የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ስዩማን አካለወልድ ተሰማ ፣ ዋና ጸሐፊው መ/ር ታዴዎስ ሽፈራው እና ሌሎችም የየክፍሉ ዋና ኃላፊዎች ከአድባራት ና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ጋር ትውውቅ አደረጉ

በዛሬው ዕለት ታህሳስ 15/2013 ዓ/ም ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባ እና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ስዩማን አካለወልድ ተሰማ ፣የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ መ/ር ታዴዎስ ሽፈራው የየክፍሉ ዋና ኃላፊዎች፣የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች በተገኙበት በሀገረ ስብከቱ የስብሰባ አዳራሽ የትውውቅ መርሃ ግብሩ ተካሂዷል።
በትውውቅ መርሃ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ስዩማን አካለወልድ ተሰማ ወደ ኃላፊነት የመጡበትን ሂደት፣በምን መልኩና እንዴት ባለ መልኩ ምን ምን ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው ግልጽ በሆነ መልኩ አብራርተዋል።
“ወደዚህ ኃላፊነት መጥቼ ከእናንተ ጋር ለመሥራት በመታደሌ በጣም ደስተኛ ነኝ” በማለት የተሰማቸውን ደስታና ሐሴት ለአድባራቱና ገዳማቱ አስተዳዳሪዎች ገልጸው፣ ሁላችንም በመተጋገዝና በመረዳዳት የተሰጠንን መንፈሳዊ አደራ ልንወጣ ይገባል በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
አያይዘውም ሕጋዊ በሆነ መልኩ በሀገረ ስብከቱ አዲስ የተዘረጋውን የአሠራር መስመር ተከትላችሁ ከመጣችሁ ጉዳያችሁን እንፈጽማለን ብለው፣ ለአድባራቱና ገዳማቱ አስተዳዳሪዎች በደብራችሁና በገዳማችሁ ሥር የምታስተዳድሯቸውን ካህናት፣ ዲያቆናትና ሠራተኞች በአግባቡ ከያዛችሁና ችግራቸውን ከፈታችሁ ለእኛ ትልቅ ሥራ ታቃልሉልናላችሁ ሲሉ ገልጸዋል።
የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ መ/ር ታዴዎስ ሽፈራው በተመደቡበት የሥራ ደርሻ በአግባቡና በተገቢው ሁኔታ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸው የአድባራትና የገዳማት አስተዳዳሪዎች ወደ ሀገረ ስብከቱ ለጉዳይ ሲመጡ በር ላይ እንዳይጉላሉ መታወቂያ እየተዘጋጀላቸው መሆኑን አብራርተዋል።
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባ እና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ስለ ዋና ሥራ አስኪያጁ ሊቀ ስዩማን አካለወልድ ተሰማ እንዴት ባለ መንገድ ወደ ኃላፊነት እንደመጡ፣ስለ ትምህርት ዝግጅታቸው፣ስለ ሥራ ልምዳቸው እና ስለ እውቀት ክህሎታቸው ገልጸዋል።
በመጨረሻም ብፁዕነታቸው ለአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ብልሹ አሠራርን በመጸየፍ እውነትን መሠረት አድርጋችሁ አገልግሎታችሁን አከናውኑ በማለት አባታዊ መልእክታቸውንና መመሪያዎችን አስተላልፈዋል።
በትውውቅ መርኃ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ስዩማን አካለወልድ ተሰማ ያስተላለፉትን ሙሉ መልእክት ከዚህ ቀጥሎ ይቀርባል፡-
“እመ ሠምረ እግዚአብሔር ወሐየውነ ንገብር ዘንተ አው ዝክተ” (ያዕ.4፡15)
“እግዚአብሔር ቢፈቅድ ብንኖርም ይህን ወይም ያን እናደርጋለን” (ያዕ.4፡15)
❖ ብፁዕ አባታችን አቡነ መልከጼዴቅ
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና
የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
❖ ክቡራን የሀገረ ስብከታችን የየዋና ክፍል ኃላፊዎች፤
❖ ጥሪ የተደረገላችሁ የሀገረ ስብከታችን የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች
ከሦስት ዐሥርት ዓመታት በፊት አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በቀድሞው አጠራር በሸዋ ጠቅላይ ግዛት ውስጥ የሸዋ ሀገረ ስብከት አንድ አካል የነበረና ራሱን ችሎ በአንድ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሊቀ ጳጳስ ዘሸዋ ይመራ እንደነበረ የቅርብ ግዜ ታሪክ ነው ፡፡
ከዛሬ ሠላሳ ዓመት ገደማ ጀምሮ ግን እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ረዳት ሊቀ ጳጳስ ተመድቦለት ሲተዳደር እንደነበርም ይታወሳል ፤ በተለይ ደግሞ በስድስተኛው ፓትርያርክ ዘመነ ፕትርክና በወጣው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ሕግ ተደንግጎለት በአንቀጽ 50 ቁጥር (1) መሠረት ልዩ ሀገረ ስብከት ተብሎ እየተሰራበት ጥቂት ዓመታትን አስቆጥሯል ፤ ይኹንና በዘንድሮው ዓመት ከጥቅምት 11 እስከ 23 ቀን 2013 ዓ/ም በተካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መዋቅራዊ ጥያቄ ላይና ብልሹ አሠራሮች ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ ዋናው የአስተዳደር ብሉሽነት መሠረትና ለሙስና መስፈፋት ክፍተት የፈጠረው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መዋቅራዊ አሠራሩ መዛነፍ መኾኑን አጽንኦት ሰጥቶ ቅዱስ ሲኖዶስ ከስምምነት ላይ ደርሷል ፤ የተዛነፈው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መዋቅራዊ ጥሰት መገለጫውና ማሳያው የዘመድ አዝማድ አሠራር፤ የአምቻ ጋብቻ ሹመት፤ የብሔር አሰላለፍና የቤተሰብ አስተዳደር እንደኾነም ከቅዱሰ ሲኖዶስ ውሳኔ ለማወቅ ችለናል ፤ በተለይም ሀገረ ስብከቱ በሰው ሀብት አስተዳደር ፤ በኩል የሚሳየው አድሏዊነት ፤ ጎጠኝነት፤ የሥራ ዋስትና ማጣትና ፍትሕ በማጣት ካህናት ለእንግልት መዳረጋቸው የሀገረ ስብከቱ የዓመታት መገለጫ መኾኑ ተመልክቷል፤ በመጨረሻም በፋይናንስ አሠራር ክፍተትና በንብረት አያያዝ ጉድለት ውስጥ የተንሰራፋው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ብልሹ አሠራርን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ከመረመረ በኋላ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እንደማንኛውም ሀገረ ስብከት በራሱ ሊቀ ጳጳስ እንዲመራና በራሱ ሥራ አስኪያጅ ሥራውን እንዲያከናውን ሲል ቅዱስ ሲኖዶስ የሕገ ቤተ ክርስቲያኑን አንቀጽ 50 ንኡስ አንቀጽ (1) ድንጋጌን አሻሽሏል ፡፡
በድንጋጌው ማሻሻያ መሠረትም ቅዱስ ሲኖዶስ ከአበው ሊቃነ ጳጳሳት መካከል ባደረገው ውድድርና ምርጫ እንዲሁም የመጨረሻውም ምርጫ በዕጣ ተከናውኖ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የኾኑት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ላይ ዕጣው በማረፉ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አድርጎ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ መድቧቸዋል ፡፡
❖ ብፁዕ አባታችን አቡነ መልከጼዴቅ
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና
የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
❖ ክቡራን የሀገረ ስብከታችን የየዋና ክፍል ኃላፊዎች፤
❖ ጥሪ የተደረገላችሁ የሀገረ ስብከታችን የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች
ብፁዕነታቸውም ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ኾነው ከተመደቡበት ቀን ጀምሮ ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ጋር በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን መክረዋል ፤ ብፁዕነታቸው ከቅዱስ ሲኖዶስ በተሰጣቸው የመፍትሔ አቅጣጫና ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከተሰነዘረላቸው ምክረ ሐሳብ መነሻነት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ሀገረ ስብከቱ ኅዳር 16 ቀን 2013 ዓ/ም በይፋ በለቀቀው መስታወቅያ ለሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅነትና ዋና ጸሐፊነት አወዳድሮ ለመመደብ ባወጣው መስፈርት መሠረት ከተወዳደሩት ከ64 የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት መካከል በመጀመርያ ዙር በተደረገው የሰነድ ምርመራ በመመረጤ ፤ ከዚያም ለሁለተኛ ዙር ከተመረጡት ከ14 የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት መካከል በተደረገው የጽሑፍ ፈተና በማለፌ እንዲሁም በሦስተኛ ዙር በተደረገው የቃለ መጠይቅ ሂደትና ፈተናን ካለፍኩ በኋላ የትምህርት ዝግጅና የአርዐያ ክህነትን መሥፈርት አሟልቼ በመገኘቴ በሀገረ ስብከቱ የተጠየቀውን ተቀዳሚውን የኃላፊነት ቦታ አግኝቼአለሁ፤ በመኾኑም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኾኜ በመመደቤ፤ እናንተንም ለማገልገል በመመረጤ በዛሬው ዕለትም ከፊታችሁ ቆሜ ለመናገር ዕድል በማግኘቴ ታላቅ ክብር ይሰማኛል ፡፡
❖ ብፁዕ አባታችን አቡነ መልከጼዴቅ
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና
የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
❖ የሀገረ ስብከታችን የየዋና ክፍል ኃላፊዎች፤
❖ ጥሪ የተደረገላችሁ የሀገረ ስብከታችን የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች
የሀገረ ስብከታችን ወሰንና መቀመጫ የኾነችው አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና ከመኾኗ አኳያ አስተዳደሯም መዘመንና መቀላጠፍ እንዳለበት ስናስብ ከሀገረ ስብከታችን የሚጠበቀውን አስተዋጽኦ ለማበርከት የሁላችንም ድርሻ እንደሚያስፈልግ ላሳስባችሁ እወዳለሁ፡፡
በተለይም በእግዚአብሔር ፈቃድ እኛ ወደዚህ ኃላፊነት የመጣነው እግዚአብሔር እስከፈቀደልን ድረስ በአገልግሎታችን አስተዋጽኦ ልናደርግ በምንችልበት ደረጃ በአዲስ አበባ ውስጥ ላሉ ነዋሪዎች ሁሉ የሚጠቅም ቢኾንም ዋናው የሚጠበቅብን ሀላፊነት ግን የሀገረ ስብከታችንን ሠራተኞች የሥራ ዋስትና ማስጠበቅና የካህናትን የኑሮ ደረጃ ማሳደግ ነው ፡፡ ስለኾነም
1.የሀገረ ስብከታችን ሠራተኛ ካህናት በአረጋዊነት ዘመናቸው መጦርያ በማጣት እንዳይጉላሉ የዕድሜ ልክ ደመወዝ ተከፋይ የሚሆኑበትን ሥርዐት በማስጠናት ተግባራዊ ለማድረግ እንሠራለን ፤
2.በሀገረ ስብከታችን አጥብያ አብያተ ክርስቲያናት ያሉ የአጥቢያው ተወላጆች በአጥቢያቸው ከደጀ ጸኝነት ባለፈ ተቀጥረው አጥብያቸውን የሚያገለግሉበት ሥርዐት እንዲዘረጋ ጥናት በማድረግ ወደ ሥራ እንገባለን፤
3.ከሀገረ ስብከት ጀምሮ እስከ አጥብያ አብያተ ክርስቲያናት ድረስ ያሉ ደጅ ጸኚዎች፤ የሀገረ ስብከት ሠራተኞች እና የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ሙሉ ታሪካቸውና የሥራ ልምዳቸው በዳታ ቤዝ- በቴክኖሎጂ መረጃ ቋት ተዘግቦ እያለቀ በመኾኑ የቅጥር፤ የዝውውር ፤ የእድገትና የሹመት ደረጃ ማከናወን ሲያስፈልግ መሥፈርትን መሠረት ያደረገ በዳታ ቤዝ ላይ ባለው መረጃ መሠረት የሚከናወን መኾኑን ከወዲሁ ላሳስብ እወዳለሁ፡፡
4.የሀገረ ስብከታችን አሠራር በዕቅድ ላይ የተመሠረተ እንዲኾን በአሁኑ ሰዓት ለሀገረ ስብከታችን ለየክፍለ ከተማዎች የሥራ ኃላፊዎች ሥልጠና ተሰጥቶ ከጥር ወር ጀምሮ የዘጠና ቀን ዕቅድ በማዘጋጀት በዕቅዳችን መሠረት ለመሥራት ዝግጅታችንን ጨርሰናል ፡፡
5.ለማሳያነት በሀገረ ስብከታችንና በክፍለ ከተሞች የተወጠነው የ90 ቀን ዕቅድ ላይ ተመሠረተ የሥራ ሂደት ወደ አጥብያዎችም ወርዶ ተግባራዊ እንዲኾን በቀጣይ አጥብያዎች በዕቅድ እንዲሠሩ ስልጠና እንሰጣለን፤
6.አዲስ አበባ የሁሉም ሕዝቦችና ማኅበረሰቦች ከተማ ከመኾኗ አንጻር ሀገረ ስብከታችንም ኹሉም ማኅበረ ሰብእ የሚስተናገድበት ሀገረ ስብከት ከመኾኑ የተነሣ ይህንን ማዕከል ያደረገ የተቀላጠፈ አሠራርን ለማከናወን እንዲረዳ የሥራ መመርያ ወረቀቶችንና ጥናታዊ ሰነዶችን እናዘጋጃለን፡፡
7.ልማታዊ ሥራዎችን በተመለከተ አሮጌው ቄራ ተብሎ በሚታወቀው ስፍራ ላይ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠበት ቦታ በመኾኑ ከከፍተኛ ኮንትራክተር ጋር ውል በመግባት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሕንጻውን ለማሠራት በሂደት ላይ ነን ፡፡
❖ ብፁዕ አባታችን አቡነ መልከጼዴቅ
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና
የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
❖ ክቡራን የሀገረ ስብከታችን የየዋና ክፍል ኃላፊዎች፤
❖ ጥሪ የተደረገላችሁ የሀገረ ስብከታችን የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች
ትላንት አባቶቻችን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና ሊቃውንት ምዕራፍና ቁጥር ጠቅሰው፤ መጻሕፍትን አልበው፤ መናፍቃንን ተከራክረው፤ ዓላውያን ነገሥታትን ገሥጸውና አስተዳደራዊ ክሂሎታቸውን ተጠቅመው ሃይማኖታችንን ከነቅርሷና ባሕሏ ጠብቀው ለእኛ ለልጆቻቸው አስረክበውናል ፡፡
እኛም እነርሱ ያስረከቡንን ቤተ ክርስቲያናችንን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍና ሕዝበ ክርስቲያኑ በስብከተ ወንጌል ተደራሽ እንዲኾን ለማድረግ እንዲሁም የተቀላጠፈ ፤ ዘመናዊና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሥራ ተዋረድና የዕዝ ሰንሰለቱን በጠበቀ መልኩ ኃላፊነታችንን ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን ፡፡
ኾኖም የሀገረ ስብከታችን ሥራ በአጭር ቀናት እንደገመገምነው ከኾነ በአንድ በኩል ዘመናዊውና መልካም አስተዳደር እንዲፋጠን የሚፈልጉ ለውጥ ፈላጊዎች እንዳሉ ሁሉ በአንጻሩ ደግሞ የነበረውን የተበላሸ አሠራር ለማስቀጠል መስዋትነት የሚከፍሉ ጎታች አካላት እንዳሉ ለመረዳት ችለናል፡፡
አመራራችንን ፈታኝ የሚያደርጉትና የሥራ ክፍተት የሚፈጥሩት የእነዚህ ኹለት ኃይሎች መጓተትና መሳሳብ እንደሚሆን ከማንም የሚሰወር ባለመኾኑ የአሠራር ክፍተት የተፈጠረ እንደኾነ ሐሳብና አስተያየት ለመቀበል ቢሮአችን ለማናችሁም ቢሆን ዘወትር ክፍት መኾኑን እገልጻለሁ ፤ ይህንን ስንል በአሠራር ሂደታችን ከዚህ ቀደም ያሉትን ጎታች አካላት ለመውቀስ ሳይሆን ያሳኳቸውን የሥራ ውጤቱችና ጥበቦች ለማስቀጠልና የነበሩባቸውን ጉድለቶች ደግሞ ለመዝጋት እንሠራለን ፤
ስለኾነም ፤
1.በሥራ ሂደት የሚያጋጥመን የሥራ ክፍተት ምን አልባትም በራሱ ችግር አለመኾኑ ቢታወቅም፤ ችግር የሚሆነው ግን መፍትሔ ሰጭው አካል ተጨማሪ ችግር ሲፈጥር መኾኑን ስለምንገነዘብ ወሳኝ አካላት የኾንን በዚህ የተሰበሰብን የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች በራሳችን የመፍትሔ አካላት እንድንኾን እያሳሰብኩ እኔም እንደ ሥራ አስኪጅነቴ ባለኝ ኃላፊነት መፍትሔ ለመስጠት ፈጣን መሆኔን ለመናገር እወዳለሁ ፡፡
2.ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ደም ተመሠረተችበት ዓላማን ለመፈጸም በዕውቀትና በአስተዳደር ጥበቧ በኹለት እግሮቿ ቆማ ወደ ስብከተ ወንጌል ልዕልና እንድትራመድ ለማድረግ የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎችን ከማስመደብ ጀምሮ ከተሰየምኩበት የሥራ አስኪያጅነት ኃላፊነት የሚጠበቀው ነገር ቢኖር መሥፈርቶችን በማውጣት ፤ ስልታዊ አቅጣጫዎችን በመቀየስና ወደ አፈጻጸም ሥራ ለመግባት ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጰስ ጋር በመማከርና እንደየአስፈላጊነቱም በአስተዳደር ጉባኤው በማስወሰን በሕግ አግባብ ብቻ እንደምሠራ በፊት ለፊታችሁ ቃል እገባለሁ ፡፡
3.በአዲስ አበባ አብያተ ክርስቲያናት ሊቃውንቱ እየተገፉ በስመ ሊቃውንት አፈ ቀላጤዎችና ጮሌዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚሰገሰጉበት አካሄድ እንዲያበቃ የሥራ ቅጥርና ዕድገት የትምህርት ዝግጅትና ችሎታ ላይ ብቻ የተመሠረተ እንዲኾን የበኩሌን ኃላፊነት እንድወጣ የእናተም አጋዥነት እንዳይለየኝ አደራ እላለሁ ፡፡
4.የሥራ ተዋረድንና መስመሩን ባልጠበቀ መልኩ ሲደረጉ የነበሩትን ዓይነት ቅጥሮችን፤ ዕድገቶችንና ዝውውሮችን ላለማድረግ ከፍተኛውን ጥረት እናደርጋለን ፡፡ ለዚሁ ጥረታችን መሳካት የሀገረ ስብከታችን የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ልማዳዊ አሠራሩን በማስቀረትና መዋቅራዊ አሠራሩን ብቻ በመከተል በጋራ እየተናበብን እንድንሠራ ከአደራ ጭምር አሳስባለሁ፤
5.አዲስ ምእራፍ ላይ ያለን መኾናችንን ታሳቢ በማድረግ አንዳንዶች ኾን ብለው የሀገረ ስብከታችን አሠራር ላይ ዕንቅፋት በመፍጠርና እኛንም መሸጋገርያ ለማድረግ የሚሠሩ አካላት እንዳሉ ከግምት በማስገባት እናንተ የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች ከሐሰተኛ ወሬ እየተጠበቃችሁ ሕግን መሠረት ባደረገ አሠራር ብቻ እንድትሰሩ በአጽንዖን አደራ እላለሁ፡፡
6.የስራ አስኪያጅነት ኃላፊነት በጋራና በመናበብ የሚሠራ እንጂ በተናጠል ባለ ዕውቀትና ችሎታ ብቻ የሚሠራ ባለመኾኑ ሀገረ ስብከቱ የሚቀይሰው ስልታዊ እቅድና አቅጣጫ ተግባራዊ እንዲሆን ሁላችሁም ተባባሪ እንድትኾኑ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ ፡፡
7.አንድ በአጽንኦት ለማስተላለፍ የምፈልገው ሐሳብ ቢኖር ከላይ እንደተጠቀሰው ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ በቅዱስ ሲኖዶስ ጥቆማና ዕጣ በመመረጣቸውና እኔም ብኾን ከ64 ተወዳዳሪ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን መካከል በተደረገው ውድድር በዚህ ኃላፊነት ላይ ለመሰየም በመብቃቴ እኔ በሕጉ መሠረት ብቻ ቤተ ክርስቲያንን ላገለግል እንጂ የማንም ውለታም ኾነ ወሮታ ለመክፈል ዕዳም ኾነ ዕገዳ የሌለብኝ መኾኔን ላስገነዝባችሁ እወዳለሁ ፡፡
❖ ብፁዕ አባታችን አቡነ መልከጼዴቅ
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና
የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
❖ ክቡራን የሀገረ ስብከታችን የየዋና ክፍል ኃላፊዎች፤
❖ ጥሪ የተደረገላችሁ የሀገረ ስብከታችን የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች
✔️በማጠቃላዬም ወደ ምስጋናና ምርቃት ስመጣ በመጀመርያ ዘወትር የማመሰግነው ልዑል እግዚአብሔር አሁንም የተመሰገነ ይሁን ፡፡
✔️ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች! የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ብልሹ አሠራርን እንዲስተካከልና መዋቅራዊ ጥቃቱ እንዲለወጥ የታገላችሁበት የዓመታት ጩኸታችሁና ጥያቄአችሁ መልስ በማግኘቱ ልትደሰቱ ይገባል እያልኩ ለዚህ ድካማችሁ በቤተ ክርስቲያን ስም ላመሰግናችሁ እወዳለሁ ፡፡
✔️ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ባለበት ተግባራዊ እንዲኾን አፈጻጸሙን የተገበራችሁ አባቶችና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም ምስጋናዬ ይድረሳችሁ !!!
✔️ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አባታችን ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ከእኔ ጋር ለመሥራት ያሳዩት ተባባሪነት ዘወትር እንዳመሰግንዎት ያደርገኛል ፡፡
☑️ ለዓመታት ይህንን ጥያቄ ስትጠይቁ የኖራችሁ ጭቁን ካህናትም እግዚአብሔር በዕድሜና በጤና ያቆያችሁ ይጠብቃችሁ እያልኩ ምስጋናዬ በያላችሁበት አቀርባለሁ፡፡
☑️ “እመ ሠምረ እግዚአብሔር ወሐየውነ ንገብር ዘንተ አው ዝክተ” ( ያዕ.4፡15)
☑️ “እግዚአብሔር ቢፈቅድ ብንኖርም ይህን ወይም ያን እናደርጋለን” ( ያዕ.4፡15)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር
አሜን !!!
ዘጋቢ መ/ር ደምሴ አየለ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ