የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ሲያካሄድ የቆየው አንደኛ መደበኛ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በሰላም ተጠናቀቀ

በትናንትናው ዕለት በተካሄደው አንደኛ መደበኛ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ ሪፖርቶች መቅረባቸውን፣ሊሠሩ የታሰቡ ዕቅዶች መደመጣቸውን፣ “ሰበካ ጉባኤ ትናንትና እና ዛሬ” በሚል ርእስ ዳሰሳዊ የጥናት ጽሑፍ መቅረቡንና ውይይት መካሄዱን የዘገብን መሆኑ ይታወሳል።
በዛሬው የመክፈቻ መርሃ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በክልል ትግራይ ደቡባዊ ዞን ማይጨውና ደቡባዊ ምሥራቅ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እያካሄደ ያለውን አንደኛ መደበኛ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አድንቀው ቤተክርስቲያን በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ ብትሆንም ጠንክረን በመሥራት የቤተክርስቲያኒቱን ሕልውና ልናስቀጥል ይገባል፣መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን በአንድ መንፈስ ሆነን በጋራ መሥራት አለብን ብለዋል።
በተያያዘ ዜናም “መልካም አስተዳደር ለቤ/ክ ሁለንተናዊ አገልግሎትና ልማት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ” በሚል ርዕስ ዳሰሳዊ ጥናት በሊ/ት በድሉ አሠፋ የቀረበ ሲሆን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ መርሃ ግብር መሪነት በቀረበው ዳሰሳዊ ጥናት ላይ በመመርኮዝ የተጠኑ ጥናቶች በተግባር ላይ እንዲውሉ፣ቅጥርን፣ዝውውርንና እድገትን በተመለከተ እንዲሁም በስብከተ ወንጌል ዙርያ ሰፊ ሥራ መሠራት እንዳለበት ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጓል::
በጉባኤው ላይ በአርቃቂ ኮሚቴ ባለ አስር ነጥብ የጋራ መግለጫ አቋም ከተነበበ በኋላ ስብከተ ወንጌልን ጨምሮ በቤተክርስቲያኒቱ ባሉ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች አመርቂ ውጤት ላስመዘገቡ፣ ከላይ የሚወርድን መመሪያ የፈጸሙና በግጭት አፈታት ላይ ትልቅ ሚና ለተጫወቱ ገዳማትና አድባራት ከእያንዳንዱ ክፍላተ ከተማ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ለወጡትና ለሰባቱ ክፍላተ ከተማ የማበረታቻ ሽልማትና የምስክር ወረቀት ከብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ተበርክቶላቸዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለቅዱሳን ፓትርያርኮች፣ ለብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ፣ ለብፁዕ አቡነ ያሬድ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ለብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ለመ/ር አካለወልድ ተሰማ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅና ለመ/ብ ሳሙኤል ደምሴ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ዋና ክፍል ኃላፊ የሽልማት ስጦታ ተበርክቷል።
በመጨረሻም በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጉባኤው በሰላምና በውጤታማነት እንዲጠናቀቅ “የረዳን ልዑል እግዚአብሔር ይመስገን” ካሉ በኋላ የስብከተ ወንጌልን እንቅስቃሴ በሰፊው ለማካሄድ፣ጥናታዊ ጽሑፎችን ስለ ማዘጋጀትና ወደፊት ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን ጠቅሰው ለሁለት ቀናት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ጽርሐ ተዋሕዶ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ሲካሄድ የቆየው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት አንደኛ መደበኛ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በዛሬው ዕለት የካቲት 20/2013 ዓ.ም በጸሎት ተጠናቋል።


ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ