የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት ካህናት አዲስ ለተመደቡት ዋና ሥራ አስኪያጅና ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቀባበል አደረጉ!!!
በመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅ/ጊዮርጊስ ቤ/ክ በዋና ጸሐፊነት ሲያገለግሉ የነበሩት ሊቀ ማእምራን የማነ ብርሃን ዘመንፈሰ ቅዱስ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ የሊቃውንት ጉባኤ አባል በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት መጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር ምክትል ሥራ አስኪያጅ በመሆን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ተመድበዋል፡፡
አዲስ የተመደቡት ዋና ሥራ አስኪያጅና ምክትል ሥራ አስኪያጁ ዛሬ መጋቢት 16/2007 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሲደረሱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና የክፍል ኃላፊዎች እና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር የሚገኙ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፤ ካህናትና ሰባኪያን ወንጌል ደማቅ አቀባበል አድርገዉላቸዋል፡፡
በተለይ ሊቀ ማዕምራን የማነ በዋና ጸሐፊነት ሲይገለግሉ የነበሩበት የመናገሻ ገነተ ጸጌ ቅ/ጊዮርጊስ ቤ/ክ ካህናት ልብሰ ተክህኖ በመልበስ ነበር በሀገረ ስብከቱ አዳራሽ በመገኘት አቀባበል ያደረጉላቸው፡፡
በመቀጠልም አዲሱ ሥራ አስኪያጅና ምክትል ሥራ አስኪያጁ በሀገረ ስብከቱ አዳራሽ በመገኝት ለሀገረ ሰብከቱ ሠራተኞችና ከየአጠቢያው ለተሰበሰቡት የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፤ ሰባኪያን ወንጌልና ልዩ ልዩ ሠራተኞች አጠር ያለ ንግግር አርገዋል፡፡
ተሰብሳቢዎቹም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በቤተክርስቲያናችን ውስጥ በላቸው የሥራ ልምድና የትምህርት ዝግጅት በግንባር ቀደምትነት ከሚታወቁት የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች መካከል ሊቀ ማዕምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ እና መጋቢ ብሉይ አእመረ አሸብርን ዋና ሥራ አስኪያጅና ምክትል ሥራ አስኪያጅ አድርገው በመመደባቸው የተሰማቸውን ደስታ ከመግለጻቸውም ባሻገር ሊቀ ማእምራን የማነ ብርሃን እና መጋቤ ብሉይ አእመረም ያላቸውን የሥራ ልምድና የአካዳሚክ እውቀት በመጠቀም በሀገረ ስብከቱ ብሎም በሀገረ ስብከቱ ሥር ባሉ ገዳማትና አድባራት አዎንታዊ ለውጥ ማምጣት ይችላሉ ሲሉ አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም ሁለቱም (ዋና ሥራ አስኪያጅና ምክትል ሥራ አስኪያጁ) በሀገረ ስብከቱ እና በሀገረ ስብከቱ ሥር ባሉ ገዳማትና አድባራት በርካታ የተማረ የሰው ኃይል ስላለ ከነሱ ጋር በመመካከር ለቤተክርስቲያናችን ብሎም ለሀገራችን እድገት በታማኝነት እና በቅንነት ለማገልገል ቃል እንገባለን ሲሉ በሀገረ ስበከቱ ሠራተኞችና ከየአጥቢያው በተሰበሰቡት የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች ፊት ቃል ገብተው የዕለቱ ፕሮግራም በጸሎት ተዘግቷል፡፡
{flike}{plusone}