የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የክፍል ኃላፊዎች የስድስት ወር ሪፖርት አዳመጠ
የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ዋና ሥራአስኪያጅ ቆሞስ አባ ሞገስ ኃ/ማርያም ፣ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ጥበብ ምናሴ ወ/ሐና፣ የየክፍሉ ኃላፊዎች፣ የሀ/ስብከቱና የሰባቱ ክፍለ ከተሞች ሠራተኞች በተገኙበት በሀ/ስብከቱ የስብሰባ አዳራሽ የሁሉም ክፍል ኃላፊዎች የስድስት ወር ሪፖርት ቀርቧል። በሪፖርቱ ብዙ አመርቂ የሚባሉ ሥራዎች እንዳሉ ሆነው በአንጻሩ ደግሞ ብዙ ሊሠሩ የሚገባቸው ሳይሠሩ እንደቀሩና ለወደፊቱ ትኩረት ተሰጥቶባቸው በአግባቡና በጊዜው ተጠናቀው እንደሚቀርቡ ተገልጿል። ለገቢ ተብሎ ቤተክርስቲያንን የሚያስነቅፉ ነገሮችም መቅረት እዳለባቸው ተደምጧል። በገቢ ደረጀም ሀ/ስብከቱ በስድስት ወር ዕድገት ቢያሳይም ካለፉ ዓመታት ሲነጻጸር በስድስት ወር ጉድለት እንዳሳየ ተነግሯል። የክፍለ ከተሞች ሒሳብ አያያዝም መቀየርና መስተካከል እንዳለበትም በክፍል ኃላፊው አጽንኦት ተሰጥቶበታል።
የሁሉም ሪፖርት ከተደመጠ በኋላ ስለ ቤተክርስቲያኒቱ ወቅታዊ ሁኔታ ውይይት ተደርጓል። በተለይ በአሁኑ ሰአት አንገብጋቢ ጉዳይ የሆነው የአንዳንድ አብያተክርስቲያናት በተለያዩ ሰዎች መታሸግ የሀ/ስብከቱና የክፍላተ ከተሞች ራስ ምታት ሆኗል።በዚህ ጉዳይም ጠለቅ ያለ ውይይት የተደረገ ሲሆን ጉዳዩን አስመልክቶ ከክፍላተ ከተማ ሥራአስኪያጆች እንደተደመጠው የችግሩ ፈጣሪዎች የቤተክርስቲያን ተልእኮ ያልገባቸው የአንዳንድ ካህናትና ሰባክያነ ወንጌል እጅ እንዳለበት ተናግረው፣ ተጨበጭ መረጃ ያላቸው መሆኑንም ገልጸዋል ። እነዚህ አካላት ሕዝቡን በማሳደም አብያተክርስቲያናት እንዲታሸጉ እያደረጉ መገኘታቸው አሳፋሪና አስነዋሪ፣ እንዲሁም ከአንድ የቤተክርስቲያን አገልጋይ የማይጠበቅ ኩፉ ሥራ መሆኑን በመግለጽ ድርጊቱን ኮንነዋል።
በመቀጠልም ሀ/ስብከቱና ክፍለከተሞች ተባብረው በአንድነት እጅና ጓንት ሆነው ካልሠሩ ችግሩ እንደሰደድ እሳት እየሰፋ መሄዱ የማያጠራጥር ጉዳይ መሆኑ ከተሰብሳቢዎች አንደበት ተሰምተዋል። ችግሩን ለመቅረፍና ዳግም እንዳይከሰት ተናብቦ መሥራት፣ የቅድመ መከላከል ሥራ ቢሠራና ውይይቶች በተደጋጋሚ ቢደረጉ የሚሉት ሐሳቦች እንደ መፍትሔ ቀርበዋል።
በሌላ መልኩ በአሁኑ ሰዓት የሀ/ስብከቱ ግቢ በባለ ጉዳዮች ተጨናንቆ መገኘቱ ሀ/ስብከቱን ዕረፍት የነሣ ሲሆን ችግሩ የሚቀረፈው ሀ/ስብከቱ ለክፍለከተሞች ሙሉ ሥልጣን ሰጥቶ ባለ ጉዳዮች ባሉበት የክፍለ ከተማ ጽ/ቤት እንዲዳኙ ሲደረግ ብቻ መሆኑን በሀ/ስብከቱ ዋና ሥራአስኪያጁ በአጽንኦት ተገልጿል።
ችግሩ ከክፍለከተማ በላይ ካልሆነ ማንኛውም ባለ ጉዳይ ክፍለ ከተማውን ጥሶ ወደ ሀ/ስብከቱ መምጣት እንደሌለበት በመግለጽ ክፍለከተሞች ከቅጥር፣ ሽግሽግና ዕድገት ውጪ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ሙሉ የመሥራት መብት እንዳላቸውና በደብዳቤም ተገልጾ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።
በመጨረሻም ዋና ሥራ አስኪያጁ ምክር አዘል የሆነ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ ለቤተክርስቲያን ነቀርሳ የሆኑትን እንደነ ሙስና፣ ዘረኝነት፣ አድመኝነት፣ መለያየት፣ ክፋትና የመሳሰሉትን እጅ ለእጅ ተያይዘን ልናስወግዳቸው ይገባል፤ በነዚህ ርካሽ በሆኑ ድርጊቶች ክብራችንን፣ ንጽኅናችንን፣ ቅድስናችንን ልናጉድፍ አይገባም ሲሉ አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል።
እንዲህ ያሉ የውይይት መድረኮች በየግዜው ቢደረጉና ጠቃሜ የመፍትሔ ሐሳቦችን እየተለዩ በአፈጣኝ ወደ ትግበራ ቢገባ ችግሮች ተቀርፈው ሰላም እንደሚገኝ ምንም ጥርጥር የሌለው መሆኑን ልንገልጽ እንወዳለን።