የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ከንቲባ ክቡር አቶ ድሪባ ኩማ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ

2551

የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ከንቲባ ድሪባ ኩማ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት እና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን ዕረቡዕ ታህሳስ 16 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም ከሰአት በፊት በተለያዩ የቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያወያዩአቸው ሲሆን በተደረገው ውይይትም ከፍተኛ መግባባት ላይ የተደረሰ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡ በከንቲባ ጽ/ቤት የጋራ ውይይት ያደረጉት ብፁዕ አቡነ አስጢፋኖስ በሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን አማካኝነትከክቡር ከንቲባ ድሪባ ኩማ ጋር የትውውቅ መርሐ ግብር አድርገዋል፡፡ በመቀጠልም በሊቀ ትጉኃን ታጋይ ታደለ የአራዳና ጉለሌ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ አማካኝነት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ጽ/ቤት ለክቡር ከንቲባ የተጻፈውን ደብዳቤ በንባብ ያቀረቡ ሲሆን የደብዳቤው ዋና ዋና ይዘትንም እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
ለክቡር አቶ ደሪባ ኩማ የአዲስ አበባ አስተዳደር ከከንቲባ ቀደም ሲል ክቡር አቶ ኩማ ደመቅሳ የአዲስ አበባ ከንቲባ ይመራ በነበረው አስተዳደርና በቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት የጋራ ውይይት እና ስምምነት መሠረት ከአስተዳደሩና ከቤተ ክርስቲያናችን ተውጣጥቶ የአዲስ አበባ አድባራት እና ገዳማት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ አቢይ ኮሚቴ የጀመረውን የካርታ አሰጣጥ ሂደት እንዲቀጥል የቀረበ ማሳሰቢያ ነው፡፡
እንደሚታወቀው ሁሉ የአዲስ አበባ አድባራት እና ገዳማት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ማግኘት ይችሉ ዘንድ በአቶ ኩማ ደመቅሳ የአዲስ አበባ አስተዳደር ይመራ በነበረው የቤተ ክርስቲያናችን መሪዎች በነሐሴ ወር 2ዐዐ5 በተደረገው የጋራ ውይይት ከሁለቱም መ/ቤቶች የተውጣጣ አስር አባላት ያሉት የአድባራት እና ገዳማት ካርታ አጥኚ ዐቢይ ኮሚቴ መቁቋሙ የምናስታውሰው ከምስጋና ጋር ነው፡፡
የጋራ አጥኚ ኮሚቴው የካርታ አስጠኝ ሂደትን በተቀላጠፈ ሁኔታ ማከናወን ይችል ዘንድ
1ኛ የአዲስ አበባ አድባራት እና ገዳማት ማስረጃን ማሰባሰብና የቦታውን ልኬት በቴክኒክ ኮሚቴ አባላት እንዲአከናውን ማድረግ፣
2ኛ. ለካርታው አሰጣጥ ሂደት ማስፈጸሚያ ከሁለት መ/ቤቶች ብር 816670 /ስምንት መቶ አስራ ስድስት ሺህ ስድስት መቶ ሰባ ማስፈለጉ ታምኖበት ከሁለቱ መ/ቤቶች እንዲፈቀድ ጥያቄ ማቅረቡና ማስፈቀዱ፣
3ኛ. የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚፈለግበትን አራት መቶ ሶስት ሺህ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራት እና ገዳማት ፕሮጀክት ማረጋገጫ ስም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አራዳ ቅርንጫፍ በተከፈተው ሂሳብ ቁጥር ገቢ ማድረጉ፣
4ኛ. ገንዘቡ በሁለት የኮሚቴ አባላት ጣምራ ፊርማ እየወጣ ለተቀደሰለት አላማ እንዲውል ማድረጉ ኮሚቴው ከተቋቋመበት ቀን እና ዓመተ ምህረት ጀምሮ የአዲስ አበባ አድባራት እና ገዳማት የእምነት፣ የጸበል፣ እና የመካነ መቃብር ቦታ አንድ መቶ ስድሳ ሁለት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታዎች ከአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት መረከባቸውን ባቀረቡት መግለጫ ለማወቅ ችለናል፡፡
ስለዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በክቡርነትዎ ለሚመራው አስተዳደር ምስጋና ታቀርባለች፡፡ ጉዳዩ በእንደህ እያለ ከመስከረም 9 ቀን 1998 ዓ.መ በፊት የተተከሉና ካርታ ያላገኙና ሕጋዊ ካርታ ተሰጥቶአቸው የቀድሞ ይዞታ የተቀነሰባቸው ገዳማት እና አድባራት መኖራቸው፣ ከመስከረም 9 ቀን አንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ዘጠኝ ዓ.መ በኋላ የተተከሉ ገዳማት እና አድባራት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ አለ መረከባቸው፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቱያን ምዕመናን እና ምዕመናት በአዲስ አበባ ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዙ መሄዳቸውን ተከትሎ የሚገለገሉበት የቤተ ክርስቲያን ማሠሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው ሀገረ ስብከቱን በመጠየቅ ላይ መሆናቸው፣ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ከተሰጣቸው በኋላ የአጥቢያ አብያተ ክርስቱያናት አስዳደሩን በማመስገን የልማት ሥራ ለመስራት በከፈተኛ ዝግጀት ላይ በሚገኙበት በአሁኑ ወቅት ካለአጥኚ ኮሚቴ ዕውቅና እና ውሳኔ ውጭ በአስተዳደሩ ብቻ እየመከኑ የሚገኙት የአንዳአንድ አድባራት እና ገዳማት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታዎች መኖራቸውን ተከትሎ ሕዝበ ክርስቲያኑ በአስተዳደሩ ላይ ቅሬታ እያሳደረ መሆኑ፣ የቅዳሴ፣ የማህሌትና የጸሎት ሥነ ሥርአት የተፈጸመባቸውና ለወደፊቱም የሚፈጸመባቸው የጥምቀትና የመስቀል በዓላት ማክበሪያ ቦታዎች ለአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ይሰጣል እንጂ ለአዲስ አበባ አድባራት እና ገዳማት አይሰጥም መባሉ፣ አብያተ ክርስቲያናት በተተከሉባቸው አንድ አንድ ቦታዎች ላይ የአካባቢ ጥበቃ ባለስለጣን ካርታ ማውጣቱን እና ለአብያተ ክርስቱያናቱም ካርታ ተዘጋጅቶላቸው ከተሰጣቸው በኋላ የተሰጣቸው ቦታ የግሪን ኤርያ ነው በሚል አንዳችም የልማት ሥራ አይሠራም ተብሎ መከልከሉ የሚል ሲሆን ከላይ የተዘረዘሩት ችግሮች መፍትሔ እንዲሰጥባቸው የቅዱስ ፓትርያርኩ ደብዳቤ ያብራራል፡፡

2554

በማያያዝም ካርታ ያልተሰጣቸው እና ካርታ የመከነባቸው አብያተ ክርስቲያናትን ዝርዝር የሚገልፅ አምስት ገፅ በቅዱስ ፓትርያርኩ ደብዳቤ ሸኚነት የተዘጋጀውን ዝርዝር መረጃ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት እና የጂማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለክቡር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ አስረክበዋል፡፡ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅን ጨምሮ ከሀገረ ስብከቱ ልዑካን በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ የማብራሪያ ሐሳቦች ቀርበዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ለክቡር ከንቲባው የሚከተለውን ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ ካርታዎች መከኑ የሚለው አነጋገር እጅግ ውስብስብ ሆኖ ነው የምናየው ካርታ መከነ ሲባል ሰምተን አናውቅም እንዲህ አይነቱ አነጋገር ምዕመናንን የሚያነሳሳ እና ችግርን የሚፈጥር አነጋገር ነው ምዕመናን በሚውሉበት አካባቢ ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት ለሚአቀርቡት ጥያቄ አወንታዊ ምላሽ ካላገኙ በራሳቸው ተነሳሽነት ቤተ ክርስቲያን ይሠራሉ፡፡ በህገ ወጥ መንገድ ነው የሠራችሁት የሚል ምንም አይነት ቅድመ ምክክር ሳይደረግ የተሠራው ቤተ ክርስቲያን እንዲፈርስ ይደረጋል፡፡ ያፈርሳል ይህ አሠራር ረብሻን ይፈጥራል፣ ነገርን ያነሳሳል፣ የሕዝብን እና የመንግሥትን ሰላማዊ ግንኙነት ያውካል ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶ ከተቀደሰበት እና ከተወሰደበት በኋላ እንዲፈርስ ከተደረገ በምዕመናን ዘንድ ትልቅ ቁጣን ይቀሰቅሳል ይህ እንደቀላል ሊታይ አይገባም፡፡ ከተማ ሲስፋፋ በከተማ ማስተር ፕላን የእምነት ተቋማት ቦታ አለመያዙ በምዕመናን ርብርብ ያለፈቃድ ቤተ ክርስቲያን ሊሠራ ይችላል፡፡ በጥናት የተደገፈ ስራ መስራት ያስፈልጋል፡፡
መንግሥታችን ለዜጎች የሚአስብ መንግሥት መሆኑን እናውቃለን ከላይ ከማዕከል የሚዘረጋው ፓሊሲ /መመሪያ/ እስከ ታች ድረስ ሊተገበር ይገባል፡፡ ቤተ ክርስቱያን ብዙ ሥራዎች ስለምትሠራ ሰፊ ቦታ ያስፈልጋታል፡፡ አሁን የምንገልፀው ችግር አሁን የተፈጠረ ችግር ሳይሆን የቆየ ችግር ነው፡፡ ክቡር አቶ ኩማ ደመቅሳ ብዙ ችግሮችን ሲፈቱ ቆይተዋል ይህ የውይይት መድረክ ለደፊቱም መለመድ አለበት ምክንያቱም ይዘን የምንመጣው የሕዝብን ችግር ነው፡፡ በማለት ብፁዕነታቸው ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በመጨረሻም ክቡር አቶ ድሪባ ኩማ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥተዋል የከተማ አስተዳደሩ የሁሉንም ቤተ እምነት ችግር በእኩል የመፍታት ሀላፊነት አለበት አሁን የቀረበውን ችግር የመፍታት ግዴታ አለብን መንግሥት መሬትን በአግባቡ የማስተዳደር ኃላፊነት አለበት፡፡ የሃይማኖት ተቋማት ልማትን እንዲሠሩ በሚገባ ማስተናገድ ይገባል የሚአስፈልጋቸውን የመሬት መጠን ለመፍቀድ ቁጭ ብሎ መወያየት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ተነስተን ስናይ ከዘጠና በፊት የተባለው የመጀመሪያ ሥራ ስለሆነ ቀሪዎቹን ማጠናቀቅ ያስፈልጋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ከዚህ ቀደመ ለቤተ ክርስቲያን ብዙ ካርታ ሰጥቷል፡፡ የቀሩት ስንት ናቸው የት አካባቢ ነው ያሉት በምን ያህል ቦታ ላይ ነው ካርታ የሚሰጠው የሚለውን ከላይ እስከ ታች ካለው መዋቅራችን ጋር ተነጋግረን ኮሚቴ አይቶ የውሳኔ ሐሳብ እያቀረበ እየወሰን የሚሄድበትን ሁኔታ መፍጠር ይቻላል፡፡
የቀረበውን ጥያቄ ዝም ብለን አናየውም፡፡
ከመሬት ላይ ብዙ ጥያቄዎች ስላሉብን ጥያቄዎችን ማመጣጠን ይገባል፡፡ በተቻለ መጠን ጥያቄዎችን አድሬስ ለማድረግ እንሞክራለን መከነባቸው የተባሉትን እያንደንዱን በዝርዝር አናየዋለን በምን መክንያት ነው የመከነው ምንድን ነው ያመከነው የሚለው ጉዳዩ ከሚመለከተው ጋር በዝርዝር እንነጋገራለን፡፡ ከዚያም በኋላ እንደገና ቁጭ ብለን እንነጋገራለን፡፡ ካርታ ዝመ ብሎ ሊመከን አይገባም፡፡ ለመወሰን የሚያስችል እርምጃ እንወስዳለን ምክንያቱም ከእምነት ተቋማት ጀርባ ምዕመናን አሉ፡፡ ሃይማኖት የሌለው ሕዝብ የለም በተቻለ መጠን የምዕመናንን ፈላጐት ለማሟላት ጥረት አናደርጋለን፡፡ ለጥያቄአችሁም ምላሽ ለመስጠት እንሞክራለን፡፡
ደንን በተመለከተ በአዲስ አበባ ደንን እናበዛለን እንጂ ደንን መቁረጥ የለብንም የእንጨት ሽያጭ አያስፈልገንም፡፡
በደን ዙሪያ ትንሽ ስራ ነው የሠራነው ገና ማስፋፋት ይኖርብናል፡፡ አዲስ አበባ ለግሪን ኤርያ የተመቸ ነው፡፡ ከታሪክ ተነስተን ስንመለከት ቤተ ክርስቲያን ደንን ታስፋፋለች ደን በኢትዮጵያ እንደቅሬት ካደረጉት ተቋማት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዋናነት ትጠቀሳለች፡፡ ደን በሌለበት አካባቢ እንኳን ብንሄድ ቤተ ክርስቲያን በደን ተከባ ነው የምናያት ቤተ ክርስቲያን በራሷ የተከለችውን ደን መቁረጥ አይገባም፡፡ በዚህ ዙሪያ ያለውን ችግር አድሬስ ለማድረግ እንሞክራለን፡፡ ምዕመናን ዕምነታቸውን የሚገለፁበት እና ለልማት የሚአውሉትን መሬት የሚአገኙበት ሁኔታ ይመቻል ለአስተዳደር ጫናን የሚፈጥር አሠራር ግን ሊስተካከል ይገባዋል ከሁላችንም ላይ ድክመት አለ፡፡ ስለዚህ ድክመቶቻችንን ልናስተካክል ይገባናለ አሁን ባለንበት በሃያ አንደኛው ዘመን ቦታን ያለአግባብ መያዝ አይቻልም ተገቢው ጥያቄ አስቀድሞ ሊቀርብ ይገባል አፋጣኝ ምላሽም ሊሰጥ ይገባል ከማስተር ፕላን ውጭ በወረራ መልክ ቦታን መያዝ አይገባም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሳይፈቀድ ቦታ አትያዙ በማለት በማስተማር ችግሮችን መፍታት አለባት፡፡ መንግሥትም ለጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣል፡፡ ቀጣዩ ማስተር ፕላናችን የዕምነት ተቋማትን ቦታ ያካተተ ነው፡፡ ስለዚህ ለሆነ ልማት ያስቀመጥነውን ቦታ በሀይል በመጠቀም መያዝ አይገባም፡፡ ሕዝቡ አስተዳደሩን ጠይቆ ምላሽ ሳይሰጥ መስራት አይገባም፡፡ ከሕዝብ ጋር ውይይት ሳይደረግ የተሠራውን ማፍረስም ተገቢ አይሆንም፡፡ በኮንዶምኒየም አካባቢ የእምነት ቦታዎች እንዲኖሩ ለማድረግ ሁኔታዎችን እናያለን በማለት ክቡር ከንቲባው ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

{flike}{plusone}