የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የሥራ ሐላፊዎች ተመደቡለት
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክያን መንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤ/ክህነት መዋቅራዊ አስተዳደር ሥር ከሚገኙት አህጉረ ስብከቶች መካከል አንዱና አንጋፋው እንዲሁም የቅዱስ ፓትርያሪኩ ልዩ ሀገረ ስብከት የሆነው አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ነው፡፡ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ካሉበት ውስብስብና ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተነሣ ብጥብጥና ትርምስ የማያጣው ተቋም እየሆነ ከመምጣቱም በላይ በርካታ የሥራ ሐላፊዎችን ያፈራረቀ ነው፡፡
በብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ዘመነ ፕትርክና ብቻ አምስት ሥራ አስኪያጆችን አፈራርቆ ስድስተኛውን ሥራ አሥኪያጅ እየተቀበለ ያለው ይኸው ተቋም የቀድሞዎቹን የሥራ ሐላፊዎች ካነሣ በኋላ በምክትል ሥራ አስኪያጁ መጋቤ ጥበባት ምናሴ ወልደሐና ለሦስት ሳምታት ያክል ሲመራ ቆይቷል፡፡
ትናንት ጥር 24/2011ዓ/ም ከስአት በኋላ በተደረገው የቋሚ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ በሐምሌ ወር 2009 ዓ/ም ከተሾሙት ኤጲስ ቆጶሳት መካከል አንዱ የሆኑትና የጉራጌ ሀገረ ስብከትን እያስተዳደሩ ያሉትን ብጹእ አቡነ መልከጼዴቅን የቅዱስ ፓትርያሪኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ አድርጎ ሲመድብ በምዕራብ ሽዋ ሀገረ ስብከት ሥር የምትገኘው ታሪካዊት የመናገሻ ቅድስት ማርያም ገዳም አበምኔት መ/ር አባ ሞገስ ኃለማርያምን ደግሞ ዋና ሥራ አስኪያጅ አድርጎ እስከ ሚቀጥለው የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ ላሉት ጥቂት ወራት ያስተዳድሩ ዘንድ በጊዜያዊነት ሾሟል፡፡
የአሁኑ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ምደባ ከአሁን በፊት ከነበሩት የብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስና የቋሚ ሲኖዶስ የሹመት አሰጣጥ ለየት የሚያደርገው የመጀመሪያው ነገር ሹመቱ ለጥቂት ወራት የተሰጠ ጊዜያዊ ሹመት መሆኑ ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በስድስተኛው ፓትርያሪክ ማለትም በብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ዘመነ ፕትርክና ከተሾሙት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች ዝርዝር ውስጥ ብቸኛው መነኮስ መሆናቸው ነው፡፡
በጊዜያዊ መልኩ ወደ ሀገረ ስብከታችን የተመደቡት የሥራ ሐላፊዎች በየጊዜው በሁከትና ትርምስ እንዲሁም የተማረውን ወጣት የሰው ኃይል ጡረታ በማውጣት ለሚታወቀው አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተሻለ የመፍትሔ አቅጣጫና አማራጭ ሐሳብ በማቅረብ ወጣቱን የሰው ኃይል በማሳተፍ እንዲሁም የሚሰራበትን የአሠራር system በመዘርጋትና ዘመኑን በመዋጀት የለውጡን በር ይከፍቱት ዘንድ ተስፋ እያደረግን ሰፊ ትንታኔና አጠቃላይ ዘገባው ደግሞ በሚቀጥለው ክፍለ ጊዜ እንደምንመለስበት እናረጋግጣለን፡፡
ለብጹእ አባታችን አቡነ መልከጼዴቅና ለዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አባ ሞገስ ኃይለማርያም መልካም የሥራ ዘመን ይሆንላችሁ ዘንድ ምኞታችን ነው፡፡
በሀገረ ስብከቱ ሚዲያ ክፍል