የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና ከካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጋር በመተባበር በሰላም ዙሪያ ለአንድ ቀን የቆየ የምክክር ጉባኤ አካሄደ
የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ከፍትሕና ሰላም ቢሮ ጋር በመተባበር ቁጥራቸው 150 ለሚደርሱ ከሰባት ቤተ እምነት ለተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች ማክሰኞ ታህሳስ 3 ቀን 2008 ዓ.ም በግዮን ሆቴል ዘላቂና ማኅበራዊ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያስችል የአንድ ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ ወርክሾፕ አድርጓል፡፡
በጉባኤው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት ዶ/ር አባ ኃ/ማርያም መለሰ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሰላም የሁሉ ነገር መሠረት ነው፡፡ ያለ ሰላም ልማት ማልማት አይቻልም፡፡ የሃይማኖት ተቋማት ተግተው ሊሠሩ ይገባል፡፡ ሀገራችን በዕድገት ላይ የምትገኘ በመሆኑ ልማቱ እንዳይደናቀፍ የሃይማኖት ተቋማት ትልቁን ሚና መጫዎት ይኖርባቸዋል፤ በመመካከርና በመወያየት የተጀመሩ ልማቶች እድገት ላይ እንዲደርሱ ማድረግና በጋራ ጉዳዮች ላይ መወያየት፣ መመካከር፣ መቻቻል፣ መረዳዳትና ለተተኪው ትውልድ ሰላም ያላት ኢትዮጵያን ማስተላለፍ ይገባል በማለት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ “የሰላም አስተዋፅኦ በሃይማኖት እይታ” በሚል ርዕስም ለተሳታፊዎቹ ጥናታዊ መግለጫ አቅርበዋል፡፡
ሊቀ ትጉኃን ታጋይ ታደለ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የዕቅድና ልማት ዋና ክፍል ኃላፊ፣ የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ ሰብሳቢ ባስተላለፉት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ሀገራችን ኢትዮጵያ የሕዝቦችና የዜጐች የመቻቻልና የመከባበር፣ የፍቅርና የአብሮነት ተምሳሌት ሆና ለዘመናት የዘለቀች ሀገር ናት፡፡
ይህ የመቻቻልና የመከባበር ባህል በተለያዩ የሃይማኖቶች ግንኙነት ጎልቶ የታየ ከመሆኑ አንጻር በዚህ ረገድ ሀገራችን በብዙ ሀገሮች ዘንድ በምሳሌነት እንድትጠራ አድርጓል፡፡
የመተሳሰብና የአብሮነት እሴታችን የዘመናት ሂደት ውጤት መሆኑ ገሀድ ቢሆንም በተለይ ከ1400 ዓመት በፊት በሀገራችን ታሪክ የተመዘገበው አስደናቂ ተግባር ግን ለእስከ አሁኑ የመቻቻል ባህላችን ጠንካራ መሠረት እንደሆነ ይታመናል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ የፍቅር፣ የመቻቻልና የመከባበር ተምሳሌት በመሆኗ የከፋቸውና ስደት የገጠማቸው፣ ነፃነት የጠማቸው ሕዝቦች የሚጠለሉባት ሀገር ሆነች፡፡
ይህ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የመቻቻልና የመከባበር ባህል ነው፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ ዘመናት የሥልጣን ርካቡን የሚቆናጠጡት ገዢዎች አንድን ሃይማኖት ከሌላው ሃይማኖት ለማበላለጥ በሚከተሉት ፖሊሲና በሚፈጥሩት ሳንካ አልፎ አልፎ በሃይማኖት ሽፋን ግጭት መፈጠሩ አልቀረም እንደዚያም ሆኖ ግን ሕዝቦች የገዢዎቻቸውን ተፅዕኖ በብልሀት ወደ ጐን ጥለው በእነሱ ሥልጣንና ጥቅም መሣሪያ ከመሆን ተቆጥበው መቻቸልን፣ አብሮነትንና መከባበርን ምርጫቸው አድርገው ኖረዋል፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከአዲስ አበባ ከቶሊካዊት ቤተ እምነት የፍትሕ ቢሮ ጋር በተመተባበር ይህንን የመሰለ መድረክ ለማዘጋጀት የቻለው፡፡
የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ የሀገራችን ርዕሰ መዲና፣ የአፍሪካ ዋና ከተማና የዓለም ሕዝቦች መኖሪያ በሆነችው በአዲስ አበባ ከተማ ለዜጐች ሁለንተናዊ ሰላም፣ ለሀገሪቱ ዕድገትና ልማት እንዲሁም በመልካም ሥነ ምግባር የታነፀ ዜጋ ከማፍራት አንጻር የበኩሉን ድርሻ ሲያበረክት ቆይቷል፡፡
በማበርከትም ላይ ይገኛል፡፡
ይህ ዛሬ እያደረግነው ያለው ጉባኤ በሰላም አብሮ በመኖር፣ በመከባበር፣ በአክራሪነትና ጽንፈኝነት ዙሪያ የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከአዲስ አበባ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የሰላምና የፍትሕ ቢሮ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ሲሆን በዚህ ጉባኤ ላይ የታደሙት ከአዲስ አበባ 10 ክፍላተ ከተሞች የሚገኙ የሰባት የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባላትና ከአዲስ አባ ፍትሕ ጽ/ቤት የፀጥታና የሃይማኖቶች ዴስክ በተውጣጡ በድምሩ 150 ለሚሆኑ የሃማኖት አባቶችና ባለድርሻ አካላት ሲሆን በዚህም መድረክ አብሮ በመኖር፣ በመከባበር፣ በአክራሪነትና ጽንፈኝነት ዙሪያ ገለፃ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡ ገለፃውንም ተከትሎ ጥያቄዎችና ውይይቶች እንደሚደረጉ እየገለጽን ቀጣዩ ውሎአችን በንቃት በመሳተፍ ላይ ያተኮረ እንዲሆን እየተመኘሁ በገንዘብ ለደገፉን ለአዲስ አበባ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የሰላምና የፍትሕ ጽ/ቤት በጉባኤው ፊት እንዳመሰግን ይፈቀድልኝ ዘንድ እየጠየቅሁ በዚህ ጉባኤ ላይ የተገኛችሁ የአስር ክፍላተ ከተማ የሃይማኖት ተቋማት አባቶች ለከተማችን ሰላም ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ ለመመራት እንድንተጋ እያሳሰብኩ በድጋሚ በተቋማችን ስም እንኳን ደህና መጣችሁ እላለሁ፡፡ “ለሰላም እንሠራለን በሰላም እንኖራለን” በማለት ጥልቅ የሆነ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
አቶ ወንድምአገኝ ወ/ጊዮርጊስ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ተወካይ ባስተላለፉት መልእክት በአሁኑ ወቅት መንግሥታችን የጀመረውን ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አጠናቆ የሁለተኛውን ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በሀገር አቀፍ ደረጃ አፅድቆ ወደ ሥራ በመግባቱ ሀገራችን ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ የልማትና ዕድገት ግስጋሴዋን እያፋጠነ ይገኛል፡፡
በመልካም አስተዳደር በኩል የሚታዩ ችግሮችን በማስተካከልና በማረም ወደ ትክክለኛ መስመር ለመግባት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ በዚህም ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሻለ ለውጥ እያመጣ እንደሆነ ለሁሉም ግልፅ ነው፡፡ ልማትና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ የሀገራችንን ሰላሟንና ደህንነቷን ማስጠበቅ፣ ኅብረተሰቡን ለማስተባበርና መቻቻልንና መከባበርን ለመፍጥር፣ ፀረ ሰላም ኃይሎችን ለመታገል፣ አክራሪነትን፣ ጽንፈኝነትና ሽብርተኝነትን ለመከላከል የሃይማኖት ተቋማት የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑን መንግሥታችን ያምናል፡፡
ስለሆነም መንግሥት ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በመሆን በጋራ የሚሠራቸው ዘርፈ ብዙ ሥራዎች አሁን በሀገራችን ለሰፈነው ልማትና መልካም አስተዳደር እንዲሁም ሰላም መገለጫዎች ናቸው፡፡
በመሆኑም መንግሥታችን ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በሕገመንግሥቱ በተገለፀው አግባብ ያለው ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ፀረ ሰላም ኃይሎችን በመታገል፣ አክራሪነትን፣ ሽብርተኝነትና ፅንፈኝነትን በመከላከል የሀገራችንን ሰላም በማረጋጋት ዕድገቷን ማፋጠን ይሆናል፡፡
ስለሆነም የሃይማኖት ተቋማት እነዚህን ጉደዮች ከግንዛቤ በማስገባት ከመንግሥት ጐን በመሆን የልማትና መልካም አስተዳደር ሥራዎችን በጋራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በየጊዜው በሚአካሂደው ፕሮግራም ላይ የከተማ አስተዳደሩ ከሃይማኖት ተቋማት ጐን በመሆን የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርግ ላረጋግጥ እወዳለሁ የዛሬውን ፕሮግራም የተሳካና ውጤታማ እንዲሆን በመገዘብ ፕሮግራሙ የተጀመረ መሆኑን አበሥራለሁ ብለዋል፡፡
አቶ ጉዑላይ ወልደጊዮርጊስ በተባሉ ባለሙያ ሰላምና ዕርቅ በተሰኘ ርዕስ ለተሳታፊዎች ሰፋ ያለ የግንዛቤ መስጫ ትምህርት ተሰጥቷል፡፡ በቀረበው ትምህርት የሰላምን ፅንሰ ሐሳብ፣ በመዝገበ ቃላት አተረጓጐም አብራርተዋል፡፡ ሰላም ለናንተ ይሁን፣ ሰላም ለንተ፣ ሰላም ላንቺ፣ ሰላም ለዚህ ቤት እየተባለ ዘወትር የሚነገረውም ምስጢራዊ አገላለፅ አብራርተዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በሕብረተሰቡ የሚታየው መከባበር ምን ያህል መሆኑን፣ በግጭት የምናሳልፈው ጊዜ ብዙ ልማት የሚሠራበት ጊዜ ሊሆን እንደሚገባው፣ በግጭት ትርፍ ያላቸው ኃይሎች መኖራቸውን፣ ፍትሕ ከሌለ ሰላም የማይኖር መሆኑን፣ ሁሉም ሰው ክብር ያለው መሆኑን፣ ጦርነት የሚጀምረው ከጭንቅላታችን መሆኑን፣ ሰላምም የሚጀመረው ከጭንቅላታችን መሆኑን፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር ከምናደርገው ግጭት ይልቅ ከራሳችን ባሕርይ ጋር የምናደርገው ግጭት የከፋ መሆኑን የጥናት አቅራቢው በጥሩ አገላለፅ አቅርበውታል፡፡ የጉባኤው ተሳትፊዎችም በቀረቡት ትምህርቶች በቂ ግንዛቤ ያገኙ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ይህ ውይይት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባልም ብለዋል፡፡ መንግሥትም ለዚህ ጉዳይ አስፈላጊውን በጀት ሊመድብ ይገባል በማለት ሃሳባቸውን የገለጹት የጉባኤው ተሳታፊዎች በተቋሙ ውስጥ የተሰጣቸውን ሥራ በማያከናውኑ የሃይማኖት ጉባኤ አባላት ምትክ ሌሎች የሚሠሩ ሊተኩ ይገባል ብለዋል፡፡ አንድ በመሆናችን ፀረ ሰላሞች እየጠፉ ናቸው፤ የሃይማኖት ተቋማቱ ለሀገራችንም ለመንግሥትም ትልቅ ኃይል ነው፡፡ ሰላም የሁላችንም ሀብት ነው፡፡ ከውይይቱ በመቀጠልም በኮማንደር መኮንን አሻግሬ የሃይማኖት ተቋማት መሥራች አባል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ የፀጥታ አስተዳደር ጉዳዮች ዋና የሥራ ሂደት ኃላፊ “ሕገ መንግሥቱና ነበሩ ባህላችን አክራሪነትንና ጽንፈኝነትን እንዴት ይከለክላል” በሚል ርዕስ የሕገመንግሥቱን ድንጋጌዎች በመተንተን ሰፋ ያለ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡ ተሳታፊዎቹም በመጨረሻ ላይ በተሰጠው ትምህርት እጅግ በጣም የረኩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ከአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት የልምድ ልውውጥ ለማድረግ በጉባኤው ላይ የተገኙት የኦሮምያ ክልል የሃይማኖት ጉባኤ የሥራ አመራርም በሊቀትጉኃን ታጋይ ታደለ የተመራውን የምክክር ጉባኤ በእጅጉ አድንቀዋል፡፡ ሊትጉኃን ታጋይ ታደለ ከኦሮምያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለተፈቀደልን አንደ ሚሊዮን ብር በጀት ከፍተኛውን የማስተባበር ሥራ የሠሩ መሆናቸውን ለጉባኤው በመግለጽ ጉባኤው ሊቀትጉኃን ታጋይ ታደለን እንዲአመስግናላቸው ጠይቀዋል፡፡ የልምድ ልውውጡም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል ብለዋል፡፡
{flike}{plusone}