የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በዘመናዊ የሒሳብ አያያዝ ያሰለጠናቸውን 36 ሒሳብ ሹሞችን አስመረቀ
የምርቃቱ ሥነ ሥርዓት ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እና የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ፤ ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መ/ር አባ ሞገስ ኃይለማርያም(ቆሞስ)፣ የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎችና ሠራተኞች ፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ሊቃነ መናብርት፣ዋና ጸሐፊዎች በተገኙበት በ14/2011ዓ.ም በደማቅ ሁኔታ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የስብሰባ አዳራሽ ተካሂዷል፡፡
ሥልጠናውን ሲከታተሉት የነበሩት ተመራቂዎች ከአድባራትና ከገዳማት የተውጣጡ 36 ሒሳብ ሹሞች ሲሆኑ ሥልጠናውም ዘመናዊ የሒሳብ አያያዝን የተመለከተ ነው፡፡ ሀገረ ስብከቱ ዘመናዊ የሒሳብ አያያዝን በተመለከተ በአንድ የሥልጠና መርሃ ግብር ላይ 36 ሰልጠኞችን በአንድ ጊዜ አሰልጥኖ ማስመረቁ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡
ሥልጠናው ሁለት ሳምንታትን ወይም 120 ሰዓታትን የፈጀ ሲሆን ሥልጠናውን የሰጡት የሀገረ ስብከቱ የሒሳብና በጀት ዋና ክፍል ኃላፊ የሆኑት ሊቀ ጠበብት ኢልያስ ተጫነ ሥልጠናውን ለሰልጣኞች በሚገባቸው መልኩ በበቂ ሁኔታ አሰልጥነዋቸዋል፡፡
ሀገረ ስብከቱ በአሁን ሰዓት በእድገት ላይ የሚገኝ መሆኑን የገለጹት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እና የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ መልከ ጼዴቅ እነዲህ ያለው ሥልጠና የገንዘብና የንብረት አያያዝን ዘመናዊና የተቀላጠፈ እንደሚያደርገው ገልጸዋል፡፡ አክለውም ይህ አይነት አሠራር የሀገረ ስብከቱን የገንዘብንና የንብረትን ብክነት በእጅጉ እንደሚቀርፍና ከዘመኑ የሒሳብ አሠራር ጋር እኩል እንድንጓዝ ያደርጋል ሲሉ የተሰማቸውን ጥልቅ ደስታ አያይዘው ገልጸዋል፡፡
ሥልጠናውን የሰጡት የሀገረ ስብከቱ የሒሳብና በጀት ዋና ክፍል ኃላፊ የሆኑት ሊቀ ጠበብት ኢልያስ ተጫነ ሀገረ ስብከቱ ዘመናዊ የሒሳብ አያያዝ በተመለከተ ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት ተጀምሮ እንደነበርና ነገር ግን በመሃል እንደተቋረጠ ገልጸው ይህ የዘመናዊ የሒሳብ አያያዝን አስመልክቶ ሥልጠና አሁን መሰጠቱ የሀገረ ስብከቱን የገንዘብና የንብረት አያያዝ እንደሚያዘምነው እና ግልጽ የሒሳብ አሠራር እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል፡፡
ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ለተመራቂዎች ሰርተፊከት ከሰጡ በኋላ አባታዊ ምክራቸውንና የሥራ መመሪያ አስተላልፈዋል፡፡ ሀገረ ስብከቱ በሰጠው ሥልጠና እጅግ በጣም መደሰታቸውን ገልጸው ተመራቂዎችም ይህንን በሥልጠና የቀሰሙትን እውቀታቸውን በተግባር እንዲያውሉ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን አስተዳደርን፣ስብከተ ወንጌልን፣ሰንበት ትምህርት ቤትን እና በመሳሰሉትም ርእሰ ጉዳዮችም ላይ ሥልጠና ቢሰጥ እጅግ መልካም እንደሆነ ገልፀው ለወደፊት ለመወያየትም ሆነ እንዲህ ያሉ መርሃ ግብሮች ሲዘጋጁ እሳቸውም በሀገረ ስብከቱ እንደሚገኙ መልካም ፍቃዳቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡