የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ተወካዮች ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የእንኳን አደረስዎ መልእክት አስተላለፉ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር የሚገኙ የገዳማትና አድባራት ተወካዮች ቅዳሜ ታህሳስ 30 ቀን 2008 ዓ.ም ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት ጀምሮ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በመገኘት ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘንበረ ተክለሃይማኖት የእንኳን አደረስዎ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በእንኳን አደረስዎ መርሐግብር ላይ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያው ኃላፊዎች እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የዋና ክፍል ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በመርሐግብሩ መጀመሪያ ላይ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀመዛሙርት “ኢትዮጵያ ትዌድሰከ እስመ አብራህከ በስብሐቲከ ኮከበ ሰመይናከ ማትያስ ፓትርያርክ” የሚል ያሬዳዊ ወረብ አቅርበዋል፡፡
ከዚያም በኋላ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የወላይታ ዳውሮ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባቀረቡት በጽሑፍ የታገዘ የእንኳን አደረስዎ ንግግር የእሳት ነበልባል የታጠቁ ቅዱሳን መላእክት በከብቶች በረት በተወለደው በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ልጅ ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ የተሸነፈ መሆኑን፣ የልደት በዓል እኛ ክርስቲያኖች ባለሟልነትን ያገኘንበት በዓል መሆኑን፣ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ታሪክ በቤተ ክርስቲያናችን ጉልላት ላይ ዘወትር ሲያበራ የሚኖር መሆኑን፣ እኛም በዚህ ታላቅ የልደት በዓል ወቅት በሽተኞችንና ችግረኞችን ልንረዳቸው የሚገባ መሆኑን፣ ዘመኑ ለብፁዕ ወቅዱስ አባታችን የልማትና የብልፅግና ዘመን እንዲሆንላቸው የላቀ ምኞት ያላቸው መሆኑን በመግለጽ መልእክት አስተላለፍዋል፡፡
ከዚያም ቀጥሎ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ከቅዱስነታቸው ፊት ቆመው የሚከተለውን ንግግር አሰምተዋል፡፡ “ወአመ በጽሐ እድሜሁ ፈነወ ወልዶ ወተወልደ እምብእሲት” (ገላ. 4÷4-6)
የሰው ልጅ ክብሩን ተገፎ ወደ ምድረ ፋይድ እንዲወድቅ ሲገፋ አምላካችን እግዚአብሔር ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ ሰውና መላእክት አንድ ሆነው እንዳመሰገኑት ሁሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም በየዓመቱ ታህሳስ 29 ቀን ይህንን ታላቅ በዓል ታከብራለች፡፡
ከበዓሉ ጋር በተያያዘ በቅዱስነትዎ አመራር ሰጪነት የተሠሩትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች በማስታወስ እንኳን አደረሰዎ እንላለን፡፡
እኛ የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች በአዲሱ ዓመት በቅዱስነትዎ አመራር ሰጪነት የተሠሩ ሥራዎችን ማለትም መስከረም 10 ቀን 2008 ዓ.ም በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የተቀጸል ፅጌ በዓልን ማክበርዎ፣ ከመስከረም 15-19 ድረስ የግብፅ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ለሆኑት ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስን ደማቅ አቀባበል እንዲደረግ አመራር መስጠትዎ፣ መስከረም 16 ቀን 2008 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ ተገኝተው አባታዊ ቡራኬና ትምህርተ ወንጌል መስጠትዎ፣ ከጥቅምት 8-11 ቀን 2008 ዓ.ም የተካሔደውን 34ኛ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በሊቀ መንበርነት በመምራትና አባታዊ መመሪያ መስጠትዎ፣ ከጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ የቅዱስ ሲኖዶስን ጉባኤ በሊቀ መንበርነት መምራትዎና በድርቅ ለተጐዱ ወገኖቻችን ሁሉ እርዳታ እንዲደረግላቸው መመሪያ መስጠትዎ፣ ጥቅምት 18 ቀን 2008 ዓ.ም. በቅዱስ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው የተነገባውን ሕንጻ መርቀው ታቦቱ እንዲገባ ማድረግዎ፣ ኅዳር 14 ቀን 2008 ዓ.ም በደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ደብር ተገኝተው የተገነባውን ባለ 5 ፎቅ ሕንፃ መመረቅዎ፣ ኅዳር 18 ቀን 2008 ዓ.ም በጀሞ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው የመሠረት ደንጊያ ማስቀመጥዎ፣ ይህ ዓመት ችግሮች የተከሰቱበት በመሆኑ ችግሮችን ለማስወገድ ዓቢይ ኮሚቴ በማቋቋም የዕርዳታ ሥራ እንዲሠራ ማድረገዎ፣ ወደ አሜሪካ ያደረጉትን መንፈሳዊ ጉዞ አሳክተው ስለመጡ እኛ ልጆቼዎ እንኳን ደህና መጡ እንላለን፡፡
የቅዱስነትዎ ቡራኬ አይለየን በማለት አስተዳዳሪዎቹ ሰፋ ያለ ሪፖርት አቀርበዋል፡፡
በመቀጠልም “ወመላእክት ተጋቢኦሙ ሰፍሑ ክነፊሆሙ ወጸለሉ ላዕለ ማርያም” የሚል ያሬዳዊ ወረብ በዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ቀርቧል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የሚከተለውን አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ሰላምታ ለመለዋወጥና ይህችን የተቀደሰች ዕለት የሰጠን እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፡፡
“… የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ የተቀበሉትን ሥልጣን ሰጣቸው” (ዮሐ. 1÷8) ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ዓለምን ያዳነ መሆኑን ላመኑት እና ለተቀበሉት የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣን ተሰጣቸው፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን አምነን ስለተቀበልን የሱ ልጆች ነን፡፡ ሕገ ወንጌልን ተቀብለን ክርስቲያኖች ተብለን ተጠርተናል፡፡ ከጠፋንበት ፈልጐ አምጥቶ ወደ ጥንተ ቦታችን መልሶናል፡፡ እኛም የጠፉትን መፈለግ አለብን፡፡ ምዕመናን ሃይማኖታቸውን እንዳይለውጡ ማስተማርና መጠበቅ አለብን፡፡ በችግራቸውም ጊዜ ፈጥነን ልንደርስላቸው ይገባናል፡፡
በ2008 ዓ.ም በዓለ ልደት ሰላማዊ ፀጥታ ያለው በዓል አክብረናል፡፡ በዓሉ የተከበረው ሰላም ስላለ ነው፡፡ ሰላማችን እንዲጠበቅ ሁላችንም ተግተን መሥራት አለብን፡፡ የሰላም ሐዋርያት መሆን አለብን፡፡ ለተራቡና ለተጠሙ ወገኖቻችን ለችግራቸው ማስወገጃ እርዳታ መስጠት አለብን በማለት ቅዱስነታቸው አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
{flike}{plusone}