የአዲስ አበባ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን በተለያዩ የቤተክርስቲያናችን አርዕሰተ ጉዳዮች ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጡ
የአዲስ አበባ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ክቡር ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን ሐሙስ ታህሳስ 10 ቀን 2006 ዓ.ም ለአዲስ ቲቪ እና ለሌሎችም የሚዲያ ተቋማት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን በመወከል በሰላም፣ በሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችና በልማት አቅጣጫ ሰፋ ያለ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡ ሲሆን የመግለጫውን ሙሉ ቃል ከዚህ እንደሚከተለው አቅረበነዋል፡፡
መቀመጥ ጥፋት ነው፣ ወንጀልም ነው፣ ልማት በቤተክርስቲያን አዲስ ስላልሆነ ቤተክርስቲያን ባሕል አድርጋ ያቆየችውን እና የራሷ መገለጫዋ የሆነውን ልማት በዘመናዊ መልክ ሥራ ላይ ማዋል አለባት፡፡ ልማት እርሻ ብቻ አይደለም፡፡ የአክሱም ሀውልት፣ የላሊበላ ሐውልት እና ሌሎቹም የልማት መገለጫዎች ናቸው፡፡
ስለዚህ የእኔም አንዱ እቅድ በአዲስ አበባ ከተማ ልማት እንዲስፋፋ ማድረግ ነው፡፡ ልማቱም በባለሙያ እየተጠና በአባቶችም ይሁንታ እያገኘ የምንሄድበት ጉዳይ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ሠራተኞችን መጨመር አልፈልግም፤ ምክንያቱም በአዲስ አበባ ከተማ ያለው የሰው ኃይል ሙሉ ነው፡፡ እንዳውም ከበቂ በላይ በመሆን ትርፍ ሆኖ ነው ያለው፡፡ ምንም ይሁን ምን ያሉት ሠራተኞች ኑሮአቸው ተሻሽሎ፣ በቂ ደመወዝ አግኘተው እንዲኖሩ ነው፡፡ ካህናቱ በመንፈሳዊ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን በልማት ላይም እንዲሳተፉ ፕሮግራምና እቅድ ማውጣት ዋና ሥራችን ይሆናል፡፡
በመንፈሳዊ አገልግሎት ጊዜ እያገለገሉ ከዚያ ውጭ ደግሞ ሠርተው ኑሮአቸውን እንዲያሳድጉ ነው፤ ይህም ማለት የሠራተኛ ቅነሳ ሳይደረግ ያሉት ሠራተኞች የሚያስፈልጋቸው ሁሉ እንዲሟላላቸው ማድረግ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ካህናትን ከልመና ጋር የሚያያይዙ ሰዎች አሉ፤ በከጠር አካባቢ የሚማሩ በተለይም ወጣቶች ማለትም የቆሎ ተማሪ የሚባሉት በዚህ ነው የሚኖሩት፤ ሕዝቡ ተማሪዎችን የሚያስተምረው በልመና ነው፤ በዚህ ዘመን ግን ይህ አሠራር የሚያስኬደን አይደለም፡፡ ስለዚህ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ይህ መንፈሳዊ ትምህርት እዲካሄድ ማድረግ ነው፡፡
የእኔ መርሐ ግብር እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ከአባቶች ጋር በመመካከር ቤተክርስቲያን ምሳሌ እንድትሆን መሥራት ነው፡፡ አገልጋዮቿም ለሌሎች ምሳሌ እንዲሆኑ ነው፡፡ በየሰበካው ያሉ ምዕመናን ቤተክርስቲያናቸውን የሚያገለግሉበት አጋጣሚ አለ፡፡ በልማት በኮሚቴ ውስጥ በመመረጥ እና በተለያዩ የሕንጻ ግንባታ ኮሚቴ በመመረጥ ነው፡፡ ካህናት አባቶችም ቤተክርስቲያንን እየመሩ ያሉት ብቻቸውን ሳይሆን ከምዕመናን ጋር ሆነው ነው፡፡
ስለዚህ ይህ አሠራር ሊቀጥል የሚገባው እና በበለጠም ሊኬድበት ሚገባው መሆኑን ማረጋገጥ ነው፡፡ የሥነ-ምግባር ችግር ያለባቸውን ሰዎች በተመለከተም ከስንዴ ጋር እንክርዳድ እንደሚገኝ ሁሉ በቤተ ክህነትም ሆነ በቤተመንግሥት አካባቢ፤ በማህበራት ውስጥ ሰዎች ሁሉ እኩልና መልካም አስተሳሰብ አላቸው ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ አንዳንድ ሥነ-ምግባር የጎደላቸው ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ተደጋጋሚ የሥነ-ምግባር ችግር ያለባቸውን ሰዎች መለየት ያስፈልጋል፡፡
የመጀመሪያው መፍትሔ ማስተማር ነው፡ ከስህተታቸው እንዲታረሙ ምክር መስጠት ነው፡፡ ከዚህ በፊት ምክርና ተግሳጽ ተሰጥቷቸው ከሆነ አሁንም መስጠት ያስፈልጋል፡፤ ከዚህ በኃላ ግን የእርምት እርምጃ ሊወሰድ ይገባል፤ መንፈሳዊ ሕጋችን ይቅርና ሕዝቡ የሚተዳደርበት የወንጀል ሕግ የሚለው ሰዎች እንዲታረሙ ነው፤ አንድ ሰው እስር ቤት ወይም ጸባይ ማረሚያ ቤት ሲገባ ሕግ መበቀያ ሆኖ አይደለም፤ በመጀመሪያ ጥፋተኛው ሰው ከራሱ ጋር እንዲታረቅ ለማድረግ ነው፤ በቤተ ክርስቲያናችን አነጋገር ንሰሐ እንዲገባ ማለት ነው፡፡ መታረም በገዳማት ያለና የገዳማት ሥርዓት ነው፡፡ የገዳማት መነኮሳት በገዳሙ ሥርዓት ውሳኔ እየተሰጣቸው ይታረማሉ፡፡
የመታረም ሁለተኛው ክፍል የበደሏቸውን ሰዎች ይቅርታ እንዲጠይቃቸው ነው፤ ይቅርታ መጠየቅ በቃል ብቻ ሳይሆን መጸጸት እና ቅጣት ስለሆነ የተበደሉ ሰዎችም በዚሁ ይረካሉ፡፡
ሌላው መታረም ለሌሎቹ ምሳሌ መሆን ነው፡፡ ምክንያቱም ሌሎቹ ወደ ጥፋት እንዳይመለሱ ያደርጋቸዋል፤ አንድ ጥፋተኛ ጥፋት ሲፈጽም የሚበድለው የበደለውን ሰው፣ ሕዝብንና መንግሥትን ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ሁሉ ሲታረም ሀገር ሰላም ይሆናል ማለት ነው፡፡
የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ አይገባም ማለት ነው፡፡ እኛ በጸሎት ጊዜ አዘውትረን ውዳሴ ማርያም እንደምንደግመው መንግሥታችንም ሁልጊዜ አዘወትሮ ስለ መልካም አስተዳደር አዋጅ ያውጃል፤ በእኛ መሥሪያ ቤትም ይህን እወጃ ማድረግ አለብን ነው የምንለው፡፡ መልካም አስተዳደር በሌለበት ልማት የለም፣ መልካም አስተዳደር በሌለበት እኩልነት የለም፣ መልካም አስተዳደር በሌለበት ሕግ አይከበርም፣ መልካም አስተዳደር የሚመጣው ከመደማመጥ ነው፡፡ ሰዎች አንድ ጥፋት ባጠፉ ጊዜ ሲቀጡ አሳባቸውን ሲገልጹ ሕግን ተከትሎ መሆን አለበት፡፡ ሕግን ተከትሎ አቤቱታ ማቅረብ ይገባል፤ በእኛ መሥሪያ ቤት አወቃቀር ከአጥቢያ ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ቤተክህነት በየደረጃው የሥራ ኃላፊዎች አሉ፤ አቤቱታውም በየደረጃው ሲቀርብ የሕዝብን ጥያቄ ለመቀበል የግድ ነው፡፡
በወቅቱ ለጥያቄው መልስ ያስፈልገዋል፡፡ ጥያቄው ትክክል ከሆነ ትክክል ነው፣ ያልተረዳው ከሆነ ግን ማስረዳት የመልካም አስተዳደር ዋና መፍትሔ ነው፡፡ ሕዝብ የሚለውን ማድመጥ ይገባል፡፡ ግለሰቦች ሊሳሳቱ ይችላሉ የሕዝብ ጥያቄ ግን ስህተት አለው ተብሎ አይገመትም፡፡ ለምን ቢባል ሲጀመር ጀምሮ ሕዝብ ሰላምን ይፈልጋል፡፡ ከሰላም ውጭ ሌላ ሕይወት የለምና፡፡ ስህተት ያለባቸው ሰዎች ለመታረም ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ ይህ መታረም ይጠቅማቸዋል፡፡ መልካም ሠርተውም የሚታረሙ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ለምን ብለው ግን ማሰብ አለባቸው፡፡ እነ ቅዱስ ጶውሎስ፣ እነ ቅዱስ ጴጥሮስ፣ እነ ቅዱስ ዮሐንስ በመልካም ሥራቸው ቢታሠሩም ሰማይ ተከፍቶ እንደታያቸው እንረዳለን፡፡
የቀድሞው የደቡብ አፍሪካን ፕሬዝዳንት ኔሰን ማንዴላን ስንመለከት ብዙ ጊዜ በመልካም ሥራቸው ታስረው ነበር፤ ነገር ግን ኔሰን ማንዴል ላሰሯቸው ሰዎች ይቅርታ አድርገውላቸዋል፡፡ ምሳሌ መሆን ማለት እንዲህ ነው፡፡
በሕግ መታረም ማለት ለታራሚውም ለሌላው አካልም ትክክለኛ መሥመር መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ አንድ ሰው ሲቀጣ የሚቀጣው ሥጋው ወይም በድኑ አይደለም፡፡ የሚቀጣው መንፈሱ ወይም ሐሳቡ ነው የሚቀጣው፡፡ ለምሳሌ አንድ አእምሮውን የሳተ ወይም ያበደ ሰው ሲያጠፋ አይቀጣም፡፡ ምክንያቱም ጥፋቱን የፈጸመው አሳቦና አልሞ አይደለም፤ በሱ ውስጥ ያለው ክፉ መንፈስ ነው የሚቀጣው፤ ስለዚህ ስህተት የፈጸሙ ሰዎች መታረም አለባቸው፡፡ የሕግ ግንዛቤ የሌለው ሰው ስህተት ቢፈጽም ከሐገር ይባረር እንዲህ ይፈጸምበት አይባልም ከመጠን ያለፈ ቅጣትም መቅጣት ሰውየውን የሚያርም ሳይሆን በቀለኛ እንዲሆን ነው የሚያደርገው፤ እግዚአብሔር ከእኛ ምንድነው የሚፈልገው ብለን ማሰብ አለብን፡፡ ሌሎችን ሰዎች አስገድደን የእኛን እምነት እንዲከተሉ ማድረግ የምንፈልግ ሰዎች ካለን ተሳስተናል ማለት ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ወደ እኛ ካልመጡ መንግሥተ ሰማያት አንገባም የሚል አስተሳሰብም ካለ ተሳስተናል፡፡ ሃይማኖት የነጻነት ጉዞ ነው፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይከተሉ የነበሩ ሰዎች ወደ ኋላ ሲመለሱ ክርስቶስ ሐዋርያትን እናንተም ከፈለጋችሁ መሄድ ትችላላችሁ አላቸው፤ አንድ የሃይማኖት መምህር ብዙ ሰዎች መሳብ የሚችለው እራሱ ምሳሌ በመሆን ነው፡፡ አስገድዶና አታሎ የእምነቱ ተከታይ ማድረግ እግዚአብሔርም አይፈልግም፤ እውነተኛውን ትምህርት አስተምህሮና አሳምኖ ከዚያም በላይ ደግሞ እራሱ ምሳሌ ሆኖ የሚወደደ አለ፡፡ መልካም የሚያስብና መልካም የሚሠራ ሰው ሲገኝ ሁሉም የእርሱ ጓደኛ መሆን ይፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ጥሩ ሰው ስለሆነ ነው፡፡ ከጥሩ ሰው ጋር እግዚአብሔር አለ፡፡ ከዚህ ውጪ ግን አክራሪነት የእግዚአብሔር ፈቃድም አይደለም፤ ይልቁንም እራሱን አጥቷል፤ ጊዜውንም እያባከነ ነው የለው እንዲህ አይነቱ ሰው የአዕምሮ እስረኛ ነው፡፡ ሐሳቡ ወልጋዳ ስለሆነ ኑሮው በጭንቀት የተሞላ ነው፡፡
የእግዚአብሔርን መንግሥትም አያገኝም፡፡ ሰላማዊ ሰው ግን በምድርም በሰማይም ይደሰታል፡፡ በምድር ላይ የሠራነው ሥራ ነው በሰማይ የሚጠብቀን፡፡ አንድ ሰው ተደብደቆ ሰው ቢገድል ውስጡ ይሰቃያል፤ ነፍስ በጎ ነገር ታስባለች፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው፤ መንፈስ ጉልበት አለው ስለዚህ አክራሪነት በእግዚአብሔር መንግሥትም በዚህ ዓለምም ሰላምን የሚያሳጣ ቅስፈት የሚያመጣ ነው፡፡ ምክንያቱም በዚህ ዓለም መገዳደልን ያመጣል፤ በዚያኛው ዓለምም ዕረፍት የለም፡፡
እግዚአብሔር የሰላም አምላክ ነው እንጂ የጭቅጭቅ አምላክ አይደለም፡፡ አንድ ሰው የሌላውን ሃይማኖት ማክበር ግዴታው ነው፡፡ ምክንያቱም የራሱ ሃይማኖት እንዲከበርለት የሚፈልግ ሰው የሌላውን ሃይማኖት ማክበር ይኖርበታል፡፡ በሌላው ላይ እኔ ክፉ እያደረግሁ ሌላው ለእኔ መልካም ያስባል ብሎ መገመት ሞኝነት ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላካችንም ክፉውን በመልካም መልሱት አለ እንጂ በክፉ መልሱት አላለም፡ የእኔ ይበልጣል ያንተ ያንሳል ከማለት መብለጡን በመልካም ነገር ማሳየት አለበት፡፡ ሲያስተምር፣ ሢሠራ፣ ሲያስታርቅ፣ ሲያስማማ፣ ክፉ ነገርን ሲጸየፍ ነው፡፡ ሐዋርያትም ይህንን ነው ያደረጉት፤ በተለይም የሥጋ ፍላጎት አጉል ጥቅማ ጥቅም አምባገነን ሆኖ መሳደብ የሌላውን እምነት ማናናቅ የተከለከለ ነው፡፡ በየትኛውም ሃይማኖት መጽሐፍ ክፉ ሥራ የተወገዘ ነው፡፡ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ስንመለስ አዲስ አበባ የሁሉ መቀመጫ፤ የሁሉ መኖሪያ ናት፣ እምነት የሌለው ሰው አዲስ አበባ ውስጥ በኃላፊነት መሥራት ይከብደዋል፤ አዲስ አበባ የአንድነት መገለጫ ናት፡፡ በጋራ፣ በአንድነት፣ በስምምነት፣ የምንኖርባት እንድትሆን እፈልጋለሁ፡፡ በየቤተክርስቲያኑ መገለጥ፣ መሰበክ፣ መነገር ያለበት ይህ ነው፡፡ የሚፈጸሙ ተግባራትም ይህንን የሚገልጹ መሆን አለባቸው፡፡
መዋቅሩን በተመለከተ በጥናት ላይ ነው የሚገኘው የሚፈለገውም ሁሉም እንዲስማማበት፣ ሁሉም እንዲፈልገው እንዲሆን ነው፡፡ መዋቅሩ እየተጠና ያለው በአዲስ አበባ የተከሰተውን የመልካም አስተዳደር እጦት እንዲፈታ ታስቦ ነው፡፡ አሁን አባቶች እየገለጹ ያሉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት እና በውጭ ባሉ የእምነቱ ተከታዮች ሊቃውንት በጋራ እንዲታይ እና እንዲገመገም ትዕዛዝ እየተሰጠ ነው ያለው፡፡ ሁሉም ባለድርሻ አካላት እንዲወያይበት ይደረጋል እንጂ በችኮላ ከሥራ ላይ አይውልም፣ መዋቅሩ ዓለማቀፍ እውቀት ባላቸው ሰዎች ከታየና በቅዱስ ሲኖዶስ ከጸደ በኋላ ነው ከሥራ ላይ የሚውለው፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን ሕግ ያስፈልጋል፤ ሕግ መንገድ ነው፤ ሕግ በሌለበት መኖር አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፤ በእርግጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሕግ አላት፡፡
ከክርስቶስ ልደት በፊትም ሕግ ነበራት፤ ከክርስቶስ ልደት በኋላም ሕግ አላት፤ ከሐዋርያት በኋላም በፍትሐ ነገሥት ስትመራ ቆይታለች፡፡ ቤተክርስቲያናችን ሕግ ያስፈልጋታል ሲባል ሕግ የሌላት ሆኖ ሳይሆን ዘመናዊ የአሠራር ሕግ ስለሚያስፈልጋት ነው፡፡ ከአጥቢያ ጀምሮ እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ ድረስ ያለው የአሠራር መዋቅር አንድ እንደሚሆን፣ ሰዎች የማይተማሙበትና ሁሉም የሚያውቀው ግልጽ የሆነ ሕግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ መዋቅር ተጠንቶ በሥራ ላይ እስከሚውል ድረስ ከዚህ ቀደም ባለው ሕግ ይሠራል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም ራሱ ሕግ ነው፡፡ የወንጀል ሕግ፣ የፍትሐብሔር ሕግም የወጣው ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ሰውን መግደል፣ ስርቆት ኃጢአት ሲሆን በወንጀል ሕግም ወንጀል ተበሎ ተጽፏል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሁላችንም የምንኖርባት ልጆቻችንን የምናሳድግባት የዓለም ሁሉ መኖሪያ የሆነች ከተማ ናት፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ቅዱስ ሕዝብ እንደሆነ ይታወቃል፤ በእርግጥ አልፎ አልፎ ክፉ ሰዎችም አሉ፤ በአቋራጭ ለመበልጸቅ የሚፈልጉ ቢታቀቡ? ሕግ ቢከበር? በጎ ሰዎች በጎ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ክፉ ሰዎች ከክፋታቸው እንዲመለሱ ይገባል የምህረት አምላክ እግዚአብሔር ይጠብቀን በማለት ክቡር ሥራ አስኪያጅ ሊቀ አእላል ቀሲስ በላይ መኮንን ሰፋ ያለ ጋዜጣዊ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመጨረሻም የዝግጅት ክፍላቸን ሥራአስኪያጁ ባስተላለፉት የሠላም፣ የሕብረት፣ የመቻቻል እና የፍቅር መልእክት መሠረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይገባል እንላለን፡፡
{flike}{plusone}