የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት ለህዳሴ ግድብ የ6 ሚሊዮን ብር ቦንድ ግዢ እንደሚፈጽም ገለጸ
በአራዳ ክፍለ ከተማ ለ10 ቀናት የቆየው የህዳሴ ግድብ ዋንጫ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ተባርኮ ወደ ሌላ ክፍለ ከተማ ተዛውሯል
ለታላቁ ግድብ ግንባታ ገቢ ለማሰባሰብ እንደ ማነቃቂያ የሚጠቅመው የህዳሴው ግድብ ዋንጫ በአራዳ ክፍለ ከተማ ለ10 ቀናት ከቆየ በኋላ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ተባርኮ ወደ ሌላ ክፍለ ከተማ በክብር ተዛወሯል።
በፕሮግራሙ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፥ ብፁዕ አቡነ ያሬድ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የአርሲ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ አቡነ አረጋዊ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት፥ የውጭ ግንኙነት የበላይ ኃላፊ እና የድሬዳዋ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ክቡር መ/ሕይወት ቆሞስ አባ ኃ/ገብርኤል ነጋሽ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ የራዳ ክፍለ ከተማና በአዲስ አበባ የህዳሴው ግድብ ገቢ አስተባባሪ ኃላፊዎችና ልዩ ልዩ ታዳሚዎች ተገኝተዋል።
ከመንግሥት መስሪያ ቤት የመጡ ኃላፊዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስተያን ለሀገር ዕድገትና ለህዳሴው ሁለንተናዊ ድጋፍ ስታደርግ የነበረችና ያለች ስትሆን አሁንም የአንድነታችን የሆነው የህዳሴ ግድብ ዋንጫ እንዲባረክልን ወደዚህ ይዘነው መጥተናል ብለዋል።
ክቡር መ/ሕይወት ቆሞስ አባ ኃ/ገብርኤል ነጋሽ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፦ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በተለያዩ ጊዜያት ህዝቡን በማስተባበር ሲያስተምር፣ ሲያስተባብርና ሲያግዝ ቆይቷል፤ አሁንም የህዳሴ ግድብ ጥቅሙ ለሀገር ላቅ ያለ ስለ ሆነ ሀ/ስብከቱ ተጨማሪ የቦንድ ግዢ እንዲደረግ መወሰኑን አብራርተዋል።
የቦንድ ግዢው በሁለት ዘርፍ የሚከናወን ሆኖ በቢሮ ደረጃ የ6 ሚልዮን ቦንድ ግዢ የሚፈጸም ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ከላይ እስከ አጥቢያ የቦንድ ግዢ እንዲደገግ መወሰኑን ገልጸዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖትም ዋንጫው ወደእኛ በመምጣቱ ደስ ብሎኛል፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሀገራችን ሃብት ሆኖ ሳለ ሳንጠቀምበት ቆይተን አሁን በቆራጦች እንዲገደብ ከተወሰነ ጊዜ ጀምሮ በግብጽ ብዙ ብስጭት የፈጠረ ቢሆንም የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ይብቃቹ እጃችሁ አንሱልን ሊላቸው ይገባል፣ እግዚአብሔር የሰጠን ሃብታችን ነውና እንጠቀምበት ብለዋል። በመጨረሻም ኢትዮጵያውያን ሁላችን ግድቡ ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅ የበኩላችን እንወጣ በማለት መልእክታቸውን ለመላ ኢትዮጵያውያን በማስተላለፍ የህዳሴው ዋንጫ ባርከው ፕሮግራሙ በጸሎትና ራኬ ዘግተዋል።
መ/ር ኪደ ዚናዊ የሀ/ስብከቱ ዘጋቢ