የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤትን ለመመርመር በጠቅላይ ቤተ ክህነት የተቋቋመውን አጥኚ ኮሚቴ አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ።

መስከረም 10 ቀን 2017 ዓ.ም በቁጥር 782/354/2017 ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ለአጣሪ ኮሚቴ በአድራሻ ሲጻፍ በተመዘገበልን ግልባጭ ለመገንዘብ እንደቻልነው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የሚስተዋሉ የአመራር ግድፈቶችንና በአሠራር ላይ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን አጥንቶ የሚያቀርብ ኮሚቴ መቋቋሙን ተረድተናል፡፡
ለኮሚቴው መቋቋም ምክንያቱ “በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የሚስተዋሉ የአሰራር ግድፈቶች ላይ የተፈጠሩ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ በአገልጋይ ካህናትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች ላይ ከፍተኛ ችግር እያስከተሉ መሆኑ” እንደሆነ በደብዳቤ ተገልጿል፡፡ የአጥኚ ኮሚቴው አባላትም አመራረጥ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ከምእመናን እና ከማኅበራት የተውጣጡ መሆኑንም ተረድተናል፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጠቅላይ ቤተ ክህነት አቋቋምኩት ያለውን ኮሚቴም ሆነ በኮሚቴ ስም የሚቀርብን የጥናት ሪፖርት በሚከተሉት ምክንያቶች የማይቀበለው መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡-
1. ጠቅላይ ቤተ ክህነት አጥኚ ኮሚቴ ያቋቋመው ምንም ዓይነት ለኮሚቴው መቋቋም የሚያበቃ ቅሬታ ሳይቀርብለት እና በማስረጃ የያዘው አቤቱታና ወቀሳ ሳይኖር በመላምት እና በግል ስሜት በመነሳሳት አጀንዳ ለመፍጠር እንደሆነ የተቋቋመው ኮሚቴ በመግቢያ ስብሰባው ለከሳሾች ካቀረበው ጥሪ እና ማስረጃ ፍለጋ ካስተላለፈው መልእክት ለመገንዘብ ችለናል፡፡ይህ በመሆኑም በሀገረ ስብከታችን ላይ ሰዎች ክስ እንዲያቀርቡ የሚያነሳሳ መግለጫ ለመስጠት የተገደደው ቅሬታ ሳይቀርብ በአየር ላይ ማስረጃ የተቋቋመ ስለሆነ ነው።
2. በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚታይ የአስራር ችግር ካለ አንዱና ዋነኛው የችግሩ አካል ጠቅላይ ቤተ ከህነቱ ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ ለ2015 ዓ.ም ለሀገረ ስብከቱ መተዳደሪያ ደንብ አርቅቆ አጸድቆ ሲሰጥ ፣ አስተዳደር ጉባኤውን በትኖ አዲስ አስተዳደር ጉባኤ በመሰየም፣ ከሕግ ውጪ በሀገረ ስብከቱ የውስጥ አሠራር ጣልቃ የሚገባው ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መሆኑ የዐደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በሌላም በኩል በተለያዩ ጊዜያት ከሀገረ ስብከታችን ጥያቄ ሳይቀርብ ሠራተኛ እየመደበ በግዳጅ የሚያሠራን በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት በማስረጃ ያልተደገፉ ከአሉባልታ ያልዘለሉ ነገር ግን የሀገረ ስብከቱንም ሆነ የቤተክርስቲያኑን ስም የሚያጠፉ ዘመቻ በተገኘው ዐውደ ምሕረት የሚያስተላልፈው ሆን ተብሎ የሀገረ ስብከቱን ስም እና የሊቀጳጳሱን የአሠራር ሂደት ለማጠልሸት አነጣጥሮ እና አልሞ የቅስቀሳ ሥራ የሚሠራው ጠቅላይ ቤተክህነቱ ነው፡፡
የዚህ ችግር አካል የሆነው ጠቅላይ ቤተክህነት ራሱን እንደገለልተኛ እና ንፁሕ አካል አድርጎ በመቁጠር በሌለ ሕግ እና አደረጃጀት በቤተክርስቲያኗ ላይ ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ እራሱን በመቁጠር ያቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ ልንቀበለው አንችልም፡፡ማጣራት የሚያስፈልግ እንኳ ቢሆን አጣሪ ሊሰየም የሚገባው የሁለቱም መዋቅሮች የበላይ በሆነው በቅዱስ ሲኖዶስ ነው።
3. የተቋቋመው ኮሚቴ የቤተ ክርስቲያንን የአስተዳደር ሥርዓት ከአስተዳደሩ ውጪ ላሉ አካላት አሳልፎ ከመስጠት ባሻገር የቤተክርስቲያንን አስተዳደር ከአስተዳደር መዋቅር ውጪ ባሉ አካላት እንዲመረመር የሚፈቅድ ሕግ በሌለበት ሀገረ ስብከቱን ለእነዚህ አካላት አሳልፎ የሚሰጠውን የአጣሪ ኮሚቴ መሰየም ምን ዓይነት አጀንዳ ለመፍጠር እና ርካሽ ተወዳጅነትን ከመፈለግ አኳያ ነው እንጂ እውነት ለተቋሟ ታስቦ እንዳይደለ ስለምናውቅ ለመቀበል እንቸገራለን፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የምእመናን እና ማኅበራትን አጥኚ ኮሚቴ ውስጥ ያካተተው ሆን ተብሎ ሀገረ ስብከቱን ከምእመናን እና ከማኅበራት ጋር በማጋጨት የእራስን ስውር አላማ በሦስተኛ ወገን ለማስፈጸም እና የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደራዊ መዋቅር ለመናድ ታሳቢ ያደረገ እንጂ አሠራሩን የሚፈቅድ ሕግ ኖሮ አይደለም።
4. የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለአስተዳደር እንዲያመች የተዋቀሩ የአስተዳደር እርከኖች ቢሆኑም ሁለቱም የሚመሩት ተጠሪነታቸው ለቅዱስ ሲኖዶስ በሆኑ ሊቃነ ጳጳሳት ሆኖ ሳለ የተሰየመው አጥኚ ኮሚቴ የአንድን ሊቀ ጳጳስ የአመራርነት ሒደት ከቤተ ክርስቲያን አስተዳደር መዋቅር ውጪ በሆነ አካላት እንዲመረመር የሚያደርግ በመሆኑ ሀገረ ስብከታችን አይቀበለውም፡፡ ሕግ እና አሠራር ባይፈቅዱም ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ ባሉ የቤተክርስቲያን አስፈፃሚ አካላት የአሁኑ መርማሪ ምርጫ ሂደት ተቀባይነት የለውም እንጂ ይሁን እንኳ ከተባለ አንድ ሊቀጳጳስ መጣራት ያለበት በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በሊቃነ ጳጳሳት በሚመራ ልዑካን ሊሆን እንደሚገባ አንጠራጠርም፡፡
5. የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በምጣኔ ሃብት ስፋት እና ባሉት አገልጋዮች ብዛት እንዲሁም ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኝ ሆኖ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ ቅርብ መሆኑ ለእይታ እና ለክትትል ምቹ ሁኔታን ፈጥሮ ካልሆነ በስተቀር ከሌሎች አኅጉረ ስብከት የሚለይበት ምንም ዓይነት ምክንያት እንደሌለ ሕገ ቤተክርስቲያኑ በግልጽ አስቀምጦታል፡፡ በሀገረ ስብከታችን ስራ እስከሰራን ድረስ የአስራር ችግሮች የለብንም ፍፁማን ነን ብለን አናምንም ቢኖሩም እንኳን ከሌሎች አኅጉረ ስብከት የተለየ የአስተዳደር ችግር የለበትም፡፡ በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ አኅጉረ ስብከት የሚስተዋሉ አለመግባባቶች እንዳሉ እየታወቀ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን ብቻ ለይቶ የሚያጠና አካል መሰየሙ ምክንያታዊ አይደለም።
6. ጠቅላይ ቤተ ክህነት በየጊዜው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን የፋይናንስ ሒደት የምርመራ ኦዲት እያደረገ በዚህም ሂደት ያገኘው ጉድለት ኖሮ የወሰደው የማስተካከያ እርማት ሳይኖር እንዲሁም ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሀገረ ስብከቱን የሰው ኃይል ቅጥር እድገትና ዝውውር ምክንያት በማድረግ ቅሬታ ቀረ በልኝ በማለት በተደጋጋሚ ምርመራ ያደረገ ቢሆንም በተለይም በቅርቡ በአስተዳደር ጉባኤ ውሳኔ የተሰየሙ አጣሪዎች በአካል ቀርበው በሰነድ በመስክ ጉብኝት እንዲሁም በቪዲዮ ጭምር የተቀረጸ ማጣራት ተደርጎ የተገኘ ጉድለት ወይም የተሰጠ ማስተካከያ መመሪያ ሳይኖር አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በድጋሚ አጣሪ መሰየሙ አሳማኝ ሆኖ ስላላገኘነው አንቀበልም፡፡
7. የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የአሁን ድርጊት ከመዋቅር ውጪ ያሉ አካላትን የቤተ ክርስቲያን መዋቅርን እንዲያጠና በማድረግ ቀደም ሲል በኦሮሚያ እና በትግራይ ባሉት አኅጉረ ስብከት የተከሰተውን ችግር ወደ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚያስፋፋ ሁከት የሚያነግስ በመሆኑ አንቀበለውም፡፡
ስለዚህ ከላይ በዝርዝር የተቀመጡትን ምክንያቶች የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በጠቅላይ ቤተ ክህነት መስከረም 9 ቀን 2017 ዓ.ም የተቋቋመውን አጣሪ ኮሚቴ እና በስሙ የሚቀርበውን ሪፖርት እንደማይቀበለው የአስተዳደር ጉባኤ የወሰነ መሆኑን ስንገለጽ ይህ ጉዳይ ለሀገረ ስብከታችን ብሶት እና ችግር መግለጫ ቢሆንም በግልባጭ የምናሳውቃችሁ የበላይ አካላት እና መንግስታዊ ተቋማት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ስልጣንን መከታ በማድረግ በሀገረ ስብከቱ እየደረሰ ያለውን ፀብ አጫሪነት በትኩረት እንድትከታተሉት ከአደራ ጋር እናሳስባለን፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት