የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ሰባክያነ ወንጌል ለመምህር ጎይቶኦም ያይኑ ደማቅ አቀባበል አደረጉላቸው

00345

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር የሚገኙ የገዳማትና አድባራት ሰባክያነ ወንጌል ለመምህር ጎይቶኦም ያይኑ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ለመጋቤ ጥበብ ናሁሠናይ በለጠ የሀገረ ስብከቱ የሰው ኃይል አስተዳደር ዋና ክፍልና ለአቶ ገ/ሕይወት አስገዶም የሀገረ ስብከቱ የሒሳብና በጀት ዋና ክፍል ኃላፊ ሰኞ ሚያዚያ 10 ቀን 2008 ዓ.ም ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
በትውውቅ አቀባበሉ መርሐ ግብር ወቅት መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ ባስተላለፉት መልእክት በገዳማቱና በአድባራቱ ሲከናወን የቆየው የአንድነት ጉባኤ ተገቢ የሆነ ውጤት አሳይቷል፡፡ ለስብከተ ወንጌሉ መጠናቀርና መስፋፋትም በባለሙያዎች እየተዘጋጀ የሚገኘው የሥልጠና ማንዋል ወደመጠናቀቂያው ደረጃ ደርሷል፡፡ የገዳማቱና አድባራቱ ዐውደምሕረቶች በሕጋውያኑ ሰባክያን ብቻ እንዲገለገሉ በመደረጉ  ተገቢውን ክብር እንዲጐናጸፉ ሆኗል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስንና የብፁዕ ወቅዱስ ፖትርያርኩን መመሪያ ለማስከበር ሲባል ከሕጉ ፈቀቅ ባሉ ክፍሎች ላይ አስፈላጊውን የማረም ርምጃ ተወስዷል፡፡ መመሪያውን ለመሻር ሙከራ ያደረጉ ክፍሎች ከስህተታቸው እንዲታረሙ ጥረት ተደርጓል፡፡ የሰባክያነ ወንጌል ቅጥር በጽሑፍ በተደገፈ የመመዘኛ ፈተና ተሰጥቶ ታአማኒነት ያለው የቅጥር ሂደት ተፈጽሟል፡፡ “ዐውደ ወንጌል ዘተዋሕዶ” በተሰኘው ጥናት ላይ አስፈላጊው ውይይት ሲደረግበት ቆይቷል፤ ውይይቱ ለወደፊቱም ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በአቀባበሉና በትውውቁ መርሐ ግብር ወቅት ከተገኙትና ብዛታቸው ከ200 በላይ ከሚደርሰው የገዳማትና አድባራት ሰባክያን በተሰጠው አስተያየት መምህር ጎይቶኦም ያይኔ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው በመመደባቸው በጣም ደስተኞች ነን፤ ምክንያቱም ስለስብከተ ወንጌል ብዙ የሚአውቁ ናቸውና፡፡ ተዳክሞ የነበረው የስብከተ ወንጌል ሥራ እንዲጠናከር ያደረጉትን መ/ሰ/ዳዊት ያሬድንም እናመሰግናቸዋለን፡፡ መምህር ጎይቶኦም ያይኑ በመቀሌ ከሣቴ ብርሃን፣ በሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስና በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጆዎች በኃላፊነትና በመምህርነት ሲሠሩ የቆዩ በመሆናቸው አሁን የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አሰኪያጅ ሆነው በመምጣታቸው ካላቸው የሥራ ልምድ አንጻር ከፍተኛ የሥራ ፍሬ ሊሳአዩ እንደሚችሉ እናምናለን፡፡
ለወደፊቱ ለሥራችን እንቅፋት የሚሆኑንን ነገር ለማስወገድ የጋራ ጥረት ማድረግ አለብን፤ ቤተክርስቲያን በራሷ ልጆችና በራሷ አውደ ምሕረት መጠቀም ጀምራለች /እየሠራች ነው/ የጀርባ /የኋላ/ ሰባክያን ዙሩን ለማክረር ጥረት እያደረጉ ናቸው፤ የቅዱስ ሲኖዶስን መመሪያ ማስከበር አለብን ለቤተክርስቲያናችን ጠበቆች ሆነን መሥራት ይኖርብናል፡፡ ከዘርና ከወገንተኝነት የጸዳ አገልግሎት መስጠት አለብን፤ የቤተ ክርስቲያን ቁልፍ በእኛ እጅ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ቤተክርስቲያን የማታውቃቸው ሰባክያን ቤተክርስቲያንን በእጅጉ ሲፈታተኑአት ቆይተዋል፡፡ በአንድ አንድ አድባራት ማይክ የሚነጥቁ፣ ቢሮ የሚአሽጉ ሰዎች ነበሩ፡፡
እነዚህ ድንኳን ሰባሪዎች በአሁኑ ጊዜ ታግሰውልናል፤ የገዳማትና አድባራት አውደ ምሕረት ተከብሮል፤ ድንኳን ሰባሪዎቹ መመሪያ ሰጪዎችና ጉልበተኞች በመሆን ብዙ ሁከትና ብጥብጥ ፈጥረዋል፤ እነዚህ ሰዎች በማኀበራት የታቀፉ ግለሰቦች ሲሆኑ እኛ ያልጋገርነው እንጀራ አይጣፍጥም ይላሉ በማለት ሰባክያኑ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በመቀጠልም መጋቤ ጥበብ ናሁሠናይ በለጠ የሀገረ ስብከቱ የሰው ኃይል አስተዳዳር ዋና ክፍል ኃላፊ ባስተላለፉት መልእክት በፍቅር የሚኖር እግዚአብሔርን ያውቃል ተብሎ በቅዱስ መጽሐፍ ተጽፎል፡፡ ስለዚህ ሥራችን ሁሉ በፍቅር እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ እናንተ ሁላችሁ መምህራን ናችሁ፤ ለመምህር መመሪያ አይሰጥም፤ አውቆ ይሠራል እንጂ፤ የምንችለውን ያህል መሥራት አለብን፤ ጥፋት ሲፈጸም ተጠያቂዎች ነን፤ ቤተ ክርስቲያን የምታዘንን ነገር ለመፈጸም አይከብደንም፤ ሰባኪ የሆነ ሁሉ ከአልባሌ ቦታና ከመጥፎ ሥራ በመራቅ አርአያነት ያለው ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም መምህር ጎይቶኦም ያይኑ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ባስተላለፉት መልእክት የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት ምን እናድርግ ማለት አለብን ቅዱስ ሲኖዶስና ብፁዕ ወቅዱስ ፖትርያርኩ የሚአስተላልፉትን መመሪያ መፈጸምና ማስፈጸም አለብን፤ ቤተክርስቲያንን መጠበቅ አለብን፡፡ ቤተክርስቲያን የምትለውን ከሰማን በሕይወት እንኖራለን፡፡ ቤተክርስቲያናችንም ተከብራ ትኖራለች፡፡
አዲስ ነገር የለም፡፡ የነበረውንና የተላለፈውን መመሪያ አጠናክረን መቀጠል አለብን፡፡ መሪ ሊቀያየር ይችላል፡፡ ሥራው ግን አንድ ነውና ሥራውን በመፈጸም ተግተን መሥራት አለብን፡፡ ከላይ የሚተላለፈው መመሪያ የማባረርና የማገድ መመሪያ አይደለም፤ ሰዎች መመሪያውን ጠብቀው፣ በውስጧ ገብተው በሕጉና በሥርዓቱ እየተመሩ እንዲአገለግሉ የሚአግዝ ነው፡፡
የቤተ ክርስቲያን በር ሁል ጊዜ ክፍት ነው፡፡
እንደክርስትና የምናስብ ከሆነ የሚጠቅመን ከቤተክርስቲያን ጐን መቆሙ ነው፤ ከቤተክርስቲያን  ውጭ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ዋስትና የለንም፡፡ ሕዝቡ በፌስ ቡክና በጋዜጣ ጋራ እየተገባ ነው ያለው፤ የምንኖረው ባሳደገችንና ባስተማረችን ቤተክርስቲያን ውስጥ ነው፡፡ በመካከላችን ልዩነት ሊኖር አይገባም፤ በየገዳማቱና አድባራቱ የሚካሄደው የአንድነት ጉባኤ ለአንድነት ዓላማ ሊውል ይገባዋል፡፡ የቤተክርስቲያንን አንድነት መጠበቅ አለብን፤ የግል ዕቅዳችንን ማስቀደም የለብንም፤ የቤተክርስቲያንን ሐሳብና ዕቅድ ማስቀደም አለብን፡፡ በወንገል እንቅስቃሴአችን ላይ ወደ ፊት ብዙ እንወያያለን፡፡
ሕዝባችን መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ መረዳት እንዲችል ከምእምናን ቤት ድረስ ገብተን መስበክ የምንችልበትን ሁኔታ መፍጠር አለብን፡፡ የዛሬ 20 ዓመትም ሆነ ዛሬ 40,000,000.00 /አርባ ሚሊዮን/ ሕዝብ አለን ማለት ሳይሆን ምዕመናንን የምናጠናክርበት መንገድ መፍጠር አለብን የቁጥጥር ሥርዓታችንን ማስተካከል አለብን፡፡ የትምህርት ስህተት አለ በማለት ማለት  አስቀድመን ወደ ክስ ከመሄዳችን በፊትና ምዕመናን ግራ ከመግባታቸው በፊት ስህተቶችን የምናርምበትን ስልት መፍጠር አለብን፡፡ አንድ ሰው እንዳይጠፋ ተግተን መሥራት አለብን በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ላይ ማሳሰቢያ የሰጡት መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ የሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል ዋና ክፍል ኃላፊ ማስረጃ ሳይኖር እገሌ የሃይማኖት ህፀፅ አለበት ተብሎ መከሰስ የለበትም፡፡ ማስረጃ ካለ /ከተገኘ/ እንደቤተክርስቲያን ቀኖና ተጠርጣሪው በመጀመሪያ መመከር አለበት፡፡ ከዚያ አልመከረም ካለ በሊቃውንት ጉባኤ ጉዳዩ ታይቶ በቅዱስ ሲኖዶስ የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል ብለዋል፡፡