብከቶች የተቃኑ ይሆናሉ፡፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከተ የተቃና ከሆነና መልካም አስተዳደር ካለው ከዚህ እስከ ታች ድረስ ያለው መልአካምና የተስተካከለ ይሆናል፡፡
ስለዚህ አንድ ልብ በመሆን ከብፁዕ አባታችን ጋር በመሆን ባንድ ልብ ከተሠራ ባንድ ልብ ከደከምን ሁሉም ነገር የተስተካከለ ይሆናል፡፡ አሁንም የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ ብፁዕ አባታችን ወደ እናንተ መጥተዋል፡፡
ስለዚህ ባንድ ልብና ባንድ ቃል ሆናችሁ እንድትሠሩ አደራ እላለሁ፡፡ ሀገረ ስብከቱ የብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ልዩ ሀገረ ስብከት እንደመሆኑ መጠን በበላይነት የሚመሩት ቅዱስ አባታችን ናቸው፡፡
ስለዚህ ከቅዱስ አባታችን መመሪያ በመቀበል ከብፁዕ አባታችን አቡነ ሕዝቅኤል ጋር የተሻለ ሥራ ይሠራል ብለን እናስባለን፡፡ የጊዜው ሁኔታ አጠር ያለና የኩንትራት ሥራ ይመስላል፡፡ ይሁን እንጂ ለዚያውም ቢሆን የተሻለ ሥራ ከተሠራ የተቃና ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡
በመቀጠልም ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የጠቃላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የማይጨውና የደቡብ ምሥራቃዊ ትግራይ አዲግራት አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት መልእክት የዘመኑን ሁኔታ ስንመለከተው ተባብሮ መሥራት ነው ውጤታማ ሊአደርግ የሚችለው፡፡ ሰው ካልተባበረና አንድ ካልሆነ ምንም አይነት ውጤት ሊአመጣና ሊአስመዘግብ አይችልም፡፡ ለቤተክርስቲያናችን ዕድገት አንድነት ያስፈልጋል፡፡ ከላይም ከታችም ተደማምጦ መሥራት ያስፈልጋል፤ ለሥራውና ለራስም ሕይወት ሲባል ተደማምጦ መምራትን የመሠለ ነገር የለም፤ በዚህ ሰአት ቤተ ክርስቲያናችን ከእኛ ብዙ ቁም ነገር ትፈልጋለች፤ አባቶቻችን አንጀታቸውን አስረውና ጾማቸውን አድረው ምንም አይነት ምቹ ሁኔታ ሳይኖር፣ ለስለት፣ ለእሳት፣ ለመከራ ሕይወታቸውን እየገበሩ ይችን ቤተ ክርስቲያን ጠብቀው ከዚህ ደረጃ አድርሰዋታል፡፡ እኛ ግን እንደ አባቶቻችን  የተቀበልነው መከራ የለም፡፡ የአባቶቻችንን ሕይወት ወደ ኋላ ዘወር ብለን ማየት ከቻልን  ለቤተ ክርስቲያኒቱ የከፈሉት መስዋዕትነት እስከ ሕይወት ድረስ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱን እኛ ያገኘናት በነጻ ነው፡፡ ምክንያቱም መስዋዕትነቱን አባቶቻችን ስለከፈሉ ነው፡፡ ስደቱንም መከራውንም አባቶቻችን ከፍለውልናል፡፡ አባት ያበጀው ለልጅ ይበጀው እንደተባለው እነሱ ያበጁት ለእኛ መልካም ሕይወትንና መልካም ኑሮን ፈጥሮልናል፡፡ ስለዚህ አሁንም አቅም በፈቀደ የአባቶቻችንን ሕይወት መከተል ይገባናል፡፡ ምዕመናንን መጠበቅ አለብን፡፡ ቤተ ክርስቲያን ተራማጅ እንድትሆንና ራስ የነበረችው ቤተ ክርስቲያን ጅራት እንዳትሆን ልናስብ ይገባናል፡፡ እኛ በቁርጠኝነት እግዚብሔርን ካገለገልን እግዚአብሔር ዳገቱን ሜዳ፣ ጨለማውን ብርሃን አድርጎ በዚህ ሂዱ ይለናል፡፡ ለሥራችን እንቅፋት የሆነውን ሁሉ ያስወግድልናል፡፡ ዘመኑ ጥሩ ነው፡፡ እኛም እድለኞች ነን፡፡
ስለዚህ ተግባብቶና ተደማምጦ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን በዚህ ቦታ ላይ ለሶስት ጊዜና ለአራት ጊዜ አባቶችን ለማድረስና ለእናንተ መመሪያ ለመስጠት ተመላልሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ ከዚህ በኋላ አባቶችን ለማድረስና ለእናንተ መመሪያ ለመስጠት መምጣት የለባቸውም፡፡ የእናንተን የሥራ ውጤትና የሥራ ሪፖርት ለመስማትና ልጆቼ በርቱ ለማለት፣  ለመባረክ ነው መምጣት ያለባቸው፡፡ ማመን ያለብን በሰው ቅያሬ አይደለም፤ በሥራው ቅያሬ እንጂ፡፡ ሰው በመቀያየርና በመለዋወጥ ለውጥ ሊመጣ አይችልም፡፡ ሥራውን ጠንክሮ በመሥራት ነው ለውጥ ሊመጣ የሚችለው፡፡ ሁሉም ሰው ጠንክሮ ከሠራ ለውጥ ሊመጣ ይችላል፡፡ የእግዚአብሔርም የሕዝብም አደራ አለብን፡፡ ሕዝብ ባይጠይቀን እግዚአብሔር ይጠይቀናል፡፡ እግዚአብሔርም ባይጠይቀን ሕዝብ ይጠይቀናል፡፡
ስለዚህ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ጠንክረን መሥራት ይኖርብናል፡፡ በዚህ ዘመን የሚነፍሰው ነፋስ ከባድ ነው፡፡  ስለዚህ ነፋሱን ማስቆም አለብን፡፡ ነፋሱን ለማስቆም ሁሉም ራሱን ማዘጋጀት አለበት፡፡ ክፉ ነፋስ አለ ደግም ነፋስ አለ፡፡ ጤና የሚሆን ንፋስ አለ በሽታም የሚሆን ነፋስ አለ፡፡ የአዲስ አበባ ምዕመናን ለገጠሩ ገዳማትና አድባራት ተደራሽ ናቸው፡፡
ከአዲስ አበባ የሚመነጨው ምንጭ ጎርፉ እስከ ገጠር ይደርሳል፡፡ ስለዚህ ከላይ እስከ ታች ሰላምንና አንድነትን ይዘን በጊዜአችን መሥራት ያለብንን መሥራት አለብን፡፡ ሰው የሚከበረው በሥራው ነው፡፡ አግዚአብሔርም የሚሠሩትን ይወዳል፡፡ መንግሥተ ሰማያትም ቢሆን፣ ገነትም ቢሆን ለመግባት መልካም ሥራ ያስፈልጋል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ ሕዝቅኤልም ወደ ሀገረ ስብከቱ ለሁለተኛ ጊዜ ነው የመጡት፡፡ ብፁነታቸው የመጡት ለሥራ ነው፡፡ ይህ ደግሞ መልካም ዕድል ነው፡፡ የቅዱስ አባታችንና የቅዱስ ሲኖዶስ መልካም ፈቃድ ሆኖ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ሆነው እንዲሠሩ ፈቅዷል፡፡ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የወንጌል ገበሬ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከብፁዕ አባታችን ጋር ተባብራችሁ መሥራት አለባችሁ፡፡ የቀይ ላም ወተትና የጥቁር ላም ወተት በአንድ ላይ ቢቀላቅሉት ልዩነት አያሳይም፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ሁላችንም የቤተ ክርስቲያንዋ ልጆች ነን፡፡ አንዱ የእንጀራ ልጅ፣ ሌላው ገለልተኛ አንዱ ቀራቢ፣ አንዱ ወገን መሆን አይገባንም፡፡ ቋንቋችን የቤተ ክርስቲያን ቋንቋ መሆን አለበት፡፡ ቋንቋችን አንድ፣ እምነታችን አንድ፣ ሥራችን ቤተ መቅደስ ነው፡፡ ተለያይተን ላንለያይ በማንኛውም አቅጣጫ ያልሆነ ቋንቋ ሊኖረን አይገባም፡፡ የሥራ ቋንቋ ብቻ ነው ሊኖረን የሚገባው፡፡ አሮጌው ዘመን አልፎ አዲሱ ዘመን የሰላም ዘመንና የሥራ ዘመን ሊሆን ይገባል፡፡ ብፁዕ አባታችን አቡነ ሕዝቅኤል እንኳን ደስ አለዎት ሳይሆን የምንላቸው እግዚአብሔር ያስችልዎት ነው የምንላቸው፡፡ ለብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የሰላምና የሥራ ዘመን ያድርግላቸው ብለዋል፡፡
ከብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ መልእክት በመቀጠል ለጉባኤው መልእክታቸውን ያስተላለፉት ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ የከፋ ሸካ ቤንችና ማጂ አህጉረ ስብከትና በአዲስ አበባ  ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ  ረዳት ሊቀ ጳጳስ የሚከተለውን መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ “አንትሙ ማኅተምየ ለመጻሕፍትየ” እናንተ የመጻሕፍቶቼ ማኅተም ናችሁ ይላል መጽሐፍ፡፡ ደብዳቤ ተጽፎ ማኃተም ከሌለው ተቀባይነት የለውም፤ አደራሻው አይታወቅምና፡፡ ይህንን ያልኩበት ምክንያት እናንተ በአዲስ አበባ ውስጥ የምትገኙ አስተዳዳሪዎች የቤተ ክርስቲያንዋ መታወቂያዎች ናችሁ፡፡ ሊቃውንትም ናችሁ፡፡ ያለውንም የሌለውንም፣ የሞላውንም የጎደለውንም የምታውቁ ስለሆናችሁ ለማለት ያህል ነው፡፡ ቃሉን የተናገረው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ነው፡፡ “ወናሁ ሳልስየ እንዘእመጽእ ኃቤክሙ” ወደ ናንተ ስመጣ ይህ ሶስተኛ ጊዜዬ ነው በማለት የተናገረው ቃል ነው፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ሊቃነ ጳጳሳትን እየያዙ ወደ እዚህ ቦታ ሲመጡ ሶስተኛ ጊዜአቸው ነው፡፡ ሶስት ጊዜ ያመላለሳቸው ችግር ምን ይሆን? የዚህን ትርጉም ሁላችሁም ታውቁታላችሁ ሶስት ጊዜ ተመላልሰው በሶስተኛው ከተረጋጋ መልካም ነው፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን በሶስትነት ታምናለችና ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ባንድነትም በሶስትነትም ታምናለች፡፡ አንድነትንና ሶስትነትን የማያምን ከሥላሴ ልጅነት የለውም፤ የመንግሥተ ሰማያትም ዜጋ አይደለም፡፡ ይህን ምሳሌ ያመጣሁት አብሮ ለመሥራት ነው፡፡ አብሮ መሥራት ደግሞ እንደቀላል ነገር የሚታይ አይደለም፡፡ ሀገረ ስብከቱን ከችግር ውስጥ ልናስገባው አይገባንም፡፡ ሀገረ ስብከቱን ከችግር ውስጥ የምናስገባው ለእኔ የሚል ጥያቄ ስለሚበዛ ይመስለኛል፡፡ ለቤተ ክርስቲያንዋ የሚል ጥያቄ ከበዛ ችግሮች ሊፈጠሩ አይችሉም፡፡ ለእኔ የሚል ካለ ሰላም ሊመጣ አይችልም፡፡ ሰላም ከሰማይ ሊወርድ አይችልም፡፡ ሰላም ከመሬትም የሚመነጭ አይደልም፡፡ ሰላም በአንደበታችን ተናግረን፣ በእግራችን ተራምደን የምናመጣው ይሆናል፡፡ ጥፋትን አንደበታችን ያመጣል አንደበታችንም ብቻ ሳይሆን እጃችንም እግራችንም ጥፋትን ሊአመጣ ይችላል፡፡ እጅም እግርም ከተሰበሰበ ግን ሰላም በአካባቢው ሊሰፍን ይችላል፡፡ በዚህ ሐሳብ ካልተግባባን ሰላም ሊመጣ አይችልም፡፡ ሰላም ሳይኖር ሰላም ሰላም ትላላችሁ ሰላም ግን ከእናንተ ርቋል ይላል ነቢዩ ኤርምያስ የአዲስ አበባ ገዳማትንና አድባራትን እኔም አውቃቸዋለሁ፤ እነሱም ያውቁኛል፤ ነገር ግን መተዋወቁ ብቻ ሳይሆን ልብ ለልብ ተገናኝቶ መሥራቱ ለሥራችን ውጤት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ የምናገላግለው ሰውንም እግዚአብሔርንም ነው፡፡ ይህች የምናገለግላት ቤተ ክርስቲያን በማንም ደም አልተመሠረተችም፡፡ የተመሠረተችው በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነው፡፡ መሠረቷም ጉልላቷም ክርስቶስ ነው፡፡ የመሠረታትም ደሙን አፍስሶ ነው፡፡
የማንም ደም ጠብ አላለላትም፡፡ ሐዋርያትም ሰማዕታትም ደማቸውን አፍስሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ እነሱ  ደማቸውን ያፈሰሱት መሪያቸውን ክርስቶስን ተከትለው ነው፡፡ የክርስቶስ ደም መሠረት ሲሆን የነቢያት፣ የሐዋርያት የሰማዕታት ደም ለቤተ ክርስቲያናችን እንደ አርማታና እንደ ስሚንቶ ነው፡፡ ሲምንቶውንና አርማታውን ቀጥ አድርጎ እንደ ሚያአቆመው የክርስቶስ ደምም ቤተ ክርስቲያንን ቀጥ አድርጎ አቁሟታል፡፡ ነቢያት፣ ሐዋርያትና ሰማዕታት የክርስቶስን ደም መሠረት አድርገው ወንጌልን አስተምረዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን እስከ አሁን ድረስ ጸንታ የኖረችው በክርስቶስ ደም ነው፡፡ ወደፊትም ጸንታ ትኖራለች፡፡ ክርስቶስ በደሙ የመሠረታትን ቤተ ክርስቲያን እንግፋት የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡  ነገር ግን እንግፋት የሚሉት እነሱ ተገፍተው ሲውድቁ እንጂ ቤተ ክርስቲያንን ገፍተው ሲጥሏት አላየንም፡፡
ምክንያቱም እግዚአብሔርን ገፍቶ የሚጥል አካል የለምና ነው፡፡ እገፋለሁ የሚል ሁሉ ተገፊ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ከማንታገለው ጋር ትግል እንዳንገጥም አደራ እላለሁ ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን የማጠቃለያ መልእክትና አባታዊ መመሪያ በሰጡበት ወቅት “አንትሙ ወእቱ ብርሃኑ ለዓለም” እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤ ብርሃናችሁ በሰው ሁሉ ፊት ይብራ በማለት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  እንዳስተማረው እኛ የዓለም ብርሃን ተብለናልና ብርሃናችን በዓለም ላይ፣ በቤተ ክርስቲያን ላይ፣ በሕዝብ አእምሮ ላይ እንዲአበራ ነው ክርስቶስን የምንለምነው፡፡ ዛሬ ብፁዓን አባቶች ያስተላለፉት መልእክት እርካታን የሚሰጥና አእምሮን የሚአድስ ነው፡፡ ብፁዓን አባቶች ያስተላለፉትን መልእክት ልንሠራበትና ልንጠቀምበት ይገባናል የተላለፈው መልእክት ለቤተ ክርስቲያን የሚገባና ጆሮአችን ሊአዳምጠው የሚገባ መልእክት ነው፡፡
ለቤተ ክርስቲያን የሚአስፈልጋት በመጀመሪያ አምልኮተ እግዚአብሔር ነው፡፡ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለን ከሆን ሁሉንም ሥራ አስተካክለን መሥራት እንችላለን፤ አንድነታችን ሁሉንም ነገር ያስተካክለዋል፤ ተስማምቶ፣ ተግባብቶና ተመካክሮ መሥራት ሁሉንም ነገር ያስተካክለዋል፤ ቤተ ክርስቲያናችንም የምትፈልገው ይህንኑ ነው፡፡
ከዚህ ውጭ ያለውን ነገር ራሱ እግዚአብሔር ያስተካክለዋል፡፡ በተላለፉት መልእክቶች መሠረት ሁላችንም አንድ አካልና አንድ አምሳል ሆነን በመግባባት ከሠራን ሰላሙም ይመጣል፡፡  እግዚአብሔርም ምሕረቱን ያወርዳል፡፡ ሰላሙም፣ ፍቅሩም፣ ጠቡም በእጃችን ውስጥ ነው ያለው፤ እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥረው ባለ አእምሮ አድርጎ ነው የፈጠረው፡፡ ራሱን እንዲመራና እራሱን እንዲአስተዳድር ሰፊ አእምሮ ሰጥቶታል፡፡
ስለዚህ እግዚአብሔር በሰጠን አእምሮ ከተመራንና ከሠራን የሚመጣብን ችግር የለም፡፡ በአዲስ አበባ በየጊዜው ብዙ ነገር ይነገራል፡፡ በዚህ ዘመን እንደዚህ ሆነ፣ በዚህ እንዲህ መጣ፣ እንዲህ ተፈጠረ እየተባለ ብዙ ነገር ይነገራል፡፡ ይህን ሁሉ እኛው ልናስተካክለውና ልንፈታው የምንችለው ነገር ነው፤ ሰላምን ልናመጣው የምንችለው እኛው ነን፡፡
ስለዚህ ከሁሉ በፊት እርስበርሳችን ተስማምተን፣ ተፈቃቅረንና ተማምነን ለአንድ እግዚአብሔርና ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን መሥራት አለብን ብለን ከወሰንን ሁሉም ሰላም ይሆናል፡፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለሁሉም አህጉረ ስብከት የሰላም ምልክት መሆን አለበት፡፡ አዲስ አበባ ለመላው የኢትዮጵያ አህጉረ ስብከት የሰላም መሪና ምልክት ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ አለብን፡፡ ሥራ ሲሠራ ጥፋት ሊፈጠር ይችላል፤ ነገር ግን ጥፋት የምንለው አውቆና ሆን ብሎ ጥፋት ሲፈጸም ነው፡፡ ሰው በእግዚአብሔር ዘንድ የሚፈረድበት አውቆ ሲአጠፋ ነው፡፡ እንስሳት ሲአጠፉ አይፈረድባቸውም፤ ምክንያቱም ሳር በልተውና ውሃ ጠጥተው መግባትን ብቻ ነው የሚአውቁት እንጂ አውቀው የሚአጠፉት ጥፋት የለባቸውም፡፡ እኛ ግን ስንፈጠር አዋቂ ሆነን ነው፤ መልካሙንም መጥፎውንም ለይተን የምናውቅ ነን፡፡
ስለዚህ እያወቅን ካላጠፋን በስተቀር ሁሉንም እናውቃለን፡፡ ስናጠፋ ህሊናችን ይወቅሰናል፡፡ ነገር ግን ግዙፉ ሥጋችን እየጎተተን ሥጋዊውን ሥራ እንሠራለን፡፡ ሥጋ ሥጋዊ ሥራ ይሠራል፡፡ ትልቁንም ትንሹንም፣ ጧትም ማታም እየተመካከርን ከሠራን መጥፎ ነገር ሁሉ ይጠፋል፤ ብፁዕ አቡነ ሣዊሮስ የብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ሥራ የኩንትራት ሥራ ነው በማለት ሲናገሩ ሰምተናል፡፡
ይሁን እንጂ መልካም ሥራ ከተሠራ ኩንትራት ሊራዘም ይችላል፡፡ ኩንትራት የሚቀየረው ጥፋት ሲፈጸም ብቻ ነው፡፡ በሥራ ዓለም ላይ ኩንትራት ማራዘም የተለመደ ነው፡፡ ስለዚህ ለማን ሊሆን ነው? ማንስ ሊመጣ ነው? ሰው ጥሩ ሥራ ከሠራ የበለጠ ኃላፊነት ሊሰጠው ይችላል፡፡ ሁሉንም የሚመራው መልካም ሥራ ነው፡፡ ስለዚህ የሚአስመሰግን ሥራ መሥራት አለብን፤ ከላይ እስከ ታች ሁላችንም መልካም ሥራ ለመሥራት ኃላፊነት አለብን፤ መልካም ሥራ ለመሥራት መንፈሳዊ ግዴታም አለብን፤ ቤተ ክርስቲያን የምትመሰገንበትን ሥራና እግዚአብሔር የሚመሰገንበትን መልካም ሥራ መሥራት አለብን፤ ካህናቱም፣ ሊቃውንቱም፣ ጳጳሳቱም የሚአስመሰግን ሥራ መሥራት አለብን፤ የቤተ ክርስቲያንን ስዕል በፊታችን አስቀምጠን እሱን እየተመለከትን ከሠራን ሁሉም ነገር የተቃና ይሆናል፡፡
ነገር ግን የቤተ ክርስቲያኒቱን ቅድስና እና ሕልውና ሳናስብ ለግል ኑሮአችን ብቻ ካሰብን ጥፋት ይመጣል፡፡ ሰው ለሚሠራው ሥራ ጥቅም ማግኘት አለበት፤ ነገር ግን ከተፈቀደለት ውጭ መፈለግ የለበትም ሕጋዊ ያልሆነ ነገር መፈለግ የለብንም፡፡
ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ለሁለተኛ ጊዜ መመደባቸው ጥሩ የሥራ ልምድ ይሆናቸዋል፤ ሰው ወደሚአውቀው ቤት ለመሄድ መንገድ ሳይጠፋበት ይደርሳል፡፡ ስለዚህ አዲስ አበባንና ውስጧን ማወቃቸው በትክክል እንዲሠሩ ያደርጋቸዋል፡፡ ሁላችንም በተናገርነው መሠረት አንድንሠራ እግዚአብሔር ይርዳን በማለት ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን መልእክታቸውን ካስተላለፉ በኋላ ጉባኤውን በጸሎት ዘግተዋል፡፡